መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 19

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1“እነሆ፣ ንጉሡ ለልጁ ለአቤሴሎም እያለቀሰ ነው” ተብሎ ለኢዮአብ ተነገረው፡፡
2“ንጉሡ ለልጁ እያለቀሰ ነው” የሚለውን ሠራዊቱ በዚያን ቀን ሰምቶ ስለነበረ፣ የዚያን ቀኑ ድል ለሠራዊቱ ወደ ኃዘን ቀንነት ተለወጠ፡፡
3ከጦርነት ሸሽተው የሚመጡ በኀፍረት ሹልክ ብለው እንደሚገቡ በዚያን ቀን ወታደሮቹ ሹልክ ብለው ወደ ከተማ ይገቡ ነበር፡፡
4ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖና ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፣ አቤሴሎም፣ ልጄ፣ ልጄ!” እያለ አለቀሰ፡፡
5ከዚያም ኢዮአብ ወደ ቤት ወደ ንጉሡ ዘንድ ገብቶ፣ “የሚወዱህን ትጠላለህና የሚጠሉህንም ትወዳለህና ዛሬ ሕይወትህን፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሕይወት፣ የሚስቶችህን ሕይወት እንዲሁም የቁባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን የወታደሮችህን ሁሉ ፊት አሳፍረሃል፡፡
6የሚጠሉህን ትወዳለህ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችና ወታደሮች ለአንተ ምንም እንዳይደሉ ዛሬ አሳይተሃልና፡፡ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት በኖረና እኛ ሁላችንም ብንሞት፣ ያ ደስ ያሰኝህ እንደነበረ አምናለሁ፡፡
7ስለዚህ አሁንም ተነሥተህ ውጣና ለወታደሮችህ በትሕትና ተናገራቸው፣ ባትሄድ ግን፣ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ በዛሬው ሌሊት አንድም ሰው ከአንተ ጋር አይቀርም፡፡ ይሄ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ከደረሰብህ መከራ ሁሉ የከፋ ይሆንብሃል፡፡”
8ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በከተማይቱ በር አጠገብ ተቀመጠ፣ ለሰዎችም ሁሉ፣ “እነሆ፣ ንጉሡ በበሩ ተቀምጦአል” ተብሎ ተነገራቸው፡፡ ከዚያ በኋላም ሰዎች ሁሉ በንጉሡ ፊት መጡ፡፡ በዚህን ጊዜ በእስራኤል ሰው ሁሉ ወደየቤቱ ሸሽቶ ነበር፡፡
9በመላው እስራኤል በየነገዱ ያሉ ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው፣ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አስጥሎናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁን ደግሞ ከአቤሴሎም ሸሽቶ ከአገር ወጥቷል፡፡
10በላያችን ላይ የቀባነውም አቤሴሎም በጦርነቱ ተገድሏል፡፡ ስለዚህ ንጉሡን መልሰን ስለማምጣት ለምን አንነጋገርም?” እያሉ ይነጋገሩ ነበር፡፡
11ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር ልኮ፣ “ለይሁዳ ሽማግሌዎች፣ ‘ወደ ቤተ መንግሥቱ ይመልሰው ዘንድ የመላው የእስራኤል ልብ ለንጉሡ ድጋፍ የሚሰጥ ነውና፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እናንተ የመጨረሻዎቹ የምትሆኑት ለምንድን ነው?
12እናንተ የሥጋዬ ቁራጭ የአጥንቴ ፍላጭ ናችሁ፡፡ ታዲያ፣ ንጉሡን ለመመለስ እናንተ የመጨረሻዎቹ የሆናችሁት ለምንድን ነው?’
