1ከዚህ በኋላ የዳዊት ልጅ አምኖን የዳዊት ሌላ ልጅ የአቤሴሎም ሙሉ እኅት በነበረችው በውቧ ግማሽ እህቱ በትዕማር እጅግ ተማረከ፡፡
2በእኅቱ በትዕማር ምክንያት እስኪታመም ድረስ አምኖን እጅግ ተጨነቀ፡፡ ድንግል ስለነበረች በእርሷ ላይ ምንም ነገር ማድረግ ለአምኖን የማይቻል መሰለው፡፡
3አምኖን ግን የዳዊት ወንድም የሳምዕ ልጅ ኢዮናዳብ የተባለ ወዳጅ ነበረው፡፡ ኢዮናዳብ እጅግ ተንኮለኛ ሰው ነበር፡፡
4ኢዮናዳብም ለአምኖን፣ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፣ በየጥዋቱ ጭንቀት የሚሰማህ ለምንድን ነው? አትነግረኝምን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ አምኖንም፣ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እህት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” ብሎ መለሰለት፡፡
5በዚህን ጊዜ ኢዮናዳብ፣ “የታመምህ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ፣ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፣ ‘እህቴ ትዕማር የምበላውን ምግብ ታቀርብልኝ ዘንድ እባክህ ላክልኝ፤ ምግቡንም ዓይኔ እያየ ከእጇ እንድጎርስ እዚሁ መጥታ ታዘጋጅልኝ’ ብለህ ጠይቀው፡፡”
6ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው በመጣ ጊዜ አምኖን ለንጉሡ፣ “ለሕመሜ የሚሆን ጥቂት ምግብ በፊቴ እንድታዘጋጅልኝና ከእጇም እንድበላ እባክህ እህቴን ትዕማርን ላክልኝ” ብሎ ጠየቀው፡፡
7ከዚያም ዳዊት፣ “አሁን ሂጂና ለወንድምሽ ለአምኖን ምግብ አዘጋጂለት” በማለት በቤተ መንግሥቱ ወደ ነበረችው ትዕማር መልእክት ላከባት፡፡
8ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካችው በኋላ ቂጣ አደረገችው፣ ጋገረችውም፡፡
9ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ ቂጣውን አቀረበችለት፣ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም፡፡ ስለዚህ አምኖን በዘያ ለነበሩት ለሌሎቹ፣ “ማንኛውንም ሰው ከዚህ ከእኔ ዘንድ አስወጡልኝ” አላቸው፤ ስለዚህ ሰው ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ፡፡
10ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “ምግቡን ከእጅሽ እበላ ዘንድ ወደዚህ ወደ ክፍሌ አምጭልኝ” አላት፡፡
11ምግቡን ባመጣችለት ጊዜ አምኖን እጇን ያዛትና፣ “እህቴ ሆይ፣ ነይ ከእኔ ጋር ተኚ” አላት፡፡
12እርሷም፣ “አይሆንም፣ ወንድሜ ሆይ፣ አታስገድደኝ፤ ይህን የመሰለ ነገር በእስራኤል ሊደረግ አይገባውምና፡፡ ይህን አሳፋሪ ነገር አታድርግ፡፡
13ይሄ ነገር ከሚያስከትልብኝ ዕፍረት ለማምለጥስ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ይህም ድርጊት አንተን በመላው እስራኤል ኀፍረተ-ቢስ ጅል አድርጎ ያስቆጥርሃል፡፡ እባክህ፣ ለንጉሡ እንድትነግረው እጠይቅህሃለሁ፤ እንድታገባኝ ይፈቅድልሃል፡፡”
14ይሁን እንጂ አምኖን አልሰማትም፡፡ ከትዕማር ይልቅ ብርቱ ስለ ነበረ ይዟት ከእርሷ ጋር ተኛ፡፡
15ከዚያም አምኖን ትዕማርን ከመጠን በላይ ጠላት፤ አፍቅሯት ከነበረውም ይልቅ ጠላት፡፡ አምኖንም፣ “ተነሺ፣ ውጭልኝ” አላት፡፡
16እርሷ ግን፣ “አይሆንም፣ ምክንያቱም እኔን በማስወጣት የምታደርገው ይህ ክፉ ነገር ቀድመህ ካደረግኸው ይልቅ የከፋ ነው፡፡” አምኖን ግን እርሷን አልሰማትም፡፡
17ከዚያ ይልቅ የግል አገልጋዩን ጠርቶ፣ “ይህችን ሴት ከእኔ ዘንድ አስወጥተህ፣ በሩን ቀርቅረው” አለው፡፡
18ከዚህ በኋላ አገልጋዩ አስወጣትና በሩን ከበስተኋላዋ ቀረቀረባት፡፡ ድንግል የሆኑት የንጉሡ ሴት ልጆች እንደዚያ ይለብሱ ነበርና፣ ትዕማር በጣም ያጌጠ ቀሚስ ለብሳ ነበር፡፡
19ትዕማር በራሷ ላይ ማቅ ነሰነሰች፣ ቀሚሷንም ቀደደች፡፡ እጇንም በራሷ ላይ አድርጋ ሄደች፣ በምትሄድበትም ወቅት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አለቀሰች፡፡
20ወንድሟ አቤሴሎምም፣ “ወንድምሽ አምኖን ካንቺ ጋር ነበርን? ሆኖም፣ እህቴ ሆይ፣ አሁን ዝም በይ፡፡ ወንድምሽ ስለሆነ ነገሩን በልብሽ አትያዢው፡፡” ስለሆነም ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሆና ኖረች፡፡
21ነገር ግን ንጉሥ ዳዊት ይህንን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፤
22አቤሴሎም ለአምኖን ምንም አልተናገረውም፤ ስላደረገባት ነገር እህቱንም ትዕማርን ስላስነወራት ጠልቶት ነበርና፡፡
23ከሁለት ሙሉ ዓመት በኋላ አቤሴሎም በጎቹን በኤፍሬም አጠገብ በነበረው በቤላሶር ከተማ በጎችን የሚሸልቱ ሰዎች አስመጥቶ ነበር፤ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ወደዚያ ስፍራ ጋበዛቸው፡፡
24አቤሴሎም ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “እነሆ፣ ባሪያህ በጎችን የሚሸልቱ አስመጥቷል፣ንጉሡና አገልጋዮቹ እባክህን ከባሪያህ ጋር ይምጡ” አለው፡፡
25ንጉሡም ለአቤሴሎም፣ “ልጄ ሆይ፣ ሁላችንም መሄድ የለብንም፤ ሸክም እንሆንብሃለን” ብሎ መለሰለት፡፡ አቤሴሎም ንጉሡን አደፋፈረው፣ እርሱ ግን መሄድ ባይፈልግም አቤሴሎምን ባረከው፡፡
26ከዚህ በኋላ አቤሴሎም፣ “ይሄ ካልሆነ፣ እባክህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር ይሂድ” አለው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ አቤሴሎምን፣ “አምኖን አብሮአችሁ የሚሄደው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
27አቤሴሎም አጥብቆ ስለለመነው፣ አምኖንና የንጉሡ ልጆች አብረውት እንዲሄዱ ፈቀደ፡፡
28አቤሴሎም አገልጋዮቹን፣ “ልብ ብላችሁ አድምጡ፣ አምኖን ወይን ጠጅ ጠጥቶ መስከር ሲጀምርና እኔ ‘አምኖንን ምቱት’ ስላችሁ፣ በዚያን ጊዜ ግደሉት፤ አትፍሩ፡፡ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝና በርቱ፣ ጠንክሩ፡፡” ብሎ አዘዛቸው፡፡
29ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት፡፡ ከዚያ በኋላም የንጉሡ ልጆች በየበቅሎአቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ፡፡
30እነርሱም እየሄዱ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገደለ፣ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ዜና ለዳዊት ደረሰው፡፡
31ከዚያ በኋላ ንጉሡ ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፣ በወለሉም ላይ ተጋደመ፣ አገልጋዮቹም ልብሳቸውን ቀደው በአጠገቡ ቆሙ፡፡
32የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ ግን፣ “የሞተው አምኖን ብቻ ነውና የንጉሡ ልጆች የሆኑትን ጎልማሶች ሁሉ ገድለዋቸዋል ብሎ ጌታዬ አይመን፡፡ አምኖን እህቱን ትዕማርን ከደፈራት ቀን አንስቶ አቤሴሎም ይህንን ሲያቅድ ነበር፤
33ስለሆነም የሞተው አምኖን ብቻ ነውና፣ የንጉሡ ልጆች ሁሉ ሞተዋል ብሎ እስከሚያምን ድረስ ጌታዬ ንጉሡ የሚለውን ዜና ወደ ልቡ አያስገባው፡፡”
34አቤሴሎም ሸሸ፡፡ ለጥበቃ የቆመውም አገልጋይ ቀና ብሎ ሲመለከት ከእርሱ በስተምዕራብ ካለው ኮረብታ ጥግ ባለው መንገድ ብዙ ሰዎች ሲመጡ አየ፡፡
35በዚያን ጊዜ ኢዮናዳብ ለንጉሡ፣ “እነሆ፣ የንጉሡ ልጆች እየመጡ ነው፤ ልክ ባሪያህ እንዳለው ነው፡፡”
36ስለሆነም ተናግሮ እንደጨረሰ፣ የንጉሡ ልጆች ደረሱ፣ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፡፡ ንጉሡና አገልጋዮቹም ሁሉ አምርረው አለቀሱ፡፡
37አቤሴሎም ኮብልሎ የጌሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ፡፡ ዳዊትም ስለ ሞተው ልጁ ዘወትር ያለቅስ ነበር፡፡
38አቤሴሎም ለሶስት ዓመታት ወደ ቆየበት ወደ ጌሹር ሸሽቶ ሄደ፡፡
39በልጁ በአምኖን ሞት ከደረሰበት ሐዘን ተጽናንቶ ስለነበረ ንጉሥ ዳዊት በሃሳቡ ወደ አቤሴሎም የመሄድ ናፍቆት አደረበት፡፡