1ኤልሳዕም፡- «እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ስማ! ነገ በዚህ ጊዜ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር በሰማርያ በር ይሸመታል» አለ፡፡
2በዚህ ጊዜ የንጉሡ ባለሥልጣን ለእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፡- እግዚአብሔር የሰማይ መስኮቶችን እንኳ ቢከፍት ይህ ሊሆን ይችላልን? ኤልሳዕም እንዲህ ሲል መለሰለት፡- ይህ ሲፈጸም በዐኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፤፤ አንተ ግን ከዚህ ምንም አትበላም፡፡
3አራት ለምጻሞች ከሰማርያ ከተማ በር ቆመው ነበር፡፡ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፡- እስክንሞት ለምን እዚህ እንቀመጣለን?
4ወደ ከተማ እንግባ ካልን በከተማው ራብ ስላለ እንሞታለን፡፡ ነገር ግን እዚህ ከተቀመጠንም መሞታችን ነው፤ ወደ ሶርያውያን ጦር ሰፈር እንሂድ፤ በሕይወት ካቆዩንም በሕይወት እንኖራለን፤ ከገደሉንም መሞት ብቻ ነው፡፡
5ስለዚህም ቀኑ ሊመሽ ሲል ወደ ሶርያውያን ጦር ሰፈር ሊሄዱ ተነሡ፤ ወደ ሰፈሩም በደረሱ ጊዜ እዚያ ማንም