1ኤልሳዕም ልጅዋን ከሞት ያስነሣላትን፣ በሱነም የነበረችውን ሴት አስቀድሞ እንዲህ ሲል ነግሮአት ነበር፡- እግዚአብሔር እስከ ሰባት ዓመት የሚቆይ ራብ በዚህች ምድር ላይ ልኮአል፤ ከቤተ ሰብሽ ጋር በሕይወት ለመትረፍ ከዚህ ተነሥተሽ ወደ ሌላ ስፍራ ሂጂ፡፡
2ስለዚህም የኤልሳዕን ምክር ሰምታ ከነቤተ ሰብዋ ወደ ፍልስጥኤም አገር በመሰደድ እስከ ሰባት ዓመት ቆየች፡፡
3ሴቲቱም ከሰባቱ የራብ ዓመቶች ፍፃሜ በኋላ ከፍልስጥኤም አገር ተመልሳ መጣች፤ ስለ መኖሪያ ቤትዋና ስለ እርሻ መሬትዋ ለመጠየቅ ወደ ንጉሡ ሄደች፡፡
4ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ ከግያዝ ጋር፡- «ኤልሳዕ ስላደረጋቸው ታላላቅ ነገሮች ንገረኝ» እያለ ይነጋገር ነበር፡፡
5ግያዝም ኤልሳዕ እንዴት የሞተውን ሕፃን እንዳስነሣው ለንጉሡ እየነገረ እያለ ኤልሳዕ ሕፃኑን ከሞተ ያስነሣላት ሴት ንጉሡን ስለ መኖሪያ ቤትዋና ስለ እርሻ መሬቷ ለመጠየቅ መጣች፡፡ ግያዝም እንዲህ አለ፡- «ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሴቲዮዋ እነሆ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጅዋም ይሄ ነው!»
6ንጉሡም ሴቲቱን ስለ ሕፃኑ በጠየቃት ጊዜ በሚገባ አስረዳችው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ አንዱን ባለሥልጣን ስለ እርስዋ እንዲህ ሲል አዘዘ፡- የእርስዋ የሆነውን ማናቸውንም ነገርና የእርሻ መሬትዋን ከሰባት ዓመት ጀምሮ አገሩን ከለቀቀችበት እስካሁን ያለውን ሰብል ጭምር እንዲመልስላት አዘዘው፡፡
7የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ በታመመ ጊዜ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፡፡ ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው መምጣቱን ሰማ፡፡
8ንጉሡም አዛሄልን፡- «በእጅህ አንድ ስጦታ ይዘህ ወደ እግዚአብሔር ሰው ሂድና ከዚህ ሕመም እድናለሁን? ብለህ ጠይቅ አለው፡፡
9ስለዚህ አዛሄል በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ የምድር በረከት ሁሉ በአርባ ግመሎች ጭኖ ወደ ኤልሳዕ ሄደ፡፡ አዛሄልም መጥቶ በኤልሳዕ ፊት ቆመና፡- «ልጅህ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ከሕመሙ ይድን እንደሆነ እንድትነግረው እጠይቅህ ዘንድ ልኮኛል» አለው፡፡
10ኤልሳዕም፡- «ቤን ሀዳድን አንተ በርግጥ ትድናለህ ብለህ ንገረው፣ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል፤» አለው፡፡
11ከዚያም ኤልሳዕ ፊቱን በማጥቆር ትኩር ብሎ እስኪያፍር ድረስ አዛሄልን ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው እንባውን ማፍሰስ ጀመረ፡፡
12አዛሄልም፡- «ጌታዬ ስለምን ታለቅሳለህ?» ሲል ጠየቀው፡፡ ኤልሳዕም፡- «በእስራኤል ሕዝብ ላይ የምትፈፅመውን አሰቃቂ ነገር ስለማውቅ ነው፡፡ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ወጣቶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናቶቻቸውን በድንጋይ ትከሰክሳለህ፤ የእርጉዞች ሴቶችንም ሆድ ትሰነጥቃለህ» ሲል መለሰለት፡፡
13አዛሄልም፡- «ይህን ታላቅ ነገር የሚያደርግ አገልጋይህ ማን ሆኖ ነው? ይህ ሰው ውሻ ብቻ ነው ሲል ጠየቀው፡፡ ኤልሳዕም፡- «አንተ የሶርያ ንጉሥ እንደምትሆን እግዚአብሔር ገልጦልኛል» ሲል መለሰለት፡፡
14ከዚያም አዛሄል ተመልሶ ወደ ጌታው ወደ ንጉሡ መጣ፡፡ «ኤልሳዕ ምን አለህ?» ሲል ቤን ሀዳድ ጠየቀው፡፡ አዛሄልም፡- «አንተ በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል» ሲል መለሰለት፡፡
15ነገር ግን በማግስቱ አዛሄል ብርድ ልብስ ወስዶ ውሃ ውስጥ ነከረ፤ ከዚያም በቤን ሀዳድ ፊት ወረወረውና ታፍኖ ሞተ፡፡ አዛሄልም በቤን ሀዳድ ፈንታ ተተክቶ የሶርያ ንጉሥ ሆነ፡፡
16የእስራኤል ንጉሥ የአክአብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት ኢዮራም በይሁዳ መንገሥ ጀመረ፡፡ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ነበር፡፡
17እርሱም በነገሠ ጊዜ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበር፡፡ መቀመጫውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ነገሠ፡፡
18ሚስቱም የአክዓብ ልጅ ስለነበረች የእስራኤል ነገሥታት ይፈፅሙት የነበረውን እንደ አክዓብ ቤተ ሰብ የክፋት መንገድ ተከተለ፡፡ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፡፡
19ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዘሩ መንግሥታትን እንደማያጠፋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ተስፋ ሰጥቶት ስለ ነበር ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፡፡
20በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐመፀ፤ ለራሳቸውም ንጉሥ አነገሡ፡፡
21ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን በመላ አሰልፎ ወደ ጸዒር ዘመተ፡፡ የኤዶም ሠራዊትም ኢዮራምን በከበቡ ጊዜ፤ በሌሊት ተነሥተው የሠረገሎቹን አዛዦች አጠቁአቸው፤ ነገር ግን የኢዮራም ሠራዊት ሮጠው ወደየቤታቸው ተበታተኑ፡፡
22ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኤዶም በይሁዳ አገዛዝ ላይ አመፁ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም የልብና ከተማ አመፀች፡፡
23ኢዮራም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ የነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
24ኢዮራም ሞተ፤ በዳዊት ከተማም በሚገኘው በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ ከዚያም አካዝያስ በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ነገሠ፡፡
25የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
26አካዝያስ በነገሠ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት ነበረ፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም አንድ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱ ጎቶልያ ተብላ የምትጥራው የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች፡፡
27አካዝያስ የንጉሥ አክዓብን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፡፡ ምክንያቱም አካዝያስ የንጉሥ አከዓብን ልጅ ስለሚያገባ ነበር፡፡
28አካዝያስም ከንጉሥ አከዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር ለመዋጋት ወደ ራሞት ገለዓድ ዘመተ፡፡ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቆሰሉት፡፡
29ኢዮራምም ከሶሪያ ንጉሥ አዛሄል ጋር በሬማት በተደረገው ጦርነት የደረሰበትን ቁስሉን ለመታከም ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ተመለሰ፡፡ ስለዚህ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የአከዓብ ልጅ ኢዮራም ስለደረሰበት ጉዳት ለመጠየቅ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ሄደ፡፡