13ለአሜስያም፣ ‘አንተስ የሥጋዬ ቁራጭ የአጥንቴ ፍላጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ ባለደርግህ እግዚአብሔር ይህንን ያድርግብኝ፣ ከዚህም የባሰ ይጨምርብኝ’” በሉ ብሎ መልእክት ላከ፡፡
14“አንተና ሰዎችህ ሁሉ ተመለሱ” ብለው ወደ ንጉሡ መልእከት እስኪልኩ ድረስ የአንድ ሰው ልብ እንደነበራቸው ያህል የይሁዳን ሁሉ ልብ ማረከ፡፡
15ስለዚህ ንጉሡ ተመልሶ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ የይሁዳም ሰዎች ዮርዳኖስን ሲሻገር ለማጀብ፣ ንጉሡን ለመገናኘት ወደ ጌልጌላ መጡ፡፡”
16ከብራቂም የሆነው የጌራ ልጅ ሳሚ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ከይሁዳ ሰዎች ጋር ፈጥኖ ወረደ፡፡
17ከእርሱ ጋር ከብንያም አንድ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ ደግሞም ከሲባ ከሳዖል አገልጋይ ጋር አሥራ አምስት ልጆቹና ሃያ አገልጋዮቹ ነበሩ፡፡ በንጉሡ ፊት ዮርዳኖስን አቋረጠው ተሻገሩ፡፡
18የተሻገሩት የንጉሡን ቤተሰብ ለማምጣትና እርሱ መልካም ነው ያለውን ለማድረግ ነበር፡፡
19ሳሚ ለንጉሡ፣ “ጌታዬ እኔን በደለኛ አድርጎ አይቁጠረኝ ወይም ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣበት ቀን ባሪያህ በግትረኛነት ያደረገውን ትኩረት አይስጠው፡፡ ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ ይህንን በልብህ አታኑረው፡፡
20ባሪያህ ኃጢአት ማድረጌን አውቃለሁ፡፡ ከመላው የዮሴፍ ቤት ጌታዬ ንጉሡን ለመቀበል የመጀመሪያ ሆኜ ዛሬ የመጣሁት እነሆ፣ ለዚህ ነው፡፡” አለ፡፡
21ነገር ግን የጽሩይ ልጅ አቢሳ፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ተራግሟልና ስለዚህ ጉዳይ ሳሚ ሊገደል አይገባውምን?”
22ከዚያ በኋላ ዳዊት፣ “ዛሬ ለእኔ ጠላቶች ትሆኑኝ ዘንድ እናንተ የጽሩያ ልጆች ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ በእስራኤል አንድ ሰው ሊገደል ይገባዋል? በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁት በዛሬው ቀን አይደለምን?”
23ስለዚህ ንጉሡ ለሳሚ፣ “አትሞትም” አለው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ በመሐላ ቃል ገባለት፡፡
24ከዚያ በኋላ የሳዖል ልጅ ሜምፊቦስቴ ንጉሡን ለመቀበል መጣ፡፡ ንጉሡ ከሄደበት ቀን ጀምሮ በሰላም ወደ ቤቱ እስከተመለሰበት ቀን ድረስ በእግሩ ሱሪ አላስገባም፣ ጢሙን አልተላጨም ወይም ልብሱን አላጠበም፡፡
25ስለዚህም ንጉሡን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ ከእኔ ጋር ለምን አልሄድክም?” አለው፡፡
26እርሱም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አገልጋዬ አታለለኝ፣ ምክንያቱም፣ ‘እኔ ባሪያህ ሽባ ስለሆንኩኝ እንድቀመጥበትና ከንጉሡ ጋር እንድሄድ አህያዬን እጭናለሁ’ ብዬ ነበርና፡፡
27አገልጋዬ ሲባ እኔን ባሪያህን ለጌታዬ ለንጉሡ አማ፤ ጌታዬ ንጉሡ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡ ስለዚህ በዓይንህ ፊት መልካም መስሎ የታየህን አድርግብኝ፡፡
28የአባቴ ቤት ሰዎች ሁሉ በጌታዬ በንጉሡ ዘንድ የሞት ሰዎች ነበሩና፤ ነገር ግን ባሪያህን በገበታህ ከሚበሉት አንዱ አድርገህ አስቀመጥኸኝ፡፡ ስለዚህ አሁንም በንጉሡ ፊት ልቅሶዬን ለመቀጠል እኔ ምን መብት አለኝ?”
