መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 11

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብለው እንደ ነበር ሰሙ።
2ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቶ በነበረ ጊዜ፣ ከመገረዝ ወገን የነበሩት ነቀፉት፤
3“ካልተገረዙ ወንዶች ጋር ተባብረሃል፣ አብረሃቸውም በልተሃል!” አሉት።
4ጴጥሮስ ግን እንዲህ ብሎ ጉዳዩን በዝርዝር ያብራራላቸው ጀመር፤
5እኔ በኢዮጴ ከተማ እጸልይ ነበር፤ በተመስጦም አራት ማዕዘን ያለው ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ መያዣ ከሰማይ ሲወርድ ራእይ ዐየሁ፤ ወደ እኔ ወረደ፣
6ትኵር ብዬ ተመለክትሁትና ስለ እርሱ ዐሰብሁ። አራት እግር ያላቸው የምድር እንስሳትን፣ አራዊትን፣ የሚሳቡ ፍጥረታትን፣ የሰማይ አዕዋፍንም ዐየሁ።
7በዚያን ጊዜ አንድ ድምፅ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፣ ተነሣ፣ አርደህም ብላ!” ሲለኝ ሰማሁ።
8“ጌታ ሆይ፣ አይሆንም፣ ምክንያቱም ጸያፍ ወይም ርኩስ የሆነ ምንም ነገር ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም” አልሁ።
9ነገር ግን ድምፁ ዳግመኛ ከሰማይ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ነው ያለውን አንተ ርኩስ ብለህ አትጥራው” ብሎ መለሰ።
10ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፤ ከዚያም ሁሉም ነገር እንደ ገና ወደ ሰማይ ተወሰደ።
11እነሆ፣ ወዲያውኑ እኛ በነበርንበት ቤት ፊት ለፊት ሦስት ሰዎች ቆመው ነበር፤ እነርሱም ከቂሣርያ ወደ እኔ የተላኩ ናቸው።
12መንፈስም ከእነርሱ ጋር እንድሄድ፣ ስለ እነርሱም ልዩነት እንዳላደርግ አዘዘኝ። እነዚህ ስድስት ወንድሞች አብረውኝ ሄዱ፤ ወደ ሰውዬውም ቤት ገባን።
13እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና እንዲህ እንዳለውም ነገረን፤ “ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ላክና ሌላው ስሙ ጴጥሮስ የሆነውን፣ ስምዖንን አስመጣ።
14አንተና ቤተ ሰቦችህ ሁሉ የምትድኑበትን መልእክት ይነግርሃል።”
15ለእነርሱ መናገር እንደ ጀመረና ልክ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ሆነው፣ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደ።
16“ዮሐንስ በእርግጥ በውሃ አጥምቆ ነበር፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” ብሎ እንደ ተናገረ፣ የጌታን ቃሎች አስታወስሁ።
17እኛ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመንን ጊዜ እንደ ሰጠን ያለ ስጦታ እግዚአብሔር ለእነርሱ ከሰጣቸው እንግዲያ፣ እግዚአብሔርን እቃወም ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?”
18እነርሱ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ፣ መልስ አልሰጡም፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን አመስግነው፣ “እግዚአብሔር ለአሕዛብ ለሕይወት የሚሆን ንስሓን ደግሞ ሰጥቷቸዋል” አሉ።
19ስለዚህ በእስጢፋኖስ መሞት የተጀመረው ሥቃይ ከኢየሩሳሌም የበተናቸው እነዚህ አማኞች እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄዱ። ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን መልእክት ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለሌላ ለማንም አልተናገሩም።
20ነገር ግን ከቆጵሮስና ከቀሬና የነበሩ ሰዎች አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው ለግሪኮች ተናገሩ፤ ጌታ ኢየሱስንም ሰበኩላቸው።
21የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ በቍጥ ብዛት ያላቸው ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ።
22ስለ እነርሱ ወሬ በኢየሩሳሌም ባለችው ጉባኤ ተሰማ፤ በርናባስንም እስከ አንጾኪያ ላኩት።
23እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ስጦታ ባየ ጊዜ፣ ደስ አለው። ከሙሉ ልባቸው ከጌታ ጋር እንዲኖሩ ሁላቸውንም አበረታታቸው።
24ምክንያቱም እርሱ መንፈስ ቅዱስና እምነት የሞላበት በጎ ሰው ነበር፤ ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ።
25ከዚያም በርናባስ ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ ወጣ።
26ባገኘውም ጊዜ፣ ወደ አንጾኪያ አመጣው። እንዲህም ሆነ፣ አንድ ዓመት ሙሉ በቤተ ክርስቲያን አብረው ተሰበሰቡ፣ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ። ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።
27በእነዚያ ቀናትም አንዳንድ ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ።
28ከእነርሱ አንዱ አጋቦስ የተባለው፣ ተነሥቶ ቆመና በመላው ዓለም ላይ ታላቅ ራብ እንደሚሆን በመንፈስ አመለከተ። ይህም በቀላውዴዎስ ዘመን ሆነ።
29ስለ ሆነም፣ ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው እንደ ዐቅማቸው በይሁዳ ላሉት ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ።
30ይህንም አደረጉ፤ በበርናባስና በሳውል እጅ ለሽማግሌዎቹ ገንዘብ ላኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።