1ነቢዩ ኤልሳዕም ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለ፡- «በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ሬማት ለመሄድ ተዘጋጅ፤ ይህንንም የዘይት ማሰሮ ያዝ፡፡
2እዚያም በደረስህ ጊዜ የኢዮሳፍጥ ልጅ የናሜሲ ልጅ የሆነውን ኢዩን ፈልግ፤ እርሱንም ከጓደኞቹ በመለየት ወደ ውስጥ አስገባው፡፡
3ይህን የወይራ ዘይት በራሱ ላይ አፍስስበትና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ‹አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ» ብለህ ንገረው አለው፡፡ ከዚያም በሩን ከፍተህ ከዚያ ስፍራ ተነሥተህ ሽሽ፤ አትዘገይም፡፡»
4ስለዚህም ወጣቱ ነቢይ ወደ ሬማት ሄደ፡፡
5እዚያም በደረሰ ጊዜ የጦር አዛዦች ተቀምጠው ነበር፡፡ ወጣቱም ነቢይ እንዲህ አለ፡- «ጌታዬ የምነግርህ መልእክት አለኝ» አለው፡፡ ኢዩም፡ «ለማናችን ነው የምትነግረው?» ሲል ጠየቀው፡፡ ወጣቱም ነቢይ፡- «የምናገረው ለአንተ ነው ጌታዬ» ሲል መለሰለት፡፡
6ስለዚህ ኢዩ ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ወጣቱ ነቢይም ዘይቱን በኢዩ ራስ ላይ አፈሰሰበትና እንዲህ አለው፡- «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረው ይህ ነው፡- ‹በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ፡፡
7አንተም የአክዓብን የጌታህን ቤተ ሰብ መግደል አለብህ፤ በዚህም በኤልዛቤል የተገደሉትን፣ የአገልጋዮቼን የነቢያቴንና የእግዚአብሔር አገልጋዮችን ደም በሙሉ እበቀላለሁ፡፡
8መላው የአክዓብ ቤተ ሰብና ትውልዱ ሁሉ ይጠፋሉ፤ ከእርሱ ቤተ ሰብ ወንድ የሆነውን ማንኛውንም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አጠፋለሁ፡፡
9የእስራኤል ነገሥታት በነበሩት በናባጥ ልጅ በኢዮርብአምና በአኪያ ልጅ በባኦስ ቤተሰቦች ላይ ያደርግኹትን ሁሉ በአክዓብ ቤተ ሰብ ላይ እፈፅማለሁ፡፡
10ኤልዛቤል የመቀበር ዕድል እንኳ አታገኝም፤ የኤልዛቤልን ሬሳ በኢይዝራኤል ከተማ ውሾች ይበሉታል፤ ማንም አይቀብራትም፡፡» ከዚያም ወጣቱ ነቢይ በሩን ከፍቶ ከዚያ ክፍል ወጥቶ ሸሸ፡፡
11ከዚያም ኢዩ ወደ ንጉሡ አገልጋዮች በመጣ ጊዜ አንዱ፡- «ሁሉ ነገር ሰላም ነውን? ለመሆኑ ይህ እብድ ወደ አንተ ለምን መጣ?» ሲሉ ጠየቁት፡፡ ኢዩም «ሰውየውንም ሆነ እርሱ የሚናገረውን እናንተ ታውቁታላችሁ» አላቸው፡፡
12እነርሱም «ይህ ሐሰት ነው፡፡ አንተ ንገረን» ሲሉ መለሱለት፡፡ ኢዩም፡- «በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር ቀብቼሃለሁ»› አለኝ ሲል አስረዳቸው፡፡
13ከዚያም እነርሱ ወዲያውኑ ልብሳቸውን እያወለቁ ኢዩ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፡፡ በዚያም ላይ እንዲቆም አድርገው እምቢልታ ነፉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው «ኢዩ ንጉሥ ነው!» ሲሉ ጮኹ፡፡
14በዚህ ሁኔታ የኢዮሳፍጥ ልጅ የናሜሲ ልጅ ኢዩ በንጉሥ ኢዮራም ላይ ሤራ ማካሄድ ጀመረ፡፡ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ አዛሄል ጋር በሬማት ገለዓድና እስራኤል በሙሉ ሲከላከሉ፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ በኢይዝራኤል ውስጥ በማገገም ላይ ነበር፡፡
15ስለዚህም ኢዩ የጦር መኮንኖች «እናንተ በእርግጥ ከእኔ ጋር ከሆናችሁ በኢይዝራኤል የሚኖረውን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ አንድ ወሬ ከሬማት ወጥቶ እንዳያመልጥ አድርጉ» አላቸው፡፡
16ከዚህም በኋላ ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮራም ገና ከቁስሉ አልዳነም ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ሊጠይቀው መጥቶ በዚያ ነበር፡፡
17በኢይዝራኤል ከተማ መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ጠባቂ ኢዩና ተከታዩ ጭፍራ ሲመጡ ከሩቅ አይቶ «ሰዎች እየጋለቡ በቡድን ሲመጡ አያለሁ!» አለ፡፡ ኢዮራምም «አንድ ፈረሰኛ ልከህ የሚመጡትን ሰዎች ሰላም ነውን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርግ» አለው፡፡
18መልእክተኛውም ጋልቦ ሄዶ ኢዩን፡- «ንጉሡ አመጣጥህ በሰላም ነውን?» ይልሃል ሲል ጠየቀው፡፡ ኢዩም፣ «አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!» ሲል መለሰለት፡፡ ከዚያም ጠባቂው፡- «መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም» ሲል ለንጉሡ ነገረው፡፡