29ከዚያ በኋላም ንጉሡ፣ “ከዚህ በላይ መግለጫ መስጠት ምን ያስፈልጋል? እርሻውን አንተና ሲባ እንድትካፈሉት ወስኛለሁ፡፡”
30ስለዚህ ሜምፊቦስቴ ለንጉሡ፣ “ጌታዬ ንጉሡ ወደ ራሱ ቤት በሰላም ስለመጣ፣ ግድ የለም፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው፡፡
31ከዚያም ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ለመሻገር ከሮግሊም መጣ፣ ንጉሡም ዮርዳኖስን ሲሻገር አጀበው፡፡
32ቤርዜሊ ሰማንያ ዓመት የሆነው ሽማግሌ ሰው ነበር፡፡ እጅግ ባለጠጋ ሰው ስለነበረ፣ ንጉሡ በመሃናይም በቆየበት ጊዜ ስንቅ አምጥቶለት ነበር፡፡
33ንጉሡም ለቤርዜሊ፣ “ከእኔ ጋር ና፣ እኔ በኢየሩሳሌም የምትመገበውን አቀርብልሃለሁ” አለው፡፡
34ቤርዜሊም ለንጉሡ፣ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ዘንድ ከሕይወት ዘመኔ ምን ያህል ቢቀር ነው?
35እኔ ሰማንያ ዓመቴ ነው፤ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? ባሪያህ የሚበላውንስ ሆነ የሚጠጣውን ጣዕም መለየት ይችላልን? የሚዘፍኑ ወንዶችንና የሚዘፍኑ ሴቶችን ከእንግዲህ መስማት እችላለሁን? ስለዚህ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን ሸክም ይሆናል?
36ባሪያህ የሚፈልገው ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን መሻገር ብቻ ነው፡፡ ንጉሡ ለባሪያው ይህንን ያህል ብድራት ለምን ይከፍለኛል?
37በአገሬ እሞት ዘንድ፣ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እቀበር ዘንድ፣ እባክህ ወደ አገሬ እንድመለስ ፍቀድልኝ፡፡ ነገር ግን አገልጋይህ ከመዓም ከዚህ አለ፣ እርሱ ከአንተ ጋር ይሻገር፣ የመሰለህን መልካም ነገር አድርግለት፡፡”
38ንጉሡም፣ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገራል፣ ለአንተም መልካም መስሎ የታየህን አደርግለታለሁ፤ ከእኔም የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር እኔ አደርግልሃለሁ፡፡”
39ከዚያም ሰዎቹ ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ከዚያም ንጉሡ ተሻገረ፣ ንጉሡም ቤርዜሊን ሳመው ባረከውም፡፡ ከዚህ በኋላ ቤርዜሊ ወደ ራሱ አገር ተመለሰ፡፡
40ስለዚህ ንጉሡ ወደ ጌልጌላ ተሻገረ፣ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ተሻገረ፡፡ የይሁዳ ሠራዊት ንጉሡንና የእስራኤልን ግማሽ ሠራዊት ይዞ ተመለሰ፡፡
41ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው ለንጉሡ፣ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች አንተን ዳዊትንና ቤተሰቡን እንዲሁም የዳዊትን ሰዎች ሰርቀው ዮርዳኖስን አሻግረው ለምን አመጧቸው?”
42ስለዚህ የይሁዳ ሰዎች ለእስራኤል ሰዎች፣ “ይህንን ያደረግነው ንጉሡ የቅርብ ዘመዳችን ስለሆነ ነው፡፡ ታዲያ እናንተ በዚህ ለምን ትቆጣላችሁ? እኛ የበላነውና ንጉሡ መክፈል ያለበት አንዳች ነገር አለ? ለእኛስ አንዳች ስጦታ ሰጥቶናል?”
43የእስራኤል ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች፣ “እኛ ከዳዊት ጋር የሚዛመዱ አሥር ነገዶች አሉን፣ ስለዚህ እኛ ከእናንተ ይልቅ በዳዊት ዘንድ መብት አለን፡፡ ታዲያ እናንተ እኛን ለምን ትንቁናላችሁ? ንጉሡን ለማምጣት ያቀረብነው ሃሳብ በመጀመሪያ ሊሰማ የሚገባው አልነበረምን? ነገር ግን የይሁዳ ሰዎች የሰጡት መልስ የእስራኤል ሰዎች ከሰጡት መልስ ይልቅ እጅግ የከረረ ነበር፡፡”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።