1ነገሥታት ወደ ጦርነት መውጣታቸው የተለመደ በነበረበት በፀደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን፣ አገልጋዮቹንና መላውን የእስራኤል ሠራዊት ወደ ዘመቻ ላካቸው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ረባትንም ከበቡአት፡፡ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀረ፡፡
2ከዚህም የተነሣ በአንድ የምሽት ወቅት ዳዊት ከዐልጋው ተነስቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ በዚያም ስፍራ ሆኖ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች፡፡
3ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ የሚያውቁ ሰዎችን አጠያየቀ፡፡ አንድ ሰውም፣ “ይህች የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮን ሚስት አይደለችምን?”
4ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፣ (ከወር አበባ ጊዜዋ የነጻችበት ወቅት ነበርና) አብሮአት ተኛ፡፡ ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች፡፡
5ሴቲቱ ፀነሰች፣ “አርግዣለሁ” ብላም ወደ ዳዊት መልእክት ላከችበት፡፡
6ከዚያ በኋላም ዳዊት ለኢዮአብ፣ “ኬጢያዊውን ኦርዮንን ወደ እኔ ላክልኝ” ብሎ መልእክት ላከበት፡፡ ስለዚህም ኢዮአብ ኦርዮንን ወደ ዳዊት ላከው፡፡
7ኦርዮን በደረሰ ጊዜ ኢዮአብና ሠራዊቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው፡፡
8ዳዊትም ለኦርዮን፣ “ወደ ቤትህ ሄደህ እግርህን ተታጠብ” አለው፡፡ ኦርዮንም ከቤተ መንግሥቱ ወጣ፣ ንጉሡም ኦርዮን ከወጣ በኋላ ስጦታ አስከትሎ ላከለት፡፡
9ኦርዮን ግን ከጌታው አገልጋዮች ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጥር በር ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር፡፡
10ለዳዊት “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” ብለው በነገሩት ጊዜ፣ ዳዊት ኦርዮንን፣ “ከመንገድ መግባትህ አይደለምን? ለምን ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡
11ኦርዮም ዳዊትን፣ “ታቦቱ፣ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፣ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም አገልጋዮች ገላጣ ሜዳ ላይ ሰፍረው፤ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? እንዲህ ያለውን ነገር እንደማላደርገው በነፍስህ እምላለሁ፡፡” አለው፡፡
12ከዚህም የተነሣ ዳዊት ለኦርዮ፣ “ዛሬ ደግሞ በዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው፡፡ ስለዚህ ኦርዮ በዚያ ዕለትና በማግሥቱ እዚያው ኢየሩሳሌም ቆየ፡፡
13ዳዊትም ባስጠራው ጊዜ በእርሱ ፊት በላ ደግሞም ጠጣ፣ ዳዊትም እንዲሰክር አደረገው፤ ሲመሽም ኦርዮን በአልጋው ላይ ለመተኛት የጌታው አገልጋዮች ወዳሉበት ሄደ፣ ወደ ቤቱ ግን አልሄደም፡፡
14ስለዚህ በማግስቱ ሲነጋ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፡፡
15በደብዳቤውም ውስጥ ዳዊት፣ “ኦርዮንን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም እንዲመታና እንዲሞት ከኋላው አፈግፍጉ” ብሎ ጻፈ፡፡
16ስለዚህ ኢዮአብ የከተማይቱን መከበብ እየተመለከተ ሳለ ጠንካሮቹ የጠላት ሠራዊት እየተዋጉ እንዳሉ በሚያውቅበት ግንባር ኦርዮንን መደበው፡፡
17የከተማይቱ ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት በገጠሙበት ጊዜ ከዳዊት ወታደሮች ጥቂቶቹ ሞቱ፣ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮንም በዚያ ሞተ፡፡
18ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት በላከበት ጊዜ፣
19መልእክተኛውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፣ “ጦርነቱን በሚመለከት ሁሉንም ነገር ለንጉሡ ከጨረስክ በኋላ፣
20ምናልባት ንጉሡ ይቆጣና፣ ‘ለመዋጋት ስትሉ ወደ ከተማይቱ ይህን ያህል የተጠጋችሁት ስለምንድን ነው? በግንቡ ቅጥር ላይ ሆነው ፍላፃ እንደሚወርውሩባችሁ አታውቁም ኖሮአል?
21የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ እንዲሞት ያደረገችው አንዲት ሴት ከግንቡ ላይ የወፍጮ መጅ ስለለቀቀችበት አይደለምን? ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ይልህ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቶአል’ ብለህ ንገረው፡፡”
22ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ወደ ዳዊት ዘንድ ሄደ፣ ኢዮአብ እንዲናገር የላከውን ማንኛውንም ነገር ነገረው፡፡
23መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፣ “እኛ በመጀመሪያ ከነበረው ይልቅ ጠላት በርትቶ ነበር ወደ ሜዳው ወደ እኛ ዘንድ መጡ፤ እኛም እስከ ቅጥሩ መግቢያ በር ድረስ አሳድደን መለስናቸው፡፡
24የእነርሱም ባለ ፍላጻዎች ከግንቡ ላይ ሆነው በወታደሮችህ ላይ ቀስት ወረወሩ፣ ከንጉሡ አገልጋዮችም ጥቂቶችን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ፡፡”
25ከዚያ በኋላ ዳዊት ለመልእክተኛው፣ “ለኢዮአብ፣ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፣ ሌላ ጊዜም ሌላውን ይበላልና ይህ አያሳዝንህ፡፡ በከተማይቱ ላይ ውጊያህን አጠናክረህ አፍርሳት፡፡’ በለው፣ ኢዮአብን አበረታታው፡፡”
26ስለዚህ የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ አምርራ አለቀሰችለት፡፡
27የሐዘኗም ጊዜ ካበቃ በኋላ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ ወሰዳት፣ ሚስቱም ሆነች፣ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር እግዚአብሔርን አሳዘነው፡፡