1በሳዖል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ጦርነት ነበረ፡፡ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ የሳዖል ቤት ግን እየደከመ ሄደ፡፡
2በኬብሮን ለዳዊት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፡፡ የበኩር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበር፡፡
3ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ ነበር፡፡ ሦስተኛ የነበረው፣ አቤሴሎም የጌሹር ንጉሥ ከነበረው ከተልማይ ልጅ ከመዓካ የተወለደው ነበር፡፡
4አራተኛው፣ ልጁ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፣ አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣
5ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትርኃም ነበር፤ እነዚህ ወንዶች ልጆች ለዳዊት በኬብሮን የተወለዱለት ነበሩ፡፡
6የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ አበኔር በሳዖል ቤት ራሱን ጠንካራ አድርጎ ነበር፡፡
7ሳኦል የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ የተባለች ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው፡፡
8አብኔርም በዚያን ጊዜ በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለተቆጣ እንዲህ አለ፣ “እኔ ለይሁዳ የተሰጠሁ የውሻ ራስ ነኝን? አንተን ለዳዊት አሳልፌ ባለመስጠቴ እኔ ዛሬ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለወዳጆቹ ታማኝነቴን አሳይቻለሁ፤ ይህም ሆኖ ሳለ አንተ ከዚህች ሴት ጋር በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን?
9እግዚአብሔር ለዳዊት መንግሥትን ከሳዖል ቤት አውጥቶ
10ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ዙፋኑን እንደሚያጸና በመሐላ የገባለት ተስፋ እንዲፈጸም ባለደርግ እግዚአብሔር በእኔ በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግብኝ ከዚያ የባሰም ያምጣብኝ፡፡”
11ኢያቡስቴም አበኔርን ፈርቶት ስለነበረ አንዲት ቃል ስንኳ ሊመልስለት አልቻለም፡፡
12ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ይህች ምድር የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፣ እነሆ፣ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ እንዲመለሱ ለማድረግ እጄ ከአንተ ጋር እንደሆነ ትመለከታለህ” ብለው እንዲነግሩለት መልእክተኞችን ላከ፡፡
13ዳዊትም፣ “መልካም ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ነገር ግን ከአንተ የምሻው አንድ ነገር፤ ወደ እኔ በምትመጣበት ጊዜ የሳዖልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ ካልመጣህ ፊቴን ማየት እንደማትችል እንድታውቅ ነው፡፡” አለው፡፡
14ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልእክተኞች ላከበት፡፡
15ስለዚህም ኢያቡስቴ መልእክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፍልጢኤል ወሰዳት፡፡
16ባሏም እስከ ብራቂም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “አሁን፣ ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው፡፡ ስለዚህም ተመለሰ፡፡
17አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር እንደዚህ በማለት ተመካከረ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊትን በላያችሁ ለማንገሥ ሞክራችሁ ነበር፤
18እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ስለተናገረው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት፡፡”
19አበኔርም ራሱ ሄዶ ለብንያማውያን ይህንን ነገራቸው፤ ከዚያም በኋላ አበኔር እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለገውን ሁሉ በመግለጽ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ፡፡
20ከሃያ ሰዎች ጋር አበኔር በዳዊት ፊት ለመቅረብ ወደ ኬብሮን በመጡ ጊዜ ዳዊት ግብዣ አደረገላቸው፡፡
21አበኔርም ለዳዊት፣ “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉና በፈለግኸውም ሁሉ ላይ እንድትገዛ ተነሥቼ እስራኤልን ሁሉ ወደ አንተ እሰበስባለሁ” በማለት ገለጸለት፡፡ ዳዊትም አሰናበተው፤ አበኔርም በሰላም ሄደ፡፡
22ከዚያ በኋላ የዳዊትና የኢዮአብ ወታደሮች ከዘመቻ ሲመለሱ ብዙ ምርኮ ይዘው መጡ፡፡ ዳዊት አሰናብቶት ስለነበረና እርሱም በሰላም ስለሄደ አበኔር በኬብሮን ከዳዊት ጋር አልነበረም፡፡
23ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጣ ንጉሡም አሰናበተው እርሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮአብ ነገሩት፡፡
24ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ ለምን ይሄድ ዘንድ አሰናበትኸው?
25የኔር ልጅ አበኔር የመጣው አንተን ሊያታልልህ፣ ዕቅድህን ለማወቅና የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር ለማጥናት እንደሆነ አታውቅምን?”
26ኢዮአብ ከዳዊት ዘንድ በወጣ ጊዜ አበኔር ዘንድ መልእክተኞችን ላከ እነርሱም ከሴይር የውሃ ጉድጓድ አጠገብ መለሱት፡፡ ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር፡፡
27አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በቆይታ ለማነጋገር ወደ ቅጥሩ ዞር አደረገው በዚያም ሆዱን ወግቶ ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንገድ የወንድሙን የአሣሄልን ደም ተበቀለ፡፡
28ዳዊት ይህንን በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፣ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአብኔር ደም በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ንጹሕ ነን፤
29ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም አሠቃቂ የቆዳ በሽታ ያለበት፣ በምርኩዝ የሚሄድ አንካሳ፣ ወይም በሰይፍ የሚገደል ወይም ምግብ አጥቶ የሚራብ ሰው ከኢዮአብ ቤት አይታጣ፡፡”
30ስለዚህ ወንድማቸውን አሣሄልን በገባዖን በተደረገው ጦርነት ገድሎባቸው ነበርና፣ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ አበኔርን ገደሉት፡፡
31ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፣ “ልብሳችሁን ቀዳችሁ፣ ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር አስከሬን ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ንጉሥ ዳዊትም አስከሬኑን ከሚያጅበው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሄድ ነበር፡፡
32አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ጮኾ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ፡፡
33ንጉሡም በሐዘን እንጉርጉሮ ለአበኔር አለቀሰ፣ “አበኔር እንደ ተራ ሰው ሊሞት ይገባው ነበር?
34እጆችህ አልታሰሩም፤ እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤ ሰዎች በግፈኞች ፊት እንደሚወድቁ አንተም እንደዚሀ ወደቅህ፡፡” ሕዝቡም ሁሉ እንደገና አለቀሱለት፡፡
35ገና ቀን ሳለ ምግብ እንዲበላ ለማድረግ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ዳዊት መጡ፤ ዳዊት ግን፣ “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ማንኛውንም ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ፡፡
36ሕዝቡም ሁሉ የዳዊትን ሐዘን ተመለከቱ፤ ንጉሡ የሚያደርገው ሁሉ በእርግጥ ደስ ያሰኛቸው ስለነበረ፣ በዚህም ደስ አላቸው፡፡
37ስለዚህ የኔር ልጅ አበኔር ይገደል ዘንድ የንጉሡ ፍላጎት እንዳልነበረ ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ በዚያን ዕለት ዐወቁ፡፡
38ንጉሡ ለአገልጋዮቹ እንደዚህ አላቸው፣ “በዛሬይቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን?
39ምንም እንኳን የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም እኔ ደካማ ነኝ፤ እነዚህ የጽሩይ ልጆች እጅግ ጨካኞች ሆነውብኛል፡፡ እንደ ክፋቱ በመቅጣት እግዚአብሔር ለክፉ አድራጊው እንደ እጁ ሥራ መጠን ይክፈለው፡፡”