1በዚህ ጊዜ የአክዓብ ሰባ ትውልድ በሰማርያ ይገኝ ነበር፡፡ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ አንዳንድ ቅጂ ለከተማዪቱ ገዢዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የአክዓብ ትውልድ ጠባቂዎች ሁሉ ላከ፡፡ ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፡-
2«እናንተ ለንጉሡ ትውልድ፣ ፈረሶችና ሠረገሎች የጦር መሣሪያዎችና የተመሸጉ ከተሞች በእናንተ በእጃችሁ ለሚገኙ ሁሉ ኃላፊዎች ናችሁ፡፡ እንግዲህ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ፡-
3ከንጉሡ ትውልድ የተሻለውን አንዱን መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን አንግሡት፤ ለእርሱም ለሥርወ መንግሥቱ ተዋጉለት!» የሚል ነበር፡፡
4ነገር ግን እነርሱም በፍርሃት ተሸብረው «ንጉሥ ኢዮራምና ንጉሥ አካዝያስ ሊቋቋሙት ያልቻሉትን እኛ እንዴት ኢዩን ልንቋቋመው እንችላለን?» አሉ፡፡
5ስለዚህም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊና የከተማዪቱ ገዢ ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና ከአሳዳጊ ሞግዚቶች ጋር በመተባበር ለኢዩ «እኛ አገልጋዮችህ ነን፤ አንተ የምታዘንን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ አንተ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ» ሲሉ መልእክት ላኩ፡፡
6ኢዩም፡- «እናንተ ከእኔ ጋር ከተባበራችሁና ትእዛዜንም ለመፈፀም ዝግጁዎች ከሆናችሁ ነገ በዚህ ጊዜ የንጉሥ አክዓብን ዘሮች ሁሉ ራሶቻቸውን ቆርጣችሁ ወደ ኢይዝራኤል ይዛችሁልኝ እንድትመ›ጡ› ሲል ሌላ ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡ ሰባውም የንጉሥ አክዓብ ትውልድ በታወቁ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ ሥር ነበሩ፡፡
7የኢዩ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው የሰማርያ መሪዎች ሰባውንም የአክዓብ ተወላጆች በሙሉ ገደሉ፤ ራሶቻቸውንም በመቁረጥ በቅርጫት ሞልተው በኢይዝራኤል ወደ ነበረው ወደ ኢዩ ላኩለት፡፡
8ኢዩም የአክዓብ ትውልድ ራሶች ተቆርጠው መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በከተማይቱ ቅጥር በር በሁለት ረድፍ ተከምረው እስከ ተከታዩ ቀን ጠዋት ድረስ እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጠ፡፡
9በማግስቱ ማለዳ ላይ ኢዩ ወደ ከተማይቱ ቅጥር በር ሄዶ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ «በንጉሥ ኢዮራም ላይ በማሤር የገደልኩት እኔ ነበርኩ፤ ስለዚህም እናንተ በዚያ ጉዳይ አትጠየቁበትም፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የገደለ ማነው?
10ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈፅሞታል፡፡»
11ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶችና ባለሥልጣናት የነበሩትን እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ፡፡
12ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም «የእረኞች ሰፈር» ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፡-
13ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ «እናንተ እነማን ናችሁ?» ሲል ጠየቀ፡፡ እነርሱም ‹እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተ ሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው» ሲሉ መለሱለት፡፡
14ኢዩም «እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!» ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸው፤ ኢዩም በዚያው በቤት ኤክድ አጠገብ ገደላቸው፡፡ ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም፡፡
15ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጉዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ «የእኔ ልብ ከአንተ ጋር እንደ ሆነ የአንተ ልብ ከእኔ ጋር ነውን?» ሲል ጠየቀው፡፡ ኢዮናዳብም «አዎን ከአንተ ጋር ነው» ሲል መለሰለት፡፡ ኢዩም «እንግዲያውስ ጨብጠኝ» ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠው፡፡
16«ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ታማኝ እንደ ሆንኩ ራስህ ተመልከት» አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ፡፡
