1እንደገናም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቆጣ፤ ዳዊትንም በእነርሱ ላይ በማስነሳት፣ “ሂድ እስራኤልንና ይሁዳን ቁጠር” አለው፡፡
2ንጉሡ አብሮት ለነበረው ለኢዮአብ፣ “ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወደ እስራኤል ነገዶች ሁሉ ሂዱ፣ ለጦርነት ብቁ የሆኑትንም ጠቅላላ ብዛት ማወቅ እችል ዘንድ ሕዝቡን ሁሉ ቁጠሩ፡፡” አለው፡፡
3ኢዮአብም ለንጉሡ፣ “እግዚአብሔር አምላክህ የሕዝቡ ቁጥር መቶ እጥፍ ያብዛ፣ የጌታዬ የንጉሡ ዓይንም ይህንን ለማየት ያብቃው፡፡ ነገር ግን ጌታዬ ይህንን ለማድረግ ለምን ፈለገ?”
4ይሁን እንጂ የንጉሡ ቃል የኢዮአብንና የሠራዊት አለቆችን ቃል የሚሽር የመጨረሻ ቃል ነበር፡፡ ስለዚህ የእስራኤልን ሕዝብ ይቆጥሩ ዘንድ ኢዮአብና የሠራዊቱ አለቆች ከንጉሡ ፊት ወጡ፡፡
5ዮርዳኖስን ተሻገሩና ከከተማው በስተደቡብ በሸለቆው ዘንድ ባለው በአሮዔር አጠገብ ሠፈሩ፡፡ ከዚያም በጋድ በኩል አድርገው ወደ ኢያዜር ተጓዙ፡፡
6ወደ ገለዓድና ወደ ተባሶን አደሰይ፣ ቀጥሎም ወደ ዳንየዓን ከዚያም ዞረው ወደ ሲዶና ሄዱ፡፡
7ወደ ጢሮስ ምሽግና ወደ ኤዊያውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች ደረሱ፡፡ ከዚያም በይሁዳ ቤርሳቤህ ወዳለችው ወደ ኔጌቭ ወጡ፡፡
8በመላው ምድሪቱ ከተዘዋወሩ በኋላ ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀናት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡
9ከዚያም ኢዮአብ ለንጉሡ የተዋጊ ወንዶችን ጠቅላላ ቁጥር ዘገባ አቀረበ፡፡ በእስራኤል ሰይፍን መምዘዝ የሚችሉ ስምንት መቶ ሺህ ጀግኖች ሲኖሩ በይሁዳ ደግሞ አምስት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፡፡
10ሰዎቹን ከቆጠረ በኋላ ዳዊት በልቡ ተጨነቀ፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር፣ “ይህንን በማድረጌ ታላቅ ኃጢአት ሠርቻለሁ፡፡ የሠራሁት እጅግ የስንፍና ሥራ ነውና፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ የባሪያህ በደል አስወግድ፡፡”
11ዳዊት ጠዋት ከመኝታው ሲነሣ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዳዊት ባለ ራእይ ወደ ነቢዩ ጋድ እንዲህ ሲል መጣ፣
12“ሂድና ለዳዊት፣ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህንን ነው፣ ሶስት ምርጫ እሰጥሃለሁ፣ አንዱን ምረጥ’”
13ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ሄደና፣ “የሦስት ዓመት ረሃብ ወደ ምድርህ ይምጣን? ወይስ እነርሱ እያሳደዱህ ከጠላቶችህ ለሶስት ወራት ብትሸሽ ይሻልሃል? ወይስ በአገርህ የሶስት ቀን ቸነፈር ይምጣብህ? ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አሁን ወስን” አለው፡፡
14ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረታዊ አደራረጉ እጅግ ታላቅ ስለሆነ በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ እንጂ በሰው እጅ አንውደቅ” አለው፡፡
15ስለዚህ እግዚአብሔር ህከጥዋት እስከ ተወሰነ ጊዜ ቸነፈሩን በእስራኤል ላይ ላከ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህም ሰባ ሺህ ሰዎች ሞቱ፡፡
16መልአኩ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን በዘረጋ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ስለደረሰው ጉዳት ተፀፀቶ ሕዝቡን እያጠፋ የነበረውን መልአክ፣ “ይበቃል፣ እጅህን ሰብስብ” አለው፡፡ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር፡፡
17ሕዝቡን እየቀሠፈ የነበረውን መልአክ ባየ ጊዜ ዳዊት ለእግዚአብሔር፣ “ኃጢአት ሠርቻለሁ፣ የማይገባም ነገር አድርጌአለሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህ በጎች ምን ያደረጉት ነገር አለ? እባክህን የአንተ እጅ እኔንና የአባቴን ቤተሰብ ይቅጣ፡፡” ብሎ ለእግዚአብሔር ተናገረ፡፡
18ከዚያ በኋላ ጋድ በዚያን ቀን ወደ ዳዊት መጣና፣ “ውጣና በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ” አለው፡፡
19ስለዚህ ዳዊት ጋድ እንደ ነገረውና እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወጣ፡፡
20ኦርና ሲመለከት ንጉሡና አገልጋዮቹ ሲደርሱ አየ፡፡ ስለዚህ ኦርና ወጣ ብሎ በንጉሡ ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፡፡
21ከዚያ በኋላም ኦርና፣ “ጌታዬ ንጉሡ ወደ ባሪያው ዘንድ ለምን መጣ?” ዳዊትም መለሰ፣ “ቸነፈሩ ከሕዝቡ ይወገድ ዘንድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ የምሠራበትን የአንተን ዐውድማ እገዛ ዘንድ ነው፡፡”
22ኦርናም ለዳዊት፣ “ጌታዬ ንጉሡ የራስህ አድርገህ ውሰደው፡፡ በፊትህ ደስ ያሰኘህንም አድርግበት፡፡ እነሆ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎች፣ ለማገዶም የሚሆን የመውቂያ ዕቃና ቀንበር በዚህ አለ፡፡
23ይህንን ሁሉ ንጉሤ ሆይ፣ እኔ ኦርና ለአንተ እሰጣለሁ” አለና ከዚያ በኋላ፣ “እግዚአብሔር አምላክህ ይቀበልህ” አለው፡፡
24ንጉሡም ለኦርና፣ “አይሆንም፣ ይህንን በዋጋ መግዛት ይኖርብኛል፡፡ ምንም ነገር ያላወጣሁበትን አንድም ነገር ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” አለው፡፡ ስለዚህ ዳዊት ዐውድማውንና በሬዎቹን በሃምሳ የብር ሰቅል ገዛ፡፡
25ዳዊት በዚያ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራና የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ምድሪቱ ተለመነው፣ በእስራኤል የነበረውም ቸነፈር ቆመ፡፡