መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ሳሙኤል 14

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ፡፡
2ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጥቶ፣ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፣ እባክሽን ዘይት አትቀቢ ነገር ግን ለብዙ ጊዜ እንዳዘነች መስለሽ ታዪ፡፡
3ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እኔ የምገልጽልሽን ንገሪው፡፡” ስለዚህ ኢዮአብ ለንጉሡ የምትናገረውን ነገር ነገራት፡፡
4ከቴቁሔ የመጣችውም ሴት ለንጉሡ ለመንገር በገባችበት ጊዜ በንጉሡ ፊት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት፣ “ንጉሥ ሆይ፣ እርዳኝ” አለች፡፡
5ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” አላት፡፡ ሴቲቱም፣ “እኔ በእውነቱ ባሏ የሞተባት ባልቴት ነኝ፡፡
6እኔ ባሪያህ ሁለት ልጆች ነበሩኝ፣ እነርሱም ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፣ የሚገላግላቸውም ሰው አልነበረም፡፡ አንደኛውም ሌላኛውን መታውና ገደለው፡፡
7መላው ቤተሰብም አሁን በባሪያህ ላይ ተነሥቶ፣’ስለገደለው ስለ ወንድሙ ዋጋ እንዲከፍልና እኛም እንድንገድለው ወንድሙን የገደለውን ሰው አውጥተሸ ስጪን’ አሉኝ፤ ወራሽ የሆነውንም ያጠፉ ዘንድ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ዓይነት የቀረኝን አንድ የጋለ ፍም አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው፡፡”
8ስለዚህ ንጉሡ ለሴቲቱ፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፣ አንድ ነገር እንዲደረግልሽ እኔ ትዕዛዝ እሰጣለሁ” አላት፡፡
9የቴቁሔዪቱም ሴት ለንጉሡ፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች፡፡
10ንጉሡም፣ “ማንም ሰው ቢናገርሽ ወደ እኔ ዘንድ አምጪው ከዚያ በኋላም አያስቸግርሽም” በማለት መለሰላት፡፡
11ከዚያ በኋላ ሴቲቱ፣ “ደም ተበቃዩ ሌላ ሰው እንዳያጠፋና ልጄንም እንዳያጠፉት፣ እባክህን ንጉሥ እግዚአብሔር አምላክህን አሳስብልኝ” አለችው፡፡ ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን ከልጅሽ ራስ አንዲት ፀጉር እንኳ አትወድቅም” ብሎ መለሰላት፡፡
12ከዚያ በኋላም ሴቲቱ፣ “ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሡ ተጨማሪ ቃል እንድናገር እባክህ ፍቀድልኝ” አለችው፡፡ ንጉሡም፣ “ተናገሪ” አላት፡፡
13ስለዚህ ሴቲቱ፣ “ታዲያ፣ እንዲሀ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህንን በመናገሩ ንጉሡ ራሱን በደለኛ እንደሚያደርግ ሰው ነው፣ የኮበለለውን ልጁን ንጉሡ ወደ ቤቱ አልመለሰውምና፡፡
14ሁላችንም እንሞት ዘንድ ይገባናልና፣ እንደገናም ሊሰበሰብ እንደማይችል እንደ ፈሰሰ ውሃ ነንና፡፡ እግዚአብሔር ግን የሰውን ሕይወት አይወስድም ይልቁንም ከፊቱ ራሱን ያስኮበለለውን ሰው ወደ ራሱ የሚመልስበት መንገድ ይፈልጋል እንጂ፡፡
15እንግዲህ አሁን ለጌታዬ ለንገሡ ይህንን ልናገር የመጣሁት ሕዝቡ እንድፈራ ስላደረጉኝ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ባሪያህ ለራሷ፣ ‘አሁን ለንጉሡ እናገራለሁ፣ ምናልባትም ንጉሡ የባሪያውን ጥያቄ ይቀበል ያደርግላት ይሆናል፡፡
16እኔንና ልጄን ከእግዚአብሔር ርስት ሊያጠፋን ካለው ሰው እጅ ያድን ዘንድ ባሪያውን ያወጣ ዘንድ ንጉሡ ይሰማኛልና፣’ አለች፡፡
17ከዚያ በኋላም ባሪያህ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል እፎይታን የሚሰጠኝ ይሁን፣ ምክንያቱም መልካሙን ከክፉው በመለየት ጌታዬ ንጉሡ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና’ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ይሁን፡፡”
18ከዚያ በኋላም ንጉሡ ለሴቲቱ፣ “እኔ ለምጠይቅሽ ጥያቄ እባክሽ ምንም ነገር አትደብቂኝ” አላት፡፡
19ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር የለም?” ሴቲቱም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከተናገረው አንዳችም ነገር ማንም ሰው ወደ ቀኝም ወደ ግራም ማምለጥ አይችልም፡፡ ያዘዘኝና ባሪያህም የተናገረችውን እነዚህን ነገሮች እንድናገር የነገረኝ ባሪያህ ኢዮአብ ነው፡፡
20ባሪያህ ኢዮአብ ይህንን ያደረገው ነገሮች እየሄዱበት ያለውን አቅጣጫ ለመለወጥ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ጥበብ ጌታዬ ጠቢብ ነው፤ በምድሪቱም የሚሆነውን ማንኛውንም ነገር ያውቃል፡፡”
21ስለዚህ ንጉሡ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፣ እኔ አሁን ይህንን አደርጋለሁ፡፡ እንግዲህ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን አምጣው” አለው፡፡
22ስለዚህ ኢዮአብ ለንጉሡ አክብሮቱንና ምስጋናውን ለመግለጽ ጎንበስ ብሎ እጅ ነሳ፡፡ ኢዮአብም፣ “ዛሬ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ፊት ሞገስ እንዳገኘ አወቅሁ፣ ንጉሡ የባሪያውን ጥያቄ ፈጽሞለታልና”
23ስለዚህ ኢዮአብ ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፣ አቤሴሎምንም ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡
24ንጉሡም፣ “ወደ ራሱ ቤት መመለስ ይችላል፣ ነገር ግን ፊቴን አያይም” ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ቤቱ ተመለሰ፣ የንጉሡን ፊት ግን አላየም፡፡
25በመላው እስራኤል ከአቤሴሎም ይልቅ በመልከ መልካምነቱ የተመሰገነ ማንም አልነበረም፡፡ ከእግር ተረከዙ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ ምንም እንከን አልነበረበትም፡፡
26ይከብደው ስለ ነበረ የራሱን ፀጉር በሚቆረጥበት ጊዜ ፀጉሩን ይመዝነው ነበር፣ በንጉሡም የመመዘኛ ልክ ሁለት መቶ ሰቅል ይመዝን ነበር፡፡
27አቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የምትባል አንድ ሴት ልጅ ነበሩት፡፡ ሴት ልጁም ውብ ነበረች፡፡
28አቤሴሎምም የንጉሡን ፊት ሳያይ ሁለት ሙሉ ዓመት በኢየሩሳሌም ኖረ፡፡
29ከዚህ በኋላ ወደ ንጉሡ ይወስደው ዘንድ አቤሴሎም ወደ ኢዮአብ መልእክት ላከ፣ ኢዮአብ ግን ሊመጣ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ አቤሴሎም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢዮአብ መልእክት ላከ፣ ኢዮአብ ግን አሁንም አልመጣም፡፡
30ስለዚህ አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ፣ “ኢዮአብ በእኔ እርሻ አጠገብ እርሻ አለው፣ በዚያም ገብስ አለው፤ ሂዱና በገብሱ ላይ እሳት ልቀቁበት” አላቸው፡፡ ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች በእርሻው ላይ እሳት ለቀቁበት፡፡
31ከዚያም ኢዮአብ ተነስቶ ወደ አቤሴሎም ቤት መጣና፣ “አገልጋዮችህ በእርሻዬ ላይ እሳት የለቀቁበት ለምንድን ነው?” አለው፡፡
32አቤሴሎምም ለኢዮአብ፣ “እነሆ፣ ወደ አንተ ዘንድ፣ ‘ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ዘንድ መጥተህ ለንጉሡ፣ ከጌሹር ለምን መጣሁ? እዚያው ብቆይ ይሻለኝ ነበር’ ብለህ እንድትነግርልኝ መልእክት ልኬብህ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን የንጉሡን ፊት ልይ፣ በደለኛ ከሆንኩም ይግደለኝ” አለው፡፡
33ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዶ ነገረው፡፡ ንጉሡም አቤሴሎምን ባስጠራው ጊዜ አቤሴሎም በንጉሡ ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፣ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።