17ወደ ሰማርያ በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር በሰማርያ ያሉትን የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር፡፡
18ከዚያም ኢዩ የሰማርያን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ «ንጉሥ አክዓብ ባዓልን ያገለገለው በመጠኑ ነበር፤ እኔ ግን ከእርሱ ይበልጥ ላገለግለው እፈልጋለሁ፤
19ስለዚህም የባዓልን ነቢያት በሙሉ ባዓልን የሚያመልኩትንና ካህናቱን ጭምር በአንድነት ጠርታችሁ ሰብስቡልኝ፤ በምንም ምክንያት የሚቀር አይኑር፤ እኔ ለባዓል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ በዚያ የማይገኝ ማንም ሰው ቢኖር በሕይወት አይኖርም፡፡» ይህም ሁሉ ባዓልን የሚያመልኩትን ሁሉ ለመግደል ኢዩ ያቀደው የተንኮል ዘዴ ነበር፡፡
20ከዚህም በኋላ ኢዩ «ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት ክብረ በዓል ይደረግ!» ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህም በዐዋጅ ተነገረ፡፡
21ኢዩም በእስራኤል ምድርና ባዓልን ለሚያመልኩ ሁሉ መልእክት ላከ፡፡ ማንም ከጫፍ እስከ ጫፍ ሳይመጣ የቀረ አልነበረም፤ ሁሉም ወደ ባዓል ቤተ መቅደስ ገብተው ዳር እስከ ዳር ሞሉት፡፡
22ከዚያ ኢዩ የተቀደሱ አልባሳት ኀላፊ የሆነው ካህን አልባሳትን ሁሉ አውጥቶ ለባዓል አምላኪዎች እንዲያመጣላቸው አዘዘ፡፡ እንደታዘዘውም አልባሳቱን አመጣላቸው፡፡
23ስለዚህም ኢዩ ራሱ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር አብሮ ወደ ባዓል ቤተ መቅደሱ ገባ፤ በዚያም ለሕዝቡ በዚህ የሚገኙት የባዓል አምላኪዎች ብቻ መሆናቸውንና እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንድም አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ ሲል ተናገረ፡፡
24ከዚያም እርሱና ኢዮናዳብ ለባዓል ልዩ ልዩ መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ለማቅረብ ሄዱ፡፡ ኢዩም በባዓል ቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሰማኒያ ወታደሮች በማሰለፍ እነዚህን ሁሉ ሰዎች እንድትገድሉ፣ ከእነርሱ አንድ እንኳ የሚያመልጥ ሰው ቢኖር በዚያ ሰው ምትክ እርሱ ራሱ ይገደላል ሲል መመሪያ ሰጥቶአቸው ነበር፡፡
25ኢዩ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ ወዲያውኑ ለጠባቂዎችና ለአዛዡ፡- ሂዱና ማንም ሰው እንዳያመልጥ ግደሉአቸው አለ፡፡ እነርሱም በሰይፍ ስለት ሁሉንም ገደሉአቸው፤ ሬሳቸውንም ሁሉ እየጎተቱ ወደ ውጪ ጣሉ፤ ጠባቂና የጦር አዛዦቹ ወደ ባዓል ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ገቡ፡፡
26ከዚያም በባዓል ቤተ መቅደስ የነበረውን የድንጋይ ዐምዶች ወደ ውጪ አውጥተው በእሳት አቃጠሉት።
27ከዚያም የባዓል አምላኪዎቹን አጸድ አፍርሰው የባዓልን ቤተ መቅደስ አጠፉ፤ እስከዛሬ ድረስ ቤተ መቅደሱንም መጸዳጃ እንዲሆን አደረጉት፡፡
28ኢዩ በእስራኤል የነበረውን የባዓልን አምልኮ ያስወገደው በዚህ ዓይነት ነበር፡፡
29ነገር ግን ኢዩ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን፣ በቤተልና በዳን፣ የወርቅ ጥጃ የጣዖት ማምለኪያ ምስል ያቆመበትን የኃጢአት መንገድ አልተከተልም፡፡
30ስለዚህም እግዚአብሔር ኢዩን፡- በአክዓብ ትውልድ ሁሉ ላይ ልታደርግ የሚገባህን በዐይኖቼ ፊት ትክክል የሆነውን ፈጽመሃል፤ ከዚህም የተነሣ የአንተ ትውልድ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ላይ እንደሚነግሡ የተስፋ ቃል እስጥሃለሁ አለው፡፡
31ኢዩ ግን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት ከመራበት ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልተመለሰም፡፡
32በዚያም ዘመን እግዚብሔር የእስራኤልን ግዛት እንዲቀነስ አደረገ፤ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤልን ድል ነሥቶ የእስራኤልን ግዛት ድንበሮች ያዘ፡፡
33እርሱም የያዘው ግዛት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በስተ ደቡብ በኩል ከአርኖን ወንዝ በላይ እስከምትገኘው እስከ አሮዔር ከተማ የሚደርስ ሲሆን ይህም የጋድ የቶቤልና በምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኖሩባቸው የነበሩትን ሸለቆ የገለዓድንና የባሳንን ግዛቶች ያጠቃልላል፡፡
34ኢዩ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
35ከዚህም በኋላ ኢዩ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ፡፡
36ኢዩም በሰማርያ እስራኤልን ለሃያ ስምንት ዓመት ገዛ፡፡