1ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፣ ልጁ ሐኖንም በእርሱ ምትክ ንጉሥ ሆነ፡፡
2ዳዊትም፣ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ ሁሉ እኔን ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነትን አደርግለታለሁ፡፡” አለ፡፡ ስለዚህ በአባቱ ምክንያት ከደረሰበት ኃዘን ያጽናኑት ዘንድ ዳዊት አገልጋዮቹን ላከ፡፡ አገልጋዮቹም ወደ አሞን ምድር ገቡ፡፡
3የአሞን ሕዝብ መሪዎች ግን ለጌታቸው ለሐኖን እንደዚህ አሉት፣ “አንተን እንዲያጽናኑ ሰዎቹን በመላኩ ዳዊት በእርግጥ አባትህን በማክበር ነው ብለህ ታስባለህን? ዳዊት ሰዎቹን የላከው ከተማይቱን እንዲመለከቱና ያጠፏትም ዘንድ እንዲሰልሏት አይደለምን?”
4ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፤ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም እስከ ቂጣቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ሰደዳቸው፡፡
5ይህንን ለዳዊት በገለጹለት ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበርና መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላከ፡፡ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቆዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው፡፡
6የአሞን ሰዎች ለዳዊት መጥፎ ጠረን እንዳላቸው ሰዎች እንደሆኑበት ባወቁ ጊዜ የአሞን ሰዎች መልእክተኞችን ልከው ከቤትሮዖብና ከሱባ ሃያ ሺህ አራማውያን እግረኛ ወታደሮችን፣ ከንጉሥ መዓካ አንድ ሺህ ሰዎችን ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎችን ቀጠሩ፡፡
7ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን ከመላው ተዋጊ ሠራዊት ጋር ላከው፡፡
8አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ሲሰለፉ፤ የሱባና የረአብ አራማውያን ሰዎች ለብቻቸው ሜዳው ላይ ቆሙ፡፡
9ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል በጀግንነታቸው ከታወቁት ጥቂቶቹን መርጦ በአራማውያን ግንባር አሰለፋቸው፡፡
10የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ሠራዊት ግንባር አሰለፋቸው፡፡
11ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ “አራማውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ፡፡
12እንግዲህ በርታ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ጠንካሮች መሆናችንን እናስመስክር፤ እግዚአብሔርም ለዓላማው መልካም መስሎ የታየውን ያደርጋል፡፡”
13ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ከእስራኤል ሠራዊት ፊት እንዲሸሹ ወደ ተገደዱት ወደ አራማውያን በመገሥገሥ ወደ ጦርነቱ ሄዱ፡፡
14አራማውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማይቱ ውስጥ ገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ከአሞናውያን ሕዝብ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡
15አራማውያን በእስራኤላውያን እየተሸነፉ እንደሆኑ ባዩ ጊዜ እንደ ገና ተሰባሰቡ፡፡
16አድርአዛር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ወደነበሩት ወደ አራማውያን ሠራዊት መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም በአድርአዛር ሠራዊት አዛዥ በሶባክ መሪነት ወደ ዔላም መጡ፡፡
17ይሄ ነገር ለዳዊት በተነገረው ጊዜ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ፡፡ አራማውያን ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን ገጠሙት ተዋጉትም፡፡
18አራማውያን ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ሰባት መቶ ሠረገለኞችንና አርባ ሺህ ፈረሰኞችን ገደለ፡፡ የሠራዊቱ አዛዥ ሶባክም ቆስሎ በዚያ ሞተ፡፡
19የአድርአዛር አገልጋዮች የነበሩት ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም መሠረቱ ተገዙላቸውም፡፡ ስለዚህም ሶርያውያን ከዚያ በኋላ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ፡፡