መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ ዳዊት፤ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፣ እግዚአብሔርም፣ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት፡፡
2ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ሄደ፡፡ ጠየቀ፡፡ እግዚአብሔርም፣ “ውጣ” ብሎ መለሰለት፡፡ ዳዊትም፣ “ወደ የትኛው ከተማ ልሂድ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
3ዳዊት ቤተ ሰቦቻቸውን ይዘው የመጡትን ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን ይዟቸው መጣ፡፡
4ከዚያ በኋላም የይሁዳ ሰዎች ወደ ኬብሮን መጥተው ዳዊትን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት፡፡ የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ሳኦልን እንደቀበሩት ለዳዊት ነገሩት፡፡
5ስለዚህ ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞች ልኮ እንደዚህ አላቸው፣ “ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር ይህንን በጎነት ስላሳያችሁ በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ናችሁ፡፡
6አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይገለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፡፡
7እንግዲህ እጆቻችሁ ይጠንክሩ፣ በርቱ፤ ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና፣ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል፡፡”
8የሳኦል ሠራዊት አዛዥ፣ የኔር ልጅ አብኔር ግን የሳዖልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፤
9ኢያቡስቴንም በገለዓድ፣ በአሴር፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው፡፡
10የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፣ ሁለት ዓመትም ገዛ፡፡ የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ፡፡
11ዳዊት በኬብሮን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ የሆነበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበር፡፡
12የኔር ልጅ አብኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ አገልጋዮች ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ፡፡
13እነርሱንም የጽሩይ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች በገባዖን ኩሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ በዚያም አንዱ ወገን በኩሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኩሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ፡፡
14አበኔርም ለኢዮአብ፣ “ጎልማሶች ይነሡና እርስ በርሳቸው ይጋጠሙ” አለው፡፡ ኢዮአብም፣ “እሺ፣ ይነሡ” አለ፡፡
15ከዚያ በኋላም ከብንያምና ከሳኦል ልጅ ከኢየቡስቴ ወገን አሥራ ሁለት፣ የዳዊት አገልጋዮች ከሆኑት ደግሞ አሥራ ሁለት ጎልማሶች ተነሥተው በአንድነት ተሰባሰቡ፡፡
16እያንደንዱም ሰው የባላጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጎኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ፡፡ ስለዚህ በገባዖን ያለው ያ ስፍራ በዕብራይስጥ ‘ሐልቃት አዙሪም’ ወይም ‘የሰይፍ ምድር’ ተባለ፡፡
17በዚያን ዕለት ጦርነቱ እጅግ ከባድ ነበር፣ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት አገልጋዮች ድል ሆኑ፡፡
18ሦስቱ የጽሩይ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ፡፡ አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበር፤
19አሣሄል በየትኛውም አቅጣጫ ዞር ሳይል አበኔርን በቅርበት ተከታተለው፡፡
20አበኔርም ወደ ኋላው ዞር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል አንተ ነህን?” አለው፡፡ እርሱም፣ “እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት፡፡
21አበኔርም፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጎልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው፤ አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር።
22እንደገናም አቤኔር “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው።
23አሣሄል ግን ዘወር ለማለት እምቢ አለ፤ ስለዚህ አብኔር በጦሩ ጫፍ አከላቱን ወጋው፤ ጦሩም በአካሉ በሌላው ወገን ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም ወደቀ፣ በዚያ ስፍራም ሞተ፡፡ ስለሆነም አሣሄል ወደ ወደቀበት ይመጣ የነበረ እያንዳንዱ ሰው በዚያ ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር፡፡
24ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን አሳደዱት፤ ፀሐይም በምትጠልቅበት ጊዜ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደረሱ፡፡
25የብንያም ሰዎችም ከአበኔር በስተኋላ ተሰብስበው በተራራው ጫፍ ላይ ቆሙ፡፡
26ከዚያ በኋላም አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ሰይፍ ለዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ በመጨረሻ መራራ መሆኑን አንተ አታውቅምን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደድ እንዲያቆሙ የማትነግራቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው፡፡
27ኢዮአብም ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ወታደሮቼ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ባሳደዱ ነበር” ብሎ መለሰ፡፡
28ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ሰዎቹም ሁሉ ቆሙ፤ ከዚያ በኋላም እስራኤልን አላሳደዱም፣ መዋጋታቸውንም አልቀጠሉም፡፡
29አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ በዓረባ በኩል አለፉ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረው በማግሥቱ ጥዋት ሲጓዙ ቆይተው ከዚያ በኋላ ወደ መሃናይም ደረሱ፡፡
30ኢዮአብም አበኔር ከማሳደድ ተመለሰ፡፡ አሣሄልና ከዳዊት ወታደሮች አሥራ ዘጠኙ የጎደሉባቸውን ሰዎቹን ሁሉ ሰበሰበ፡፡
31የዳዊት ሰዎች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ሥልሳ ብንያማውያንን ገድለዋል፡፡
32ከዚያ በኋላም አሣሄልን ከወደቀበት አንሥተው ቤተ ልሔም በነበረው በአባቱ መቃብር ቀበሩት፡፡ ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሠው ኬብሮን ሲደርሱ ሌሊቱ ነጋላቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።