1እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፣ “በአንድ ከተማ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ድኻ ነበረ፡፡
2ባለጠጋው እጅግ ብዙ መንጋዎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤
3ድኻው ግን ከገዛትን ካሳደጋት ከአንዲት መሲና በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም፡፡ ይህች በግ ከእርሱ ጋር ኖረች ከልጆቹም ጋር አደገች፡፡ በጊቱ እንዲያውም ከእርሱ ጋር ትበላ፣ ከጽዋውም ትጠጣ ነበር፤ በእቅፉም ትተኛ ነበር፣ ለእርሱም እንደ ሴት ልጁ ነበረች፡፡
4አንድ ቀን አንድ እንግዳ ወደ ባለጠጋው ቤት መጣ፤ ባለጠጋው ግን ለእንግዳው ምግብ ለማቅረብ ከራሱ መንጋ ወይም ከቀንድ ከብቶቹ አንድ እንሰሳ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ የድኻውን መሲና ጠቦት ወስዶ ለእንግዳው ምግብ አድርጎ አዘጋጀለት፡፡”
5ዳዊትም በባለጠጋው ላይ ቁጣው ነደደ፣ በንዴትም ለናታን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!
6እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ለደኻውም ባለመራራቱ ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት፡፡”
7ከዚያ በኋላም ናታን ለዳዊት፣ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል፣ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤
8የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ብዙ ሌሎች ነገሮችንም ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር፡፡
9ስለዚህ በእርሱ ፊት ክፉ የሆነውን ታደርግ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግ ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮንን በሰይፍ ገደለህ፣ ሚስቱንም ወስደህ የራስህ ሚስት አደረግኸት፡፡ ኦርዮንን በአሞናውያን ሠራዊት ሰይፍ ገደልኸው፡፡
10እኔን አቃለኸኛልና የኬጢያዊውንም የኦርዮንን ሚስት ሚስትህ አድርገህ ወስደሃልና ሰይፍ ከቤትህ በፍጹም አይርቅም፡፡’
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘ከራስህ ቤት ጥፋት አስነሳብሃለሁ፤ ዓይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለጎረቤትህ እሰጠዋለሁ፣ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል፡፡
12አንተ ኃጢአትህን በስውር እኔ ግን ይህንን ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ፡፡’”
13ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” አለው፡፡ ናታንም ለዳዊት መለሰለት፣ “እግዚአብሔር ኃጢአትህን አስወግዶልሃል፡፡ አንተ አትሞትም፤
14ይሁን እንጂ በዚህ ድርጊትህ እግዚአብሔርን ስላቃለልህ የተወለደልህ ልጅ በእርግጥ ይሞታል፡፡”
15ከዚያ በኋላ ናታን ወጥቶ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ እግዚአብሔርም የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ እግዚአብሔር አስጨነቀው እጅግም ታመመ፡፡
16ዳዊት ስለ ልጁ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ ሌሊቱን ወለሉ ላይ ተኝቶ አደረ፡፡
17የቤተሰቡ ሽማግሌዎችም ከወለሉ ላይ ያነሱት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፣ እርሱ ግን አልተነሳም፣ ከእነርሱም ጋር አልበላም፡፡
18በሰባተኛውም ቀን ልጁ ሞተ፡፡ “እነሆ፣ ልጁ ገና በሕይወት ሳለ ስናነጋግረው ድምፃችንን አልሰማንም፣ ታዲያ፣ ልጁ ሞቶአል ብንለው በራሱ ላይ ምን ያደርግ ይሆን?!” ብለው ስለነበረ፣ የዳዊት አገልጋዮች ልጁ እንደ ሞተ ለመንገር ፈርተው ነበር፡፡
19ነገር ግን እርስ በርሳቸው ሲንሾካሾኩ ዳዊት በተመለከተ ጊዜ፣ ልጁ እንደ ሞተ ዳዊት ተገነዘበ፤ ለአገልጋዮቹም፣ “ልጁ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፣ “ሞቶአል” ብለው መለሱለት፡፡
20ከዚያም ዳዊት ከወለሉ ላይ ተነስቶ ታጠበ፣ ቅባት ተቀባ ደግሞም ልብሱን ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤትም ሄዶ አምልኮ አቀረበ፣ ከዚያ በኋላም ወደ ራሱ ቤተ መንግሥት ተመለሰ፡፡ ምግብ እንዲያቀርቡለት በጠየቀ ጊዜ አቀረቡለት፣ እርሱም በላ፡፡
21ከዚያ በኋላ አገልጋዮቹ፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ልጁ በሕይወት እያለ ጾምህ አለቀስህም፤ ልጁ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” አሉት፡፡
22ዳዊትም፣ “ልጁ ገና በሕይወት ሳለ ጾምሁ አለቀስሁም፤ ‘ልጁ በሕይወት ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ቸርነት ያደርግልኝ እንደሆነ ማን ያውቃል’ ብዬ ነበር፡፡
23አሁን ግን፣ እርሱ ሞቶአልና ለምን እጾማለሁ? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም፡፡”
24ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፡፡ ከዚህም የተነሣ ወንድ ልጅ ወለደች፣ ልጁም ሰሎሞን የሚል ስም ተሰጠው፤ እግዚአብሔርም ወደደው፡፡
25ስለሆነም እግዚአብሔር ስለወደደው ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ፡፡
26በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያን የንጉሥ ከተማ የነበረችውን ረባትን ወግቶ ምሽጉን ያዘ፡፡
27ስለሆነም ኢዮአብ ወደ ዳዊት መልእክተኞችን በመላክ እንዲህ አለው፣ “ረባትን ወግቼ የከተማይቱን የውሃ ማከፋፈያ ይዤአለሁ፡፡
28እንግዲህ አሁን፣ የቀረውን ሠራዊት አሰባስበህ በከተማይቱ ዙሪያ ሠፍረህ ያዛት፤ ምክንያቱም እኔ ከተማይቱን ከያዝኳት በስሜ መጠራቷ ነው፡፡”
29ስለዚህ ዳዊት መላውን ሠራዊት አሰባስቦ ወደ ረባት ሄዶ ከተማይቱን ወግቶ ያዛት፡፡
30ዳዊት ከሞሎክ ራስ ላይ ዘውዱን ወሰደ፤ የዘውዱም ክብደት አንድ መክሊት ወርቅ ሲሆን የከበረ ዕንቁም በላዩ ላይ ነበረበት፡፡ ዘውዱም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ፡፡ ከዚያም እጅግ ብዙ የከተማይቱን ምርኮ አመጣ፡፡
31በከተማይቱ የነበሩትንም ሰዎች አውጥቶ በመጋዝ፣ በብረት መቆፈሪያና በመጥረቢያ እንዲሠሩ አስገደዳቸው፤ የሸክላ ጡብም እንዲሠሩ አደረጋቸው፡፡ ዳዊት የአሞን ሕዝብ ከተሞች ሁሉ ይህንኑ ተግባር እንዲፈጽሙ አደረጋቸው፡፡ ከዚያም ዳዊትና ሠራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