መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 17

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ አኪጦፌል ለአቤሴሎም፣ “አሥራ ሁለት ሺህ ሰው መርጬ በዛሬይቱ ሌሊት አባትህን አሳድደዋለሁ፤
2በደከመውና ዐቅም ባነሰው ጊዜ ድንገት ደርሼ በማስፈራት አስደንቀዋለሁ፤ አብሮት ያለው ሕዝብም ይሸሻል፣ በንጉሡ ላይ ብቻ ጥቃት አደርስበታለሁ፡፡
3ሙሽራ ወደ ባሏ እንደምትመጣ ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንተ ሥር በሰላም ይሆናል፡፡”
4አኪጦፌል የተናገረውም አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኛቸው፡፡
5ከዚያ በኋላ አቤሴሎም፣ “አርካዊውን ኩሲን አሁን ጥሩትና እስቲ፣ እርሱ ደግሞ የሚለውን እንስማ” አለ፡፡
6ኩሲ ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ፣ አኪጦፌል ያለውን ከገለጸለት በኋላ፣ ኩሲን፣ “አኪጦፌል ያለውን እናድርግ? ካልሆነም የምትመክረንን አንተ ንገረን፡፡”
7ስለዚህ ኩሱ ለአቤሴሎም፣ “አኪጠፌል በዚህን ጊዜ የሰጠው ምክር መልካም አይደለም፡፡” ካለ በኋላ፣
8ኩሲ በመቀጠል፣ “አባትህና ሰዎቹ ብርቱ ተዋጊዎችና ግልገሎቿ በሜዳ እንደተነጠቁባት ድብ መራሮች እንደሆኑ አንተ ታውቃለህ፡፡ አባትህ የጦር ሰው ነው፣ በዛሬው ሌሊት ከሠራዊቱ ጋር አይተኛም፡፡
9እነሆ፣ አሁን እንኳ በአንዱ ዋሻ ወይም በሌላ ቦታ ተደብቆ ይሆናል፡፡ በውጊያው መጀመሪያ ላይ ከአንተ ሰዎች ጥቂቶቹ ቢሞቱ፣ ያንን የሰማ ማንኛውም ሰው፣ ‘አቤሴሎምን ይከተሉ በነበሩት ላይ እልቂት ተፈጽሟል’ ይላል፡፡
10ከዚያ በኋላ አባትህ ኃያል ሰው ስለሆነና ከእርሱም ጋር ያሉት በጣም ብርቱዎች መሆናቸውን መላው እስራኤል ስለሚያውቅ ልባቸው እንደ አንበሳ ልብ የሆነው እጅግ ጀግና የሆኑት እንኳን ይፈራሉ፡፡
11ስለዚህ እኔ የምመክርህ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ የሆነው ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው መላው የእስራኤል ሕዝብ ወደ አንተ ይሰብሰብ፣ አንተም በግልህ ወደ ጦርነቱ ግባ፡፡
12ከዚያ በኋላ እርሱ በየትኛውም ቦታ ቢሆን እንመጣበታለን፣ ጤዛም ምድርን እንደሚሸፍን በላዩ ላይ እንወድቅበታለን፡፡ ከእርሱ ማንኛውንም ሰው ወይም እርሱን ራሱንም እንኳን ቢሆን በሕይወት አንተውም፡፡
13ወደ አንዲት ከተማ የሚያፈገፍግ እንኳ ቢሆን፣ እስራኤል ሁሉ ገመድ አምጥቶ አንድ እንኳ እስከማይቀር ድረስ ከተማይቱን ወደ ወንዝ ውስጥ ስበን እንከታታለን፡፡”
14ከዚያም አቤሴሎምና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ፣ “የአርካዊው ኩሲ ምክር ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የተሻለች ነች” አሉ፡፡ በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ይመጣ ዘንድ እግዚአብሔር የአኪጦፌል መልካም ምክር ተቀባይነት እንዳያገኝ አደረገ፡፡
15ከዚያም ኩሲ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር፣ “አኪጦፌል አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው መክሮአቸው ነበር፣ እኔ ግን የተለየ ምክር ሰጠኋቸው፡፡
16እንግዲህ እናንተ ፈጥናችሁ ወደ ዳዊት ዘንድ ሂዱና ፣ ‘በአረባ ባለው የወንዙ መሻገሪያ እንዳታድር፣ ነገር ግን እንደ ምንም ብለህ ተሻገር፤ አለበለዚያ ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ትዋጣላችሁ’ በሉት፡፡”
17በዚህ ጊዜ፣ ዮናታንና አኪማአስ በዓይንሮጌል ባለችው ምንጭ ይጠብቁ ነበር፣ ወደ ከተማ ሲገቡ እንዳይታዩ አንዲት ሴት አገልጋይ ወደ እነርሱ እየሄደች መልእከቶችን ታቀብላቸው ነበር፤ እነርሱም በዚያን ጊዜ ለዳዊት ሄደው ይነግሩት ነበር፡፡
18በዚህን ጊዜ ግን አንድ ወጣት አያቸውና ለአቤሴሎም ሄዶ ነገረ፡፡ ስለዚህ ዮናታንና አኪማአስ ፈጥነው በግቢው ውስጥ የውሃ ጉድጓድ ወደነበረው በብራቂም ወደ ነበረ ሰው ቤት መጡ፡፡
19የሰውዬው ሚስት የውሃ ጉድጓዱን መሸፈኛ ወስዳ በጉድጓዱ አፍ ላይ ዘረጋችው ከዚያ በኋላም ዮናታንና አኪማአስ በውሃ ጉድጓድ ዘንድ እንዳሉ ማንም እንዳያውቅ በላዩ ላይ እህል አሰጣችበት፡፡
20የአቤሴሎም ሰዎች በቤት ወደነበረችው ሴትዮ መጡና፣ “አኪማአስና ዮናታን ወዴት አሉ?” አሏት፤ እርሷም፣ “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” አለቻቸው፡፡ ስለዚህ ፈልገው ሊያገኟቸው ስላልቻሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡
21እነርሱ ከሄዱ በኋላ አኪማአስና ዮናታን ከጉድጓዱ ወጡ፤ ወደ ዳዊትም ዘንድ ሄደው፣ “ተነሣና ፈጥነህ ወንዙን ተሻገር፣ ምክንያቱም አኪጦፌል አንተን በሚመለከት እንደዚህና እንደዚያ ብሎ ምክር ሰጥቶአል፡፡”
22ከዚያ በኋላ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበረው ሕዝብ ተነሡ፣ የዮርዳኖስንም ወንዝ ተሻግረው ሄዱ፤ ሲነጋም ዮርዳኖስን መሻገር አቅቶት የቀረ አንድም ሰው አልነበረም፡፡
23አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተቀበሉት ባየ ጊዜ አህያውን ጭኖ ቤቱ ወዳለበት ወደ መኖሪያ ከተማው ሄደ፣ ጉዳዩንም መልክ ካስያዘ በኋላ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ፡፡ በዚህ አኳኋን ሞተና በአባቱ መቃብር ተቀበረ፡፡
24ከዚያ በኋላ ዳዊት ወደ መሃናይም መጣ፤ አቤሴሎምም ከእርሱ ጋር ከነበሩት ከመላው የእስራኤል ሰዎች ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ፡፡
25ከዚህ በኋላም አቤሴሎም በኢዮአብ ምትክ አሜሳይን በሠራዊቱ ላይ ሾመ፤ አሜሳይ የእስራኤላዊው የዮቴር ልጅ ነበር፡፡ ዮቴር ከኢዮአብ እናት ከጽሩያ እህት ከናዖስ ልጅ ከአቢግያ ጋር ተኝቶ የነበረ ነው፡፡
26ከዚህ በኋላ እስራኤላውያንና አቤሴሎም ከበገለዓድ ምድር ሰፈሩ፡፡
27ዳዊት ወደ መሃናይም በመጣ ጊዜ ከአሞናውያን ከተማ ከራባ የመጣው፣ የናዖስ ልጅ ሾቢ፣ ከሎዶባር የመጣው የዓሚኤል ልጅ ማኪርና ከሮግሊም የመጣው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ፣
28መተኛ ምንጣፎችና ብርድ ልብሶች፣ ጎድጓዳ ሳህኖችና ድስቶች እንዲሁም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ይበሉ ዘንድ ስንዴ፣ የገብስ ዱቄት፣ የተጠበሰ እሸት፣ ባቄላ፣ ምስር፣
29ማር፣ ቅቤ፣ በግና እርጎ አመጡ፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ “ሕዝቡ በምድረ-በዳ ተርቦአል፣ ደክሞአል ደግሞም ተጠምቶአል” ብለው ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።