1ዳዊት ከተራራው ጫፍ ባሻገር ጥቂት እልፍ ብሎ እንደሄደ ሲባ የተባለው የሜምፊቦስቴ አገልጋይ፣ ሁለት መቶ እንጀራ አንድ ሙሉ ጥፍጥፍ ዘቢብ አንድ መቶ ጥፍጥፍ በለስና አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች ይዞ ተገናኘው፡፡
2ንጉሡም ሲባን፣ “ይህን ሁሉ ያመጣኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ሲባም፣ “አህዮቹን የንጉሡ ቤተ ሰቦች እንዲቀመጡባቸው፣ እንጀራውንና በለሱን ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እንዲበሉት፣ የወይን ጠጁ ደግሞ በምድረ-በዳ የደከመ ማንኛውም ሰው እንዲጠጣው ነው” አለው፡፡
3ንጉሡም፣ “የጌታህ የልጅ ልጅ የት ነው?” አለው፡፡ ሲባም ለንጉሡ፣ “’ዛሬ የእስራኤል ቤት የአባቴን መንግሥት ለእኔ ይመልስልኛል’ እያለ ስለነበረ፣ እነሆ፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል” ብሎ መለሰለት፡፡
4ከዚያም ንጉሡ ሲባን፣ “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ፣ እነሆ፣ የአንተ ሆኖአል” አለው፡፡ ሲባም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ በትሕትና በፊትህ እጅ እነሣለሁ፣ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው፡፡
5ንጉሥ ዳዊት ወደ ብራቂም ሲደርስ ከሳዖል ቤተሰብ ነገድ የሆነ የጌራ ልጅ ሳሚ ብቅ አለ፡ እርሱም እየመጣ ሳለ ይራገም ነበር፡፡
6የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊትና ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳን፣ በዳዊትና በሹማምንቱ ላይ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር፡፡
7ሳሚም እንደዚህ ብሎ ተራገመ፣ “ውጣ፣ ከዚህ ውጣ፣ አንተ ወሮበላ፣ አንተ የደም ሰው፤
8በእርሱ ምትክ የነገሥህበትን የሳዖልን ቤተሰብ ደም ብድራት ሁሉ እግዚአብሔር እየከፈለህ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንግሥቱን በልጅህ በአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ አሁንም አንተ የደም ሰው ስለሆንክ ጥፋት ደርሶብሃል፡፡”
9ከዚህ በኋላ የጽሩይ ልጅ አቢሳ፣ “ይህ የሞተ ውሻ ንጉሡ ጌታዬን ለምን ይራገማል? እባክህ፣ ተሻግሬ ልሂድና ራሱን ልቁረጠው” አለ፡፡
10ንጉሡ ግን፣ “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እርሱ የሚረግመኝ ምናልባት እግዚአብሔር፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት ይሆናል፡፡ ታዲያ እርሱን፣ ‘ንጉሡን ለምን ትረግማለህ?’ ሊለው የሚችለው ማን ነው?”
11ስለዚህ ዳዊት ለአቢሳና ለአገልጋዮቹ ሁሉ፣ “ከአብራኬ የወጣው ልጄ ነፍሴን ሊያጠፋት ከፈለገ፣ ይህ ብንያማዊ ምን ያህል ጥፋቴን አይፈልግ? እግዚአብሔር እንዲራገም አዞት ይሆናልና፣ ተዉት፣ ይራገም፡፡
12ምናልባት የተሰነዘረብኝን ውርደት እግዚአብሔር ተመልክቶ ስለ ዛሬው እርግማኑ በጎ ያደርግልኝ ይሆናል፡፡”
13ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ በመንገዱ ጉዟቸውን ቀጠሉ፣ ሳሚም በኮረብታው ጥግ ጥግ እየሄደ ድንጋይ ይወረውር አቧራም ይበትንበት ነበር፡፡
14ከዚህ በኋላ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ደከሙ፣ እነርሱም ለምሽቱ በሚቆሙበት ጊዜ እርሱ ዕረፍቱ አደረገ፡፡
15አቤሴሎምና ከእነርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ በበኩላቸው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፣ አኪጦፌልም ከእርሱ ጋር ነበረ፡፡
16የዳዊት ወዳጅ፣ አርካዊው ኩሲም ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ፣ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ንገሥ!” አለው፡፡
17አቤሴሎምም ኩሲን፣ “ለወዳጅህ ያለህ ታማኝነት ይሄ ነው? ለምን ከእርሱ ጋር አልሄድህም?” አለው፡፡
18ኩሲም አቤሴሎምን፣ “አይሆንም፣ ይልቁኑ እግዚአብሔርና ይህ ሕዝብ እንዲሁም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ከመረጡት ከእርሱ ጋር ነው እኔ የምሆነው፣ ከእርሱም ጋር እቆያለሁ፡፡
19ላገለግለው የሚገባኝ ሰው ማን ነው? በልጁስ ፊት ላገለግል አይገባኝምን? በአባትህ ፊት እንዳገለገልሁ በአንተም ፊት አገለግላለሁ፡፡”
20ከዚያ በኋላ አቤሴሎም ለአኪጦፌል፣ “ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክርህን ስጠን” አለው፡፡
21አኪጦፌልም ለአቤሴሎም፣ “ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ አባትህ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፣ ከዚያም አንተ ለአባትህ መጥፎ ጠረን እንዳለው ሰው እንደሆንክበት እስራኤል ሁሉ ይሰማል፤ ከዚያም ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች ሁሉ እጅ ይበረታል፡፡”
22ስለዚህ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ለአቤሴሎም ድንኳን ተከሉለት፤ አቤሴሎምም መላው እስራኤል እያየው ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ፡፡
23በዚያን ጊዜ አኪጦፌል ይሰጠው የነበረው ምክር ከእግዚአብሔር ከራሱ አፍ እንደ መስማት ያለ ነበር፡፡ ዳዊትም ሆነ አቤሴሎም ለአኪጦፌል ምክር የነበራቸው ግምት እንደዚህ ነበር፡፡