1የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፣ “እነሆ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቁራጭ ነን፤
2ሳኦል በእኛ ላይ ነግሦ በነበረበት ባለፈው ጊዜ የእስራኤልን ሠራዊት የምትመራ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፣ በእስራኤልም ላይ ገዥ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር፡፡”
3ስለዚህም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም ኬብሮን ላይ በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት፡፡
4ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረr፤ አርባ ዓመትም ገዛ፡፡
5በኬብሮን በይሁዳ ላይ ለሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ፡፡
6ንጉሡና ሰዎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች በሆኑት በኢያቡሳውያን ላይ ለመዝመት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፡፡ እነርሱም ለዳዊት፣ “በዕውሮችና በአንካሶች ልትመለስ ካልሆነ በስተቀር አንተ ወደዚህ አትገባም፤ ዳዊት እዚህ መምጣት አይችልም” አሉት፡፡
7ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን አምባ ያዘ፤ ይህችም አሁን የዳዊት ከተማ የሆነችው ነች፡፡
8በዚያን ጊዜ ዳዊት እንደዚህ አለ፣ “ኢያቡሳውያንን የሚያጠቃ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት፤ በዚያም ዳዊትን የሚጠሉትን ዕውሮችንና አንካሶችን ያገኛል፡፡” እንግዲህ ሰዎች፣ “አንካሶችና ዕውሮች ወደ ቤተ መንግሥት መግባት አይችሉም” ያሉት ከዚህ የተነሣ ነው፡፡
9በመሆኑም ዳዊት በአምባይቱ ኖረ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት፡፡ ከሸንተረሩ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ምሽግ ገነባባት፡፡
10የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ፣ ዳዊት እጅግ እየበረታ ሄደ፡፡
11በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም መልእክተኞችን፣ የዝግባ እንጨት፣ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን ወደ ዳዊት ላከ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤት ሠሩለት፡፡
12እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገለት ዳዊት አወቀ፡፡
13ኬብሮንን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ቁባቶችን አስቀመጠ ሚስቶችንም አገባ፤ ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም በኢየሩሳሌም ተወለዱለት፡፡
14በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ስም፣ ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣
15ኢያቤሔር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣
16ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባሉ ነበር፡፡
17ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ለመፈለግ በሙሉ ኃይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ግን ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ፡፡
18በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ፡፡
19ዳዊትም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ ሲል ዕርዳታ ጠየቀ፣ “ፍልስጥኤማውያንን ወጥቼ ልውጋቸውን? በእነርሱስ ላይ ድል ትሰጠኛለህ?” እግዚአብሔርም ለዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ በእርግጥ ድል እሰጥሃለሁና ውጋቸው” አለው፡፡
20ስለዚህ ዳዊት በበአልፐራሲም ወጋቸው በዚያም ድል አደረጋቸው፡፡ እርሱም፣ “የጎርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” በማለት ስሜቱን ገለጸ፡፡ ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም በአልፐራሲም ተባለ፡፡
21ፍልስጥኤማውያን ጣዖቶቻቸውን እዚያ ትተው ስለነበር ዳዊትንና ሰዎቹን ወሰዷቸው፡፡
22ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ በድጋሚ ተበታትነው ሰፈሩ፡፡
23ስለዚህ ዳዊት እንደገና ከእግዚአብሔር ዕርዳታ ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “በፊት ለፊት በኩል አትውጋቸው፤ ይልቁኑ በስተኋላቸው በኩል በመክበብ በበለሳኑ ዛፎች ፊት ለፊት ግጠማቸው፡፡
24በበለሳኑ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጉዞ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ለመምታት እግዚአብሔር ቀድሞ ወጥቶአልና በዚያን ጊዜ በኃይል አጥቃ” አለው፡፡
25ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ፍልስጥኤማውያንን ከገባዖን እስከ ጌዘር ድረስ ገደላቸው፡፡