መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ንጉሡ በቤቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣
2ለነቢዩ ለናታን ንጉሡ እንደዚህ አለው፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው፡፡
3ከዚያ በኋላ ናታን ለንጉሡ፣ “እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለሆነ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው፡፡
4ነገር ግን በዚያች ሌሊት እንደዚህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ፣
5“ሂድና ለባሪያዬ ለዳዊት እንደዚህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር የሚልህ እንደዚህ ነው፣ የምኖርበትን ቤት አንተ ትሠራልኛለህን?
6የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ካወጣሁበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳን ማደሪያ ውስጥ ሆኜ እንቀሳቀስ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ ኖሬ አላውቅምና፤
7በመላው የእስራኤል ሕዝብ መካከል በተመላለስሁባቸው በሁሉም ስፈራዎች ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ከሾምኋቸው መሪዎች ለአንዱ ስንኳ፣ ‘ከዝግባ እንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?’ ብያለሁን?
8እንግዲህ አሁን ለባሪያዬ ለዳዊት እንደዚህ በለው፣ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህንን ነው፣ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ ከመስክ በጎችን ትከተል ከነበርህበት ስፍራ ወሰድሁህ፤
9በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ’፤ በምድር ላይ ስማቸው ታላቅ እንደሆነው እንደ አንዱ ለአንተ ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ፡፡
10ከእንግዲህ ወዲያ በራሳቸው መኖሪያ እንዲኖሩ እንጂ እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፣ በዚያም እተክላቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በፊት እንደሆነውም ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቁናቸውም፤
11መሳፍንትን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ባዘዝሁበት ጊዜ እንዳደረጉባቸው ከእንግዲህ ወዲህ አያደርጉባቸውም፤ ከጠላቶችህም ሁሉ አሳርፍሃለሁ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ እኔ እግዚአብሔር ቤት እንደምሠራልህ እነግርሃለሁ፡፡
12ዕድሜህ በሚጠናቀቅበት ጊዜና ከአባቶችህ ጋር በምታርፍበት ጊዜ ከአብራክህ የሚወጣ ዝርያ አስነሳልሃለሁ፣ መንግሥቱንም አጸናለሁ፡፡
13እርሱ ለእኔ ቤት ይሠራልኛል፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ፡፡
14እኔ አባት እሆነዋለሁ፣ እርሱም ልጄ ይሆናል፡፡ ኃጢአት በሚያደርግበት ጊዜ በሰዎች በትር እቀጣዋለሁ፣ የሰው ልጆች በሚገረፉበትም ግርፋት እገርፈዋለሁ፤
15ከፊትህ ካስወገድሁት ከሳኦል ላይ እንደወሰድሁ ኪዳናዊ ታማኝነቴ ከእርሱ አይርቅም፡፡
16ቤትህና መንግሥትህ በፊትህ ለዘላለም የጸና ይሆናል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል፡፡”
17ናታን ለዳዊት እንደዚህ ተናገረ፣ ይህንንም ሁሉ ነገር ነገረው፤ ጠቅላላውንም ራእይ ገለጸለት፡፡
18ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባና በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጠና እንደዚህ አለ፣ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ደረጃስ ታደርሰኝ ዘንድ ቤተሰቤስ ምንድን ነው?
19ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህ በፊትህ ታናሽ ነገር ነው፡፡ ስለ ባሪያህ ቤተሰብ እንኳን ለረጅም ጊዜ የሚሆነውን ተናገርህ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ከዚህ በኋላ የሚኖረውንም ትውልዴን አሳየኸኝ!
20እኔ ዳዊት ከዚህ በላይ ለአንተ ምን እላለሁ? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ባሪያህን አክብረኸዋል፡፡
21ስለ ቃልህ ብለህ፣ ዓላማህንም ትፈጽም ዘንድ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ለባሪያህም ገልጸህለታል፡፡
22ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ታላቅ ነህና እንደ አንተ ያለም የለም፤ በገዛ ጆሮቻችንም እንደ ሰማን ከአንተም በቀር አምላክ የለም፡፡
23አንተ እግዚአብሔር መጥተህ ለራስህ እንዳዳንከው በምድር ላይ እንዳለው እንደ ሕዝብህ ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? ይህንን ያደረግኸው ለራስህ ሕዝብን ታስነሳ ዘንድ፣ ለራስህም ስምህን ታስጠራ ዘንድና ታላቅና አስፈሪ ነገር በምድርህ ታደርግ ዘንድ ነው፡፡ ከግብፅ ከዋጀኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብንና ጣዖቶቻቸውን አባረርህ፡፡
24እስራኤልን ሕዝብህ አድርገህ ለዘላለም አጸናህ፣ አንተም፣ እግዚአብሔር ሆይ አምላክ ሆንህላቸው፡፡
25አሁንም ባሪያህንና ቤተሰቡን በሚመለከት የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም አጽናለት፤ እንደተናገርኸውም አድርግለት፡፡
26የእኔ፣ የባሪያህ የዳዊት ቤት በፊትህ በሚጸናበት ጊዜ ሕዝቦች፣ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው’ ይሉ ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፡፡
27አንተ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የእስራኤል አምላክ ለባሪያህ ቤት እንደምትሠራለት ገልጸህለታልና፤ ለዚህ ነው እኔ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት ያገኘሁት፡፡
28አሁን፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ አምላክ ነህ፣ ቃሎችህም የታመኑ ናቸው፤ ይህንን መልካም የተስፋ ቃል ለባሪያህ ገብተህለታል፡፡
29በፊትህ ለዘላለም የሚቀጥል ይሆን ዘንድ፣ እንግዲህ አሁን የባሪያህን ቤት መባረክ አንተን ደስ ያሰኝህ፡፡ አንተ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ተናግረሃልና በበረከትህ የባሪያህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሆናል፡፡”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።