መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ፡፡
2ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በኪሩቤል ላይ በዙፋኑ በተቀመጠው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት በይሁዳ ወዳለው ወደ በአል ሄዱ፡፡
3የእግዚአብሔርን ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው በኮረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፡፡ ልጆቹ ዖዛና አሒዩ አዲሱን ሠረገላ ይመሩ ነበር፡፡
4የእግዚአብሔርን ታቦት በላዩ ላይ አኑረው ሠረገላውን በኮረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ አሒዩ ከታቦቱ ፊት ለፊት ይሄድ ነበር፡፡
5ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በጥድ እንጨት በተሠሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ማለትም በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጸናጽልና በቃጭል መጫወትና ደስታቸውን መግለጽ ጀመሩ፡፡
6ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለተደናቀፉ፤ ዖዛ የእግዚአብሔርን ታቦት ለመያዝ እጁን ዘረጋ በእጁም ያዘው፡፡
7ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ በዚያም ስፈራ እግዚአብሔር ስለ ኃጢአቱ መታው፡፡ ዖዛም በዚያ በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ ሞተ፡፡
8እግዚአብሔር ዖዛን ስለመታው ዳዊት ተቆጣ፤ የዚያን ቦታም ስም ፔሬዝ ዖዛ ብሎ ጠራው፡፡ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፔሬዝ ዖዛ ተብሎ ይጠራል፡፡
9ዳዊት በዚያን ቀን እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ሊመጣ ይችላል?” ብሎ ጠየቀ፡፡
10ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከእርሱ ጋር ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈቀደም፤ በዚህ ፋንታ አቅጣጫ ለውጦ የጌት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው፡፡
11የእግዚአብሔርም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እርሱንና ቤተሰቡንም ሁሉ እግዚአብሔር ባረካቸው፡፡
12በዚህ ጊዜ፣ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የአቢዳራን ቤተሰብና ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር ባረከለት” ብለው ለዳዊት ነገሩት፡፡ ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከኦቤድ ኤዶም ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣው፡፡
13የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት እርምጃ በሄዱ ቁጥር አንድ በሬና አንድ የሰባ ጥጃ ይሠዋ ነበር፡፡
14ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ብቻ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይጨፍር ነበር፡፡
15ስለዚህ ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት እልል እያሉና ቀንደ መለከት እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘውት መጡ፡፡
16የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ እየገባ ሳለ የሳዖል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሥ ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልና ሲጨፍር አየችው፤ ከዚያ በኋላም በልቧ ናቀችው፡፡
17ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን በተዘጋጀለት በማዕከላዊ ስፍራ አኖሩት፡፡ ከዚያ በኋላም ዳዊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ፡፡
18ዳዊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ በፈጸመ ጊዜ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ባረከ፡፡
19ከዚያ በኋላ ለመላው እስራኤል፣ ለሕዝቡ ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጀራ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ፡፡ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ ወደየቤቱ ሄደ፡፡
20ከዚያ በኋላ ቤተሰቡን ለመባረክ ተመለሰ፡፡ የሳዖል ልጅ ሜልኮልም ዳዊትን ልትቀበለው መጣችና እንደዚህ አለች፣ “ራሳቸውን ከሚያራቁቱ ባለጌዎች እንደ አንዱ ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ መካከል በነበሩት ገረዶች ፊት ራሱን በማራቆቱ ምን ያህል የተከበረ ነበር!”
21ዳዊትም ለሜልኮል እንዲህ ሲል መለሰላት፣ “እኔን ከአባትሽና ከቤተሰቡ ሁሉ በላይ በመረጠኝና በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሾመኝ በእግዚአብሔር ፊት ያንን አድርጌአለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሐሴት አደርጋለሁ!
22እንዲያውም ከዚህም የበለጠ ራሴን ዝቅ አደርጋለሁ፣ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ፡፡”
23ስለዚህም የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከምትሞተችበት ጊዜ ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።