1ወዳጆች ሆይ! ይህን ሁለተኛ መልእክት የምጽፍላችሁ፣ ቅን ልቦናችሁን ለማነቃቃት ነው፤
2ደግሞም አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያቶቻችሁ አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስታውሱ ነው።
3በቅድሚያ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻዎቹ ቀኖች የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱባችሁ ይመጣሉ።
4እነርሱም፣ «የመምጣቱ ተስፋ ወዴት አለ? አባቶቻችን ሞተዋል፤ ከፍጥረት መጀመሪያም አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል» ይላሉ።
5እነዚህ ሰዎች ሰማያትና ምድር ከብዙ ዘመን በፊት በእግዚአብሔር ቃል ከውሃና በውሃ አማካይነት መፈጠራቸውን ፣ ሆን ብለው ይክዳሉ፤
6በቃሉና በውሃ እማካይነት በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ።
7ደግሞም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል።
8ወዳጆች ሆይ፤ ፤በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አትዘንጉ ።
9አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዳችሁም እንድትጠፉ ስለማይፈልግና ሰው ሁሉ በቂ የንስሓ ጊዜ እንዲያገኝ ፈልጎ ስለ እናንተ ይታገሳል።
10ይሁን እንጂ የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይቃጠላል፤ በምድርና በእርሷም ውስጥ በተሠራው ነገር ሁሉ ላይ ይፈረድበታል።
11እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፣ ታዲያ እናንተ በቅድስናና እግዚአብሔርን በመምሰል ሕይወት ለመኖር እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል?
12ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት የምትጠባበቁና የምታፋጥኑ ሁኑ፤ በዚያን ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ ፍጥረታትም በእሳት ግለት ይቀልጣሉ፤
13እኛ ግን እርሱ በሰጠን ተስፋ መሠረት፣ ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን።
14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ነገሮች የምትጠባበቁ እንደ መሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ ከእርሱም ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ።
15እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ በተሰጠው ጥበብ መጠን እንደ ጻፈላችሁ፤ የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደ ሆነ አስቡ፤ ምንም እንኳ በመልእክቶቹ ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች ቢኖሩም፣
16ጳውሎስ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፎአል፤ ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህም ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
17እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ ጽኑ መሠረታችሁን እንዳትለቅቁ ተጠንቀቁ።
18ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን፤ አሜን!