1ዳዊት አብሮት የነበሩትን ወታደሮች ቆጠረ፤ በእነርሱም ላይ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችን ሾመላቸው፡፡
2ከዚህ በኋላ ዳዊት ሠራዊቱን ሲሦውን በኢዮአብ፣ ሲሦውን በኢዮአብ ወንድም በጽሩይ ልጅ በአቢሳ፣ ሲሦውን ደግሞ በጌታዊው በኢታይ አዛዥነት ሥር ላካቸው፡፡ ንጉሡም ለሠራዊቱ፣ “እኔ ራሴም አብሬአችሁ በእርግጥ እወጣለሁ” አላቸው፡፡
3ሰዎቹ ግን፣ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፣ ሰዎቹ ስለ እኛ ግድ አይኖራቸውም ወይም ከእኛ ግማሻችን እንኳን ብንሞት ደንታም የላቸውም፡፡ አንተ ግን ከእኛ አሥር ሺሁ ያህል ነህ፤ ስለዚህ በከተማ ሆነህ ልትረዳን ዝግጁ ብትሆን የተሻለ ነው፡፡” አሉት፡፡
4ስለዚህ ንጉሡ፣ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህ ሠራዊቱ ሁሉ በመቶና በሺህ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ ንጉሡ በከተማይቱ ቅጥር በር ቆሞ ነበር፡፡
5ንጉሡ ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ ለወጣቱ ለአቤሴሎም ራሩለት” ብሎ አዘዛቸው፡፡ ሕዝቡ ሁሉ አቤሴሎምን በሚመለከት ንጉሡ ይህንን ትዕዛዝ ለአዛዦቹ ሲሰጣቸው ሰሙ፡፡
6ስለዚህ እስራኤልን ይወጋ ዘንድ ሠራዊቱ ከከተማ ወጣ፤ ውጊያውም እስከ ኤፍሬም ደን ተስፋፋ፡፡
7በዚያ የእስራኤል ሠራዊት በዳዊት ወታደሮች ድል ሆነ፤ በዚያ ሃያ ሺህ ሰው የሞተበት ታላቅ እልቂት በዚያ ቀን ነበረ፡፡
8ውጊያው በገጠሩ ሁሉ ተስፋፋ፣ በሰይፍ ካለቀውም ይልቅ ጫካ ውጦ ያስቀረበው ሰው በለጠ፡፡
9አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ከጥቂቶቹ ጋር ተገናኘ፡፡ አቤሴሎምም በበቅሎው እየጋለበ ነበር፤ በቅሎውም ጥቅጥቅ ያሉ ቅርንጫፎች በነበሩት የወርካ ዛፍ ሥር ያልፍ ነበርና ራሱ በዛፉ ቅርንጫፎች ተያዘ፡፡ የተቀመጠበት በቅሎ ከሥሩ አልፎ ሲሄድ እርሱ በሰማይና በምድር ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡
10አንድ ሰው ይህንን ተመልክቶ፣ “እነሆ፣ አቤሴሎም በወርካ ዛፍ ላይ ተንጥልጥሎ አየሁት” ብሎ ለኢዮአብ ነገረው፡፡
11ኢዮአብም ስለ አቤሴሎም ለነገረው ሰው፣ “እነሆ፣ አንተ አየኸው፣ ታዲያ መትተህ ለምን ወደ መሬት አልጣልከውም? እኔ አሥር የብር ሰቅልና ቀበቶ በሸለምኩህ ነበር፡፡”
12ሰውዬውም ለኢዮአብ፣ “አሥር ሺህ ሰቅል የምቀበል ብሆንም እንኳን እጄን ዘርግቼ የንጉሡን ልጅ ባልነካሁም ነበር፤ ምክንያቱም አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ንጉሡ፣ ‘አንድም ሰው ወጣቱን አቤሴሎምን እንዳይነካው’ ብሎ ሲያዛችሁ ሁላችንም ሰምተናል፡፡
13ውሸት በመናገር ሕይወቴን አደጋ ላይ ብጥል እንኳን (ከንጉሡ የሚደበቅ ምንም ነገር አይኖርምና) አንተ ታጋልጠኝ ነበር፡፡” አለው፡፡
14ከዚህ በኋላ ኢዮአብ፣ “እኔ አንተን አልጠብቅም” አለ፡፡ ስለዚህ ኢዮአብ ሦስት ጦር ወስዶ ገና በሕይወት እያለና በወርካው ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሳለ በአቤሴሎም ልብ ላይ ተከላቸው፡፡
15ከዚያ በኋላም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት፡፡
16ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ-መለከቱን ነፋ፣ ኢዮአብም ከልክሏቸው ስለነበረ ሠራዊቱ እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ፡፡
17አቤሴሎምን ወስደው በጫካ ውስጥ ወደነበረ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ በሚሸሽበት ጊዜ በአስከሬኑ ላይ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፡፡
18አቤሴሎም፣ “የስሜን መታሰቢያ የሚያስጠራ ልጅ የለኝምና” በማለት ገና በሕይወቱ ሳለ ለራሱ አንድ ትልቅ የድንጋይ ሐውልት በንጉሡ ሸለቆ አቁሞ ነበር፡፡ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ስለነበረ፣ እስከዚህ ቀን ድረስ ‘የአቤሴሎም ሐውልት’ ተብሎ ይጠራል፡፡
19በዚህ ጊዜ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ እግዚአብሔር ከጠላቶቹ እንዳዳነው ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው አለ፡፡
20ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን የምታደርስለት አንተ አይደለህም፣ ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ፤ የንጉሡ ልጅ ስለሞተ ምንም የምሥራች አታደርስም፡፡”
21ከዚያም ኢዮአብ ለአንድ ኩሻዊ፣ “ሂድና ለንጉሡ ያየኸውን ተናገር” አለው፡፡ ኩሻዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ፡፡
22የሳዶቅ ልጅ አኪማአስም እንደገና ለኢዮአብ፣ “ምንም ዓይነት ነገር ይሁን፣ እባክህ፣ ኩሻዊውን ተከትዬው ልሩጥ” አለው፡፡ ኢዮአብም፣ “ለየምሥራቹ ምንም ብድራት እንደማታገኝ እያወቅህ፣ ልጄ ሆይ፣ ለምን ትሮጣለህ?” ብሎ መለሰለት፡፡
23“የሆነው ይሁን፣ እሮጣለሁ” አለ፣ አኪማአስ፡፡ ስለዚህ ኢዮአብ ፣ “እንግዲያውስ፣ ሩጥ” ብሎ መለሰለት፡፡ ከዚያም አኪማአስ በሜዳው መንገድ በኩል ሮጠ፣ ኩሻዊውንም ቀደመው፡፡
24ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ነበር፡፡ ጠባቂው ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጥቶ ወደ ውጭ ዓይኑን አንስቶ ሲመለከት አንድ ብቻውን የሚሮጥ ሰው እየተቃረበ ነበር፡፡
25ጠባቂው ተጣራና ለንጉሡ ነገረው፤ ከዚያም ንጉሡ፣ “ብቻውን ከሆነ መልካም ዜና በአንደበቱ አለ” አለ፡፡ ሯጩ እየተጠጋ መጥቶ ወደ ከተማይቱ ቀረበ፡፡
26ከዚያም ጠባቂው ሌላ የሚሮጥ ሰው አስተዋለ፤ ጠባቂውም ዘበኛውን ጠራና፣ “እነሆ፣ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አለ” አለው፡፡ ንጉሡም፣ “እርሱም መልካም ዜና አለው” አለ፡፡
27ስለዚህ ጠባቂው፣ “ከፊት እየሮጠ ያለው ሰው አሯሯጥ የሳዶቅን ልጅ የአኪማአስን ሩጫ ይመስለኛል” አለ፡፡ ንጉሡም፣ “እርሱ ጥሩ ሰው ነው፣ እርሱም የሚመጣው የምሥራች ይዞ ነው” አለ፡፡
28ከዚያ በኋላ አኪማአስ ተጣርቶ ለንጉሡ፣ “ሁሉም ደኅና ነው” አለና በንጉሡ ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሥቶ፣ ወደ መሬት እያቀረቀረ፣ “በጌታዬ በንጉሡ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠህ እግዚአብሔር አምላክህ የተባረከ ይሁን” አለው፡፡
29ንጉሡም፣ “ወጣቱ አቤሴሎም ደህና ነውን? ሲል ጠየቀ፡፡ አኪማአስም፣ “ኢዮአብ እኔን የንጉሡን አገልጋይ በላከኝ ጊዜ ትልቅ ሁካታ ነበር፣ ምን እንደሆነ ግን እኔ አላወቅሁም” አለው፡፡
30ከዚያ በኋላ ንጉሡ፣ “እልፍ በልና ቁም” አለው፡፡ ስለዚህ አኪማአስ እልፍ ብሎ ዝም ብሎ ቆመ፡፡
31ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ኩሻዊው ደረሰና፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ የምሥራች አለኝ፣ እግዚአብሔር በንጉሡ ላይ የተነሡብህን ሁሉ ዛሬ ተበቅሎልሃልና” አለው፡፡
32ንጉሡም ኩሻዊውን፣ “ወጣቱ አቤሴሎም ደህና ነውን?” አለው፡፡ ኩሻዊውም፣ “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች እንዲሁም በእርሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ በአንተ ላይ የሚነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ወጣት ይሁኑ” ብሎ መለሰለት፡፡
33በዚያን ጊዜ ንጉሡ ጥልቅ የሆነ ሐዘን አዘነ፤ በቅጥሩ በር ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ገብቶም አለቀሰ፡፡ እየሄደም ሳለ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም ልጄ፣ ልጄ!” እያለ ያለቅስ ነበር፡፡