መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 23

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እነዚህ ተወዳጁ የእስራኤል ዘማሪ፣ በያዕቆብ አምላክ የተቀባው፣ እጅግ የተከበረው፣ የእሴይ ልጅ የዳዊት የመጨረሻ ቃሎች ናቸው፡፡
2የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፣ ቃሉም በምላሴ ላይ ነበረ፡፡
3የእስራኤል አምላክ ተናገረ፣ የእስራኤልም ዐለት እንደዚህ አለኝ፣ “ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣ በፈሪሀ-እግዚአብሔር የሚያስተዳድር፣
4እርሱ ከዝናብ በኋላ ብሩሕ በሆነው የፀሐይ ብርሃን ከምድር እንደሚበቅል ለምለም ሣር፣ ደመና የሌለባት ፀሐይ ጥዋት ስትወጣ እንደሚፈነጠቅ የማለዳ ብርሃን ነው፡፡
5በእርግጥ የእኔ ቤተሰብ በእግዚአብሔር ፊት እንደዚህ አይደለምን? ከእኔስ ጋር ሥርዓት ያለውና በሁሉም መንገድ እርግጠኛ የሆነ የዘላለም ቃል ኪዳን አልገባምን? ድነቴን ከፍ ከፍ አድርጎ፣ ማንኛውንም ፍላጎቴን አይፈጽምልኝምን?
6ነገር ግን በእጅ ሊሰበሰቡ ስለማይችሉ ሁላቸውም እንደሚጣሉ እሾሆች ከንቱዎች ናቸው፡፡
7እነርሱን የሚነካ የብረት መሣሪያ መጠቀም ወይም የጦር ዘንግ መያዝ ስላለበት ባሉበት መቃጠል ይገባቸዋል፡፡”
8የዳዊት ምርጥ ወታደሮች ስም የሚከተለው ነው፡- የታህክሞን ሰው ዮሴብ የሦስቱ አለቆች አለቃና በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰዎችን የገደለ ነው፡፡
9ከእርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፣ እርሱም ከሶስቱ ኃያላን ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ እርሱም ጦርነት ለመግጠም የተሰባሰቡ ፍልስጥኤማውያን በተገዳደሩ ጊዜና የእስራኤልም ሰዎች በፈገፈጉ ጊዜ በዚያ ነበር፡፡
10ኤልኤዘር እስኪዝልና እጁ ከሰይፉ ጋር ተጣብቆ እስኪቀር ድረስ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ቆሞ ተዋጋ፡፡ የዚያን ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድል አስገኘ፡፡ ከኤልኤዘር በኋላ ሠራዊቱ የተመለሰው አስከሬኖቹን ለመግፈፍ ብቻ ነበር፡፡
11ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፡፡ ፍልስጥኤማውያኑ የምስር እርሻ በነበረበት ተሰብስበው ሳሉ ሠራዊቱ ከ እነርሱ ሸሸ፡፡
12ሣማ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ተቋቋማቸው ፍልስጥኤማዊውንም ገደለው እግዚአብሔርም ታላቅ ድል ሰጣቸው፡፡
13ከሰላሳዎቹ ወታደሮች ሶስቱ በመከር ጊዜ ወደ አዶላም ዋሻ ወደ ዳዊት ዘንድ ሄዱ፡፡ የፍልስጥኤም ሠራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍረው ነበር፡፡
14በዚያን ጊዜ ዳዊት በአንድ ዋሻ በምሽጉ ውስጥ ሲሆን ፍልስጥኤማውያን ግን በቤተልሔም ተደራጅተው ነበር፡፡
15ዳዊትም ውሃ ተጠምቶ፣ “በበሩ አጠገብ ካለችው ጉድጓድ የምጠጣውን ውሃ ምነው አንድ ሰው በሰጠኝ!” አለ፡፡
16ስለዚህ እነዚህ ሶስቱ ኃያላን ፍልስጥኤማውያንን ጥሰው አልፈው በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ቀዱ፡፡ ውሃውንም ይዘው ለዳዊት አመጡለት፣ እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈቀደ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው፡፡
17ከዚያ በኋላም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህንን እጠጣው ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉ ሰዎችን ደም ልጠጣ ይገባኛልን?” ከዚህም የተነሣ ሊጠጣው አልፈቀደም፡፡ ሶስቱ ኃያላን ያደረጓቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡
18የኢዮአብ ወንድምና የጽሩያ ልጅ አቢሳ የሶስቱ አለቃ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከሶስት መቶዎቹ ጋር በጦሩ ተዋግቶ ገደላቸው፡፡ ከሶስቱ ወታደሮች ጋር በተያያዘ ብዙውን ጊዜ ስሙ ይጠቀሳል፡፡
19እርሱ ከእነርሱም ይልቅ ዝነኛ አልነበረምን? እርሱ የሶስቱ አለቃ ሆኖ ተሾመ፡፡ ይሁን እንጂ የእርሱም ዝና ከሶስቱ እጅግ ዝነኛ ከነበሩት ወታደሮች ጋር የሚስተካከል አልነበረም፡፡
20የቀብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ታላቅ ጀብዱ የሠራ ጠንካራ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም ሁለቱን የአርኤል ልጆች ገደለ፡፡ በረዶ በጣለበትም ወቅት በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሎአል፡፡
21ደግሞም አንድ ግዙፍ ግብፃዊም ገድሎአል፡፡ ግብፃዊው በእጁ ጦር የያዘ ቢሆንም በናያስ በትር ብቻ ይዞ ገጠመው፡፡ ጦሩን ከግብፃዊው እጅ ቀምቶ በራሱ ጦር ገደለው፡፡
22በናያስ እነዚህን ጀብዱዎች ፈጸመ ከሶስቱም ኃያላን ጋርም ስሙ የተጠራ ሆነ፡፡
23በአጠቃላይ ከነበሩት ሰላሳ ወታደሮች ይልቅ ከፍ ያለ ግምት የተሰጠው ነበረ፣ ሆኖም የሶስቱ እጅግ ምርጥ ወታደሮችን ያህል ታላቅ ግምት የተሰጠው አልነበረም፡፡ ሆኖም ዳዊት የክቡር ዘበኞቹ አለቃ አደረገው፡፡
24ሰላሳዎቹ የሚከተሉትን ያካተተ ነበር፣ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣ የቤተልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣
25አሮዳዊው ሣማ፣ አሮዳዊው ኤሊቃ፣
26ፈሊጣዊው ሴሌስ፣ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ፣
27ዓኖቶታዊው አቢዔዜር፣ ኩስታዊው ምቡናይ ፣
28አሆሃዊው ጸልሞን፣ ነጦፋዊው ማህራይ፣
29የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፣ ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣
30ጲርዓቶናዊው በናያስ፣ የገዓስ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፣
31ዓረባዊው አቢዔልቦን፣ በርሑማዊው ዓዝሞት፣
32ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣ የአሳን ልጆች፤ ዮናታን የተባለው፣
33የአሮዳዊው የሣማ ልጅ፣ የአሮዳዊው የሻራር ልጅ አሒአም፣
34የማዕካታዊው የአሐሰባይ ልጅ ኤልፋላት፣ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊኦም፣
35ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፣ አርባዊው ፈዓራይ፣
36የሱባ ሰው የሆነው የናታን ልጅ ይግዓል፣
37አሞናዊው ጻሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጦር መሣሪያ ያዥ የነበረው ብኤሮታዊው ነሃራይ፣
38ይትራዊው ዔራስ ፣ ይትራዊው ጋሬብ፣
39እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮ፤ በጠቅላላው ሠላሳ ሰባት ነበሩ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።