መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ጴጥሮስ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሐሰተኞች ነቢያት በእስራኤላውያን መካከል ነበሩ፤ በእናንተ መካከል ደግሞ ሐሰተኞች መምህራን ይኖራሉ፤ እነርሱ ጥፋትን የሚያስከትል ሐሰተኛ ትምህርት በስውር ያስገባሉ፤ የዋጃቸውንም ጌታ ክደው ፈጣን ጥፋትን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ። ብዙዎች የእነርሱን መዳራት ይከተላሉ።
2ከእነርሱም አድራጎት የተነሣ የእውነት መንገድ ይሰደባል።
3እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ለገንዘብ ከመስገብገባቸው የተነሣ የሚያታልሉ ቃላትን በመጠቀም ይበዘብዙአችኋል። በእነርሱ ላይ ያለው ፍርድ አይዘገይም፤ መጥፊያቸውም የራቀ አይደለም።
4እግዚአብሔር ኀጢአት የሠሩትን መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሐነም ከጣላቸውና በሰንሰለት አስሮ እስከ ፍርድ ጊዜ ድረስ በጨለማ ውስጥ ካስቀመጣቸው፣
5የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ለጥንቱ ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ካመጣ፣
6ደግሞም ኀጢአት በሚያደርጉ ሁሉ ላይ የሚመጣው ጥፋት ምሳሌ እንዲሆኑ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ ከፈረደባቸው፣
7በሕገ ወጦች ሴሰኝነት ነፍሱ እየተጨነቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን ግን አዳነው፤
8ያ ጻድቅ ሰው በመካከላቸው ሲኖር በየቀኑ ያየውና ይሰማው በነበረው ሕገ ወጥ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱ ትጨነቅ ነበር።
9ጌታ፣ እግዚአብሔርን የሚመስሉትን ሰዎች ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል።
10በተለይም ብልሹ የሥጋ ምኞታቸውን የሚከተሉትንና ሥልጣንን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል። እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና እብሪተኞች ስለ ሆኑ የከበሩትን ሲሳደቡ አይፈሩም፤
11መላእክት ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ብርታትና ችሎታ ያላቸው ሆነው ሳሉ፣ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ ዘለፋ ያዘለ የፍርድ ቃል አይሰነዝሩም።
12እነዚህ አእምሮ እንደ ጎደላቸው እንስሳት ለምርኮና ለጥፋት የተፈጠሩ ናቸው፤ የሚሳደቡትን ስለማያውቁ ይጠፋሉ።
13እነርሱ የዐመፃቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ በቀን በመስከርና ያለ ልክ በመፈንጠዝ ይኖራሉ ፤ እነርሱ አሳፋሪዎችና ነውረኞች ናቸው። ከእናንተ ጋር ግብዣ ላይ ሲገኙ፣ በአታላይ ፈንጠዝያቸው ሐሴት ያደርጋሉ።
14ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት ከቶ አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ሰዎች ያስታሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ልጆች ናቸው።
15ቀናውን መንገድ ትተው፣ በክፉ ሥራ የሚገኘውን ገንዘብ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ስተዋል፤
16እርሱ ስለ መተላለፉ ተገሥጾአል፤ መናገር የማይችል አህያ በሰው ቋንቋ ተናግሮ የነቢዩን እብደት አስቍሟልና።
17እነዚህ ሰዎች እንደ ደረቁ ምንጮችና በዐውሎ ነፋስ እንደሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ የሚጠብቃቸውም ድቅድቅ ጨለማ ነው፤
18ፍሬ ቢስ የዕብሪት ቃል በመናገር፥ በሥጋዊ ፍትወታቸው ሰዎችን ያጠምዳሉ፤ ከተሳሳተና ከብልሹ የሕይወት ዘይቤ ለማምለጥ የሚሞክሩትን ሰዎች ያጠምዳሉ።
19እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለሚሸነፍለት ለማንኛውም ነገር ባሪያ ነውና።
20ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ፣ እንደ ገና ወደ ቀደሞው የርኵሰት ሕይወት ቢመለሱ፣ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው የከፋ ይሆንባቸዋል።
21የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባያውቋት ይሻላቸው ነበር።
22«ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል» እንዲሁም «ዐሣማ ቢታጠብም ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል» የሚለው ምሳሌ እውን ይሆንባቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።