1አበኔር በኬብሮን መሞቱን የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በሰማ ጊዜ እጆቹ ዛሉ፣ መላው እስራኤልም ተጨነቀ፡፡
2በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ የወታደር ጭፍራ መሪዎች የነበሩ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ የአንደኛው ስም በዓና ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሬካብ ይባሉ ነበር፡፡ እነርሱም ከብንያም ነገድ የብኤሮት ተወላጅ የሆነው የሬሞን ልጆች ነበሩ (ብኤሮት ከብንያም ክፍል እንደ አንዱ ትቆጠር ነበር፤
3የብኤሮት ሕዝብ ወደ ጌቴም በመሸሽ እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ) ፡፡
4የሳኦል ልጅ ዮናታን ሁለት እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው፡፡ እርሱም የሳዖልና የዮናታን ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ሞግዚቱ ይዛው ለመሸሽ አነሣችው፣ ነገር ግን ይዛው በምትሮጥበት ጊዜ የዮናታን ልጅ ወደቀና ሽባ ሆነ፡፡ ስሙም ሜምፊቦስቴ ይባል ነበር፡፡
5በዚህ ጊዜ የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ሞቃት በነበረበት በቀትሩ ሰዓት እርሱ ዕረፍት እያደረገ ሳለ ወደ ኢያቡስቴ ቤት ሄዱ፡፡
6ትጠብቅ የነበረችው ሴት ስንዴ በምታበጥርበት ጊዜ እንቅልፍ ወስዷት ነበርና ሬካብና በዓና በቀስታ አልፈዋት ገቡ፡፡
7ስለዚህ ወደ ቤት ከገቡ በኋላ በክፍሉ ተኝቶ ሳለ አጠቁት ገደሉትም፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱን ቆርጠው በመውሰድ ሌሊቱን ሁሉ በዓረባ መንገድ ተጓዙ፡፡
8የኢያቤስቴንም ራስ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት ዘንድ አምጥተው፣ “አንተን ሊገድል ይፈልግ የነበረው የጠላትህ የሳዖል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ፤ እነሆ እግዚአብሔር በዛሬው ቀን ስለ ጌታዬ ስለ ንጉሡ ሳዖልንና ዘሩን ተበቅሎአል፡፡” አሉት፡፡
9ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞን ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና ምላሽ በመስጠት እንዲህ አላቸው፣ “ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን፣
10የምሥራች ያመጣልኝ መስሎት ‘እነሆ ሳኦል ሞተ’ ብሎ የነገረኝን ሰው ይዤ ጺቅላግ ላይ ገደልሁት፤ እንግዲህ ወሬውን ላመጣው ለዚያ ሰው የሸለምሁት ይህንን ነበር፡፡
11ታዲያ በገዛ ዐልጋው ላይ ዐርፎ የተኛውን ንጹሕ ሰው ክፉ ሰዎች የገደሉት ከሆነ እንዴት ይልቅ ደሙን ከእጃችሁ አልፈልግ፣ ከዚህ ምድርስ አልደመስሳችሁ?”
12ስለዚህም ዳዊት ጎልማሶቹን አዘዘ፤ እነርሱም ገደሏቸው፤ እጅና እግራቸውንም ቆርጠው በኬብሮን ካለው ኩሬ አጠገብ ሰቀሏቸው፡፡ ነገር ግን የኢያቡስቴን ራስ ወስደው ኬብሮን በሚገኘው በአብኔር መቃብር ውስጥ ቀበሩት፡፡