1እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳዖል እጅ በታደገው ጊዜ፣ ዳዊት በዚህ መዝሙር ያሉትን የቅኔ ቃላት ለእግዚአብሔር ዘመረ፡፡
2እንዲህም እያለ ጸለየ፣ “እግዚአብሔር ዐለቴ፣ አምባዬና ታዳጊዬ ነው፡፡
3እግዚአብሔር የምጠጋበት ዐለቴ፣ ጋሻዬና የድነቴ ቀንድ ነው፡፡ እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊዬና ከግፍ የሚያድነኝ ነው፡፡
4ሊመሰገን የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ፡፡
5የሞት ማዕበል ከበበኝ፤ የከንቱነት ጎርፍም አጥለቀለቀኝ፡፡
6የሲዖል ገመድ ተጠመጠመብኝ፣ የሞትም ወጥመድ አጥምዶ ያዘኝ፡፡
7በጨነቀኝ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፣ አምላኬን ጠራሁት፣ ከመቅደሱ ድምፄን ሰማኝ፤ ለረድኤት ያደረግሁት ጥሪም ወደ ጆሮው ደረሰ፡፡
8በዚያን ጊዜ ምድር ተንቀጠቀጠች እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበረና የሰማይ መሠረቶች ተናወጡ ተንቀጠቀጡም፡፡
9ከአፍንጫው ጢስ፣ ከአፉም ፍሙን የሚያግል የሚንበለበል እሳት፡፡
10ሰማይን ከፍቶ ወረደ፣ ድቅድቅ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበር፡፡
11በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፣ በንፋስም ክንፍ ተቀምጦ ሲበር ታየ፡፡
12በሰማይ ላይ ያሉ ከባድ የዝናብ ደመናዎችን በማሰባሰብ ጨለማን እንደ ድንኳን እንዲከበው አደረገ፡፡
13በፊቱ ካለው ነጎድጓድ የእሳት ፍም ወረደ፡፡
14እግዚአብሔር ከሰማይ አንጎደጎደ፣ የልዑልም ድምፅ አስተጋባ፡፡
15ፍላፃውን ወረወረ ጠላቶቹንም በተነ - መብረቁ እንዲበርቅ አደረገ፣ በታተናቸውም፡፡
16በዚያን ጊዜ የውሃ መውረጃዎች ታዩ፣ እግዚአብሔር ባስተጋባው የክተት ድምፅ፣ ከአፍንጫው በሚወጣ የእስትንፋስ ግፊት የምድር መሠረቶች ተጋለጡ፡፡
17ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፣ እየተንዶለዶለ ካለውም ውሃ አወጣኝ፡፡
18ብርቱ ከሆነው ጠላቴ፣ ከሚጠሉኝም ታደገኝ፣ በእኔ ላይ እጅግ በርትተውብኝ ነበርና፡፡
19በጭንቀቴ ጊዜ መጡብኝ፣ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ፡፡
20እርሱም ሰፋ ወዳለ ስፍራ አወጣኝ፡፡ በእኔ ደስ ተሰኝቶ ነበርና አዳነኝ፡፡
21እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን ብድራትን ከፍሎኛል፣ እንደ እጄም ንጽሕና መጠን ወደ ስፍራዬ መልሶኛል፡፡
22የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፣ ከአምላኬም ዞር በማለት ክፋትን አላደረግሁም፡፡
23የጽድቅ ሥርዓቱ በፊቴ ናቸውና፣ ከድንጋጌም ፈቀቅ አላልሁም፡፡
24ቅንነቴን በፊቱ ጠብቄ ነበርና፣ ራሴንም ከኃጢአት አርቄ ነበር፡፡
25ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ ጽድቅ ደረጃዬ፣ በፊቱ ካለኝ የንፅሕና አቋሜ መልሶኛል፡፡
26ታማኝ ለሆነው ታማኝነትህን ታሳያለህ፣ ነቀፋ ለሌለበትም ሰው ነቀፋ የሌለብህ መሆንህን ታሳያለህ፡፡
27ከንጹሖች ጋር ንጹሕ መሆንህን ስታሳይ ለተጣመሙት ግን ጠማማ ነህ፡፡
28የተጎሳቆሉትን ታድናለህ፣ ዐይኖችህ ግን በትዕቢተኞች ላይ ነው፣ ታዋርዳቸውማለህ፡፡
29እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ መብራቴ ነህና፣ እግዚአብሔር ጨለማዬን ያበራል፡፡
30በአንተ መሰናክሉን ጥሼ አልፋለሁ፣ በአምላኬ ቅጥሩን እዘላለሁ፡፡
31የእግዚአብሔር መንገድማ ፍጹም ነው፣ የእግዚአብሔር ቃል ንፁሕ ነው፡፡ ወደ እርሱ ለሚጠጋ ለማንኛውም ሰው ጋሻ ነው፡፡
32ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው?
33እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነው፣ ነቀፋ የሌለበትንም ሰው በመንገዱ ይመራዋል፡፡
34እንደ ዋላ እግሮች እግሮቼን ፈጣን ያደርጋቸዋል፣ በተራራም ላይ ያቆመኛል፡፡
35እጆቼን ለውጊያ፣ ክንዴንም የናስ ቀስት ለመለጠጥ ያሠለጥናቸዋል፡፡
36የድነትን ጋሻ ሰጥተኸኛል፣ ሞገስህም ታላቅ አድርጎኛል፡፡
37በእግሮቼ ሥር ያለውን ስፍራ ሰፊ አድርገህልኛል፣ ስለዚህ እግሮቼ አልተንሸራተቱም፡፡
38ጠላቶቼን አሳደድኋቸው፣ አጠፋኋቸውም፡፡ እስካጠፋቸውም ድረስ አልተመለስሁም፡፡
39ፈጽሜ አጠፋኋቸው፣ አደቀቅኋቸውም፣ ተመልሰው መነሣት አይችሉም፡፡ በእግሬ ሥር ወድቀዋል፡፡
40እንደ ጦር መታጠቂያ ኃይልን በእኔ ላይ አደረግህ፣ በላዬ ላይ የተነሡትንም ከእኔ በታች አደረግኸቸው፡፡
41የጠላቶቼን ማጅራት ሰጠኸኝ፣ የሚጠሉኝንም አፈራረስኳቸው፡፡
42ዕርዳታ ለማግኘት ተጣሩ ነገር ግን ማንም አላዳነቸውም፣ ወደ እግዚአብሔር ተጣሩ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም፡፡
43እንደ አቧራ መሬት ላይ ፈጨኋቸው፣ በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃም ረገጥኋቸው፡፡
44ከራሴ ሕዝብ ክርክር አድነኸኛል፣ የሕዝቦችም ራስ አድርገህ አጽንተኸኛል፣ የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል፡፡
45ባዕድ ሕዝቦች ለእኔ ለመስገድ ተገደዱ፣ ስለ እኔ እንደሰሙ ወዲያውኑ ታዘዙኝ፡፡
46ባዕዳን ከምሽጋቸው እየተንቀጠቀጡ ወጡ፡፡
47እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐለቴ የተመሰገነ ይሁን፣ የድነቴ ዐለት እግዚአብሔር ከፍ ይበል፡፡
48በቀልን የሚበቀልልኝ፣ ሕዝብንም ከእኔ ሥር የሚያደርግልኝ አምላክ ይሄ ነው፡፡
49ከጠላቶቼ ነፃ ያወጣኛል፡፡ እንዲያውም በእኔ ላይ ከተነሡት በላይ አውጥተኸኛል፡፡ ከግፍኞች ታድገኸኛል፡፡
50ስለዚህ እግዚብሔር ሆይ፣ በሕዝቦች መካከል ለአንተ ምስጋና አቀርባለሁ፣ ለስምህም ምስጋና መዝሙር እዘምራለሁ፡፡
51እግዚአብሔር ለንጉሡ ታላቅ ድልን ይሰጠዋል፣ ኪዳናዊ ታማኝነቱን እርሱ ለቀባው፣ ለዳዊትና ለዘሮቹ ለዘላለም ያሳየዋል፡፡”