መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሳዖል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት በአማሌቃውያን ላይ ጥቃት ከማድረስ በመመለስ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቆየ፡፡
2በሦስተኛው ቀን የተቀዳደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ፡፡ ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም ወደ መሬት ለጥ ብሎ ሰገደለት፡፡
3ዳዊትም “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር አምልጬ የመጣሁ ነኝ” ሲል መለሰ፡፡
4ዳዊትም፣ “እስቲ የሆነውን ሁሉ ንገረኝ” አለው፡፡ እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነት ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል ደግሞም ሞተዋል፤ ሳዖልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ፡፡
5ዳዊትም ለወጣቱ፤ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
6ወጣቱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት፤
7ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም ‘እነሆኝ አለሁ’ አልኩት፡፡
8እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፡፡ አኔም፣ ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት፡፡
9እርሱም አለኝ ‘እኔ በታላቅ ስቃይ ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ፡፡
10ስለሆነም፣ ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፤ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፣ ለጌታዬ አምጥቻለሁ፡፡” አለው፡፡
11ከዚያም ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ፡፡
12የወደቁት በሰይፍ ነበርና ለሳኦል ለልጁ ለዮናታንና ለእግዚአብሔር ሕዝብ አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾ፡፡
13ዳዊትም ወጣቱን ሰውዬ፣ “የየት አገር ሰው ነህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም፣ “በአገሪቱ ውስጥ በመጻተኛነት የሚኖር አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ፡፡
14ዳዊትም፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ንጉሥ በገዛ እጅህ ስትገድል ለምን አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው፡፡
15ዳዊትም ከጎልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “ግደለው” አለው፤ ጎልማሳው ሰው ሄዶ መታው፣ አማሌቃዊውም ሞተ፡፡
16ከዚያም ዳዊት ለሞተው አማሌቃዊ፣ “‘እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል አፍህ መስክሮብሃልና ደምህ በራስህ ላይ ነው” አለው፡፡
17ከዚያም ዳዊት ለሳዖልና ለልጁ ለዮናታን የሚከተለውን የሐዘን እንጉርጉሮ አንጎራጎረ፡፡
18እንዲሁም የቀስት እንጉርጉሮ የተባለውን ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ ይህም በያሸር መጽሐፍ ተጽፎአል፡፡
19“እስራኤል ሆይ፣ ክብርህ ሞቶአል፣ በተራሮችህ ላይ ተገድሎአል! ኃያላኑ እንዴት ወደቁ!
20የፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንዳይደሰቱ፣ ያልተገረዙት ሴት ልጆች ፌሽታ እንዳያደርጉ ይህን በጌት አትናገሩ፣ በአስቆሎናም መንገዶች አታውጁት፡፡
21እናንት የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ ጠል አያረስርሳችሁ፣ ዝናብም አይውረድባችሁ፤ የቁርባን እህል የሚያበቅሉም እርሻዎች በዚያ አይኑሩ፤ በዚያ የኃያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፣ የሳዖል ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም፡፡
22ከሞቱት ሰዎች ደም፣ ከኃያላኑም ገላ የዮናታን ቀስት ተመልሶ አልመጣም፤ የሳዖልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም፡፡
23ሳዖልና ዮናታን በሕይወት እያሉ የሚዋደዱና ግርማ ያላቸው ነበሩ፤ ሲሞቱም አልተለያዩም፤ከንስርም ይልቅ ፈጣኖች ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ፡፡
24እናንተ የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ፤ ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ ፤ ልብሶቻችሁንም በወርቀ-ዘቦ ላስጌጠላችሁ ለሳዖል አልቅሱለት፡፡
25ኃያላን እንዴት እንዲህ በጦርነት መካከል ወደቁ! ዮናታን ከፍ ባሉ ስፍራዎቻችሁ ላይ ሞቶአል፡፡
26ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤ አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበር፤ ከሴት ፍቅርም የላቀ ነበር፡፡
27ኃያላን እንዴት ወደቁ፤ የጦር መሣሪዎቹስ እንዴት ከንቱ ሆኑ!”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።