መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2 ጢሞቴዎስ 3

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ነገር ግን ይህን እወቅ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት አደገኛ ዘመን ይመጣል፡፡
2ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትእቢተኞች፣ ትምክህተኞቸ፣ በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል የሚናገሩ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣
3ተፈጥሮአዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ሰላምን የማይፈጥሩ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ አመጸኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣
4ከዳተኞች፣ ምክርን የማይሰሙ፣ በትእቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፡፡
5እግዚአብሔርን የመምሰል መልክ አላቸው ነገር ግን ኃይሉን ይክዳሉ፣ ከእነዚህ ሰዎች ራቅ፡፡
6ከእነዚህም አንዳንዶች በቤተ ሰብ ውስጥ ሾልከው እየገቡ በኃጢአት የሚገረሙትንና በልዩ ልዩ ምኞትም የሚነዱትን ሞኞችን ሴቶች ይማርካሉ፡፡
7እነዚህ ሴቶች ሁል ጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ይሞክራሉ፣ ነገር ግን ፈጽሞ ወደ እውነት እውቀት ሊደርሱ አይችሉም፡፡
8ኢያኔስ እና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደተቃወሙት፣ እነዚህ የስህተት አስተማሪዎች እውነትን ይቃወማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አዕምሮአቸው የተበላሸባቸው፣ የእምነታቸውም እውነተኝነት ያልተረጋገጠ ነው፡፡
9ዳሩ ግን የእነዚያ የሁለቱ ሰዎች ሞኝነት እንደተጋለጠ፣ እነዚህም ሞኝነታቸው ይገለጣልና አይሳካላቸውም፡፡
10አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ መጽናቴን፣ ፍቅሬን፣ ትእግስቴን፣
11ስደቴን፣ መከራዬን፣ በአንጾኪያ፣ በኢቆንዮን እና በልስጥራን የደረሰብኝን ሁሉ ተከትለሃል፡፡ ይህን ሁሉ ስደት በጽናት አልፌዋለሁ፣ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ፡፡
12በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሚወደው ሊኖሩ የሚፈልጉ ሁሉ ይሰደዳሉ፡፡
13ከፉ ሰዎች እና አታላዮች በክፋት እየባሱ ሌሎችንም እያሳቱና ራሳቸውም ችየሳቱ ይሄዳሉ፡፡
14አንተ ግን በተማርህበትና በምታምንበት ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደተማርከው ታውቃለህና፡፡
15ከሕፃንነትህ ጀምሮ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ስለሚገኘው መዳን ጥበብ ሊሰጡህ ስለሚችሉት ቅዱሳት መጻሕፍት አውቀሃል፡፡
16በእግዚአብሔር የተገለጡ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ለመሠረተ እምነት፣ በእምነትም ለመጽናት፣ በጽድቅም ላለው ምክር ይጠቅማሉ፣
17በመሆኑም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ የተዘጋጀ እና የታጠቀ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።