19ሌላም መልእክተኛ ተልኮ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ለኢዩ አቀረበለት፡፡ ኢዩም፡- «አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!» ሲል መለሰለት፡፡
20ጠባቂውም እንደገና፡- «እርሱ ተገናኝቶአል ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም» አለ፡፡ ‹ምክንያቱም የሠረገላ አነዳዱ እንደ እብድ ሰው እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ ነው! ልክ ኢዩን ይመስላል!» ሲል ተናገረ፡፡
21ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፡- «ሠረገላ አዘጋጁልኝ» አለ፡፡ ሠረገላውም ተዘጋጅቶለት ኢዮራም የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየግል ሠረገላችው እየጋለቡ ኢዩን ሊገናኙት ወጡ፡፡ እነርሱም ኢዩን የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ አገኙት፡፡
22ኢዮራምም፡- «ኢዩ ሆይ አመጣጥህ በሰላም ነውን?» ሲል ጠየቀ፡፡ ኢዩም፡- «የእናትህ የኤልዛቤል የአመንዝራይቱ ጣዖትና ጥንቆላ ሥራ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ?» ሲል መለሰለት፡፡
23በመሆኑም ኢዮራም፡- «አካዝያስ ሆይ! ይህ ክሕደት ነው!» እያለ ሠረገላውን መልሶ ሸሸ፡፡
24ኢዩ ቀስቱን ስቦ ባለው ኀይል ሁሉ ፍላጻውን ባስፈነጠረ ጊዜ ኢዮራምን ወግቶ በትከሻዎቹ መካከል ወደ ልቡ ዘለቀ፤ ኢዮራምም ሞቶ በሠረገላው ውስጥ ወደቀ፡፡
25ኢዩም ቢድቃር ተብሎ የሚጠራውን የጦር አዛዥ «ሬሳውን አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ ወርውረህ ጣለው አለው፡፡ እኔና አንተ የንጉሥ ኢዮራም አባት ከነበረው ከአክዓብ በስተኋላ እየጋለብን ስንሄድ እግዚአብሔር በአክዓብ ላይ የተናገረውን ቃል አስታውስ፡፡
26‹ትናንትና የናቡቴንና የልጆቹን መገደል አየሁ፤ በዚሁ እርሻ ላይ እንደምቀጣህ እምላለሁ› የሚል ነበር፡፡» ስለዚህ ኢዩ «እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይፈፀም ዘንድ የኢዮራምን ሬሳ አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ በመወርወር ጣለው» ሲል የጦር አዛዡን አዘዘው፡፡
27የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ይህን ባየ ጊዜ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ቤት ሀጋን ከተማ ሸሸ፡፡ ኢዩ ተከታትሎ እያሳደደው «እርሱንም ደግሞ በሠረገላው ውስጥ ግደሉት» አለ፡፡ እነርሱም ተከታትለው በኢዮርብዓም ከተማ አጠገብ በጉር በሠረገላው ሳለ ወጉት፤ አካዝያስም ወደ መጊዶ ከተማ ሸሸ፤ በዚያም ሞተ፡፡
28አገልጋዮቹም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደው በዳዊት ከተማ በሚገኘው በአባቶቹ መካነ መቃብር ቀበሩት፡፡
29አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር፡፡
30ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል በደረሰ ጊዜ፣ ኤልዛቤል ይህን ሰምታ ዐይንዋን ተኳለች፤ ጠጉርዋንም ተሠርታ በመስኮት ትመለከት ነበር፡፡
31ኢዩም የቅጥሩን በር አልፎ ሲገባ «አንተ ዘምሪ! አንተ የጌታህ ገዳይ፣ እዚህ ደግሞ የመጣሃው በሰላም ነውን?» አለችው፡፡
32ኢዩ ቀና ብሎ ወደ ላይ በመመልከት፡- «ከእኔ ጋር የሚተባበር ማን ነው?» አለ፡፡ ቁጥራቸው ሁለት ወይም ሦስት የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በመስኮት ወደ እርሱ ተመለከቱ፡፡
33ኢዩም «ኤልዛቤልን ወደ ታች ወርውሯት!» አላቸው፡፡ እነርሱም አንሥተው በወረወሯት ጊዜ ደምዋ በግንቡና በፈረሶች ላይ ተረጨ ኢዩም ሬሳዋን በፈረስና ሠረገላው ረጋገጠ፡፡
34ኢዩም ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ተመገበ፤ ጠጣም፡፡ ከዚያም «የንጉሥ ልጅ ነችና ያችን የተረገመች ሴት ቅበሩአት» አለ፡፡
35ሊቀብሩዋት የሄዱ ሰዎች ግን ከራስ ቅልዋ፣ ከእግሮችዋና ከእጆችዋ መዳፍ በቀር ምንም አላገኙም፡፡
36ይህንንም ለኢዩ በነገሩት ጊዜ ኢዩ እንዲህ አለ፤ «ይህ ሁሉ የተፈፀመው እግዚአብሔር በአገልጋዩ በቴስቢያዊው በኤልያስ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው፤ ይኸውም ‹የኤልዛቤልን ሬሳ በኢይዝራኤል ውሾች ይበሉታል፡፡
37ከሬሳውም የሚተርፈው እንደ ፍግ በዚያ ይበተናል፤ ስለዚህም ማንም እርሷነቷን ለየቶ በማወቅ፡- ይህች ኤልዛቤል ናት ሊል አይችልም፡፡»