1ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ ሃምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ፡፡
2አቤሴሎም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማይቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆማል፡፡ ሙግት ያለበት ማንኛውም ሰው ዳኝነት ለማግኘት ወደ ንጉሡ ሲመጣ፣ በዚያን ጊዜ አቤሴሎም ወደ እርሱ ይጠራውና፣ “ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” ይለው ነበር፡፡ ሰውዬውም፣ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው?” ይለው ነበር፡፡
3ከዚህም የተነሣ አቤሴሎም፣ “ተመልከት፣ ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ጉዳይህን ለመመልከት ከንጉሡ ሥልጣን የተሰጠው ማንም ሰው የለም፡፡” ይለው ነበር፡፡
4ከዚህ ጋር በማያያዝ አቤሴሎም፣ “ሙግት ወይም ጉዳይ ያለው ማንኛውም ሰው ወደ እኔ እንዲመጣና እኔም ፍትሕ እንድሰጠው በምድሪቱ ዳኛ ሆኜ መሾም እመኛለሁ” ይል ነበር፡፡
5ስለዚህ ክብርን ሊሰጠው ማንኛውም ሰው ወደ አቤሴሎም በሚመጣበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር፡፡
6ከንጉሡ ፍትሕ ለማግኘት በሚመጡ እስራኤላውያን ሁሉ አቤሴሎም እንደዚህ ያደርግ ነበር፡፡ በዚህም ሁኔታ አቤሴሎም የእስራኤላውያንን ልብ ሰረቀ፡፡
7በአራተኛው ዓመት ፍጻሜ አቤሴሎም ለንጉሡ፣ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ እባክህን ፍቀድልኝ፡፡
8ባሪያህ በአራም በጌሹር በነበርኩበት ጊዜ፣ ‘እግዚአብሔር በእርግጥ ወደ ኢየሩሳሌም ዳግመኛ የመለሰኝ እንደሆነ በኬብሮን እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስዬ ነበር፡፡”
9ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፡፡
10አቤሴሎም ግን ወደ መላው የእስራኤል ነገዶች፣ “የመለከትን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ’ ማለት ይገባችኋል” የሚሉ ሰላዮችን ላከ፡፡
11ከአቤሴሎምም ጋር ሁለት መቶ የተጋበዙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፡፡ አቤሴሎም ምን እንዳቀደ ምንም ነገር ሳያውቁ በየዋህነት ነበረ የሄዱት፡፡
12አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ ለሆነው ለአኪጦፌል ወደሚኖርበት ወደ ጊሎ መልእክት ላከበት፡፡ አቤሴሎምን ይከተለው የነበረው ሕዝብ እየጨመረ ስለነበረ የአቤሴሎም ሤራ ጠንካራ ነበር፡፡
13“የእስራኤል ሰዎች ልብ አቤሴሎምን እየተከተለ ነው፡፡” የሚል መልእክተኛ ወደ ዳዊት መጣ፡፡
14ስለዚህ ዳዊት በኢየሩሳሌም ለነበሩት አገልጋዮቹ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ለመውጣት ተዘጋጁ አለዚያ እርሱ መጥቶ ይይዘናል በእኛም ላይ ጥፋት ያደርስብናል፣ ከተማይቱንም በሰይፍ ይመታታል፡፡” አላቸው፡፡
15የንጉሡም አገልጋዮች፣ “እነሆ፣ ጌታችን የወሰነውን ማንኛውንም ለማድረግ አገልጋዮችሀ ዝግጁ ነን” በማለት ለንጉሡ ነገሩት፡፡
16ንጉሡ ከእርሱም ጋር መላው ቤተሰቡ ሄዱ፣ ነገር ግን ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁ ዘንድ ቁባቶች የነበሩ አሥር ሴቶችን እንዲቀሩ አደረገ፡፡
17ንጉሡና እርሱን ተከትሎ መላው ሕዝብ ከሄደ በኋላ ከመጨረሻው ቤተ ሲደርሱ ቆሙ፡፡
18ሠራዊቱ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተጓዙ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡት ስድስት መቶ ጌታውያን በንጉሡ ፊት አለፉ፡፡
19ከዚያም ንጉሡ ጌታዊውን ኢታይን፣ “አንተ ደግሞ ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? እንግዳና ስደተኛ ነህና ተመልሰህ ሄደህ ከአቤሴሎም ጋር ቆይ፤ ወደ ራስህ አገር ሂድ፡፡
20የወጣኸው ገና ትላንት ስለሆነ፣ ከእኔ ጋር በየቦታው ለምን እንድትንከራተት ላድርግህ? ወዴት እንደምሄድ እንኳን አላውቅም፡፡ ስለዚህ ተመለስ የአገርህንም ሰዎች መልሳቸው፤ በጎነትና ታማኝነት ከአንተ ጋር ይሁን፡፡” አለው፡፡
21ኢታይ ግን ለንጉሡ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት ንጉሡ ወደሚሄድበት ወደየትኛውም ቦታ አገልጋይህም ይሄዳል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
22ስለዚህ ዳዊት ለኢታይ፣ “እንግዲያውስ፣ ከእኛ ጋር መሄድህን ቀጥል” አለው፡፡ ከእርሱ ጋር ከነበሩት ሰዎች ሁሉና አብረውት ከነበሩት ቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ጌታዊው ኢታይ ከንጉሡ ጋር ተጓዘ፡፡
23ሕዝቡ ሁሉ ንጉሡም ራሱ የቄድሮንን ወንዝ ሲሻገሩ የአገሩ ሕዝብ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ምድረ-በዳ በሚወስደው መንገድ ተጓዘ፡፡
24ሳዶቅም እንኳን የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ከተሸከሙት ሌዋውያን ጋር በዚያ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡትና አብያታር ከእነርሱ ጋር ሆነ፤ እነርሱም ሕዝቡ ሁሉ ከከተማይቱ እስኪወጡ ድረስ ጠበቁ፡፡
25ንጉሡም ሳዶቅን፣ “ታቦቱን ወደ ከተማይቱ ይዘህ ተመለስ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ካገኘሁ ወደዚህ መልሶ ያመጣኛል፣ ታቦቱንና እርሱም የሚኖርበትን ስፍራ እንደገና ያሳየኛል፡፡
26ነገር ግን እርሱ፣ ‘በአንተ አልተደሰትሁም’ ካለኝ፣ እነሆ፣ በፊቱ አለሁ፣ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግብኝ፡፡”
27ንጉሡ ለካህኑ ለሳዶቅ፣ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? አንተ ከሁለቱ ልጆችህ፣ ከልጅህ አኪማአስና ከአብያታር ልጅ ከዮናታን ጋር ሆናችሁ በሰላም ወደ ከተማይቱ ተመለሱ፡፡
28ከአንተ ዘንድ መልእክት እስካገኝ ድረስ፣ እነሆ፣ እኔ በአረባ በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቆያለሁ፡፡”
29ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እዚያው ቆዩ፡፡
30ዳዊት ግን እያለቀሰ በባዶ እግሩ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፣ ራሱንም ተከናንቦ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር የነበረውም እያንዳንዱ ሰው ራሱን ተከናንቦ ነበር፤ እየሄዱም ሳሉ ያለቅሱ ነበር፡፡
31አንድ ሰውም ለዳዊት፣ “በሤራው ውስጥ ከአቤሴሎም ጋር ካሉት አንደኛው አኪጦፌል ነው” ብሎ ነገረው፡፡ ስለዚህ ዳዊት፣ “እባክህ፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ የአኪጦፌልን ምክር ወደ ሞኝነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ፡፡
32ዳዊት እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ወደ መንገዱ ጫፍ በደረሰ ጊዜ፣ አርካዊው ኩሲ መጎናጸፊያውን ቀድዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ፡፡
33ዳዊትም ለእርሱ፣ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትህንብኛለህ፤
34ነገር ግን ወደ ከተማይቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን ‘ንጉሥ ሆይ፣ አገልጋይህ እሆናለሁ፣ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ አሁን ደግሞ የአንተ አገልጋይ እሆናለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማደናገር ትረዳኛለህ፡፡
35ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተ ጋር አሉልህ አይደለምን? በንጉሡ ቤተ መንግሥት የምትሰማውን ማንኛውንም ነገር ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር መንገር አለብህ፡፡
36የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ሁለቱ ወንዶች ልጆች በዚያ አብረዋቸው መሆናቸውን አረጋግጥ፡፡ የምትሰማውን ማንኛውንም ነገር በእነርሱ በኩል ላክልኝ፡፡”
37ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ኩሲ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት በዚያው ወቅት ወደ ከተማይቱ መጣ፡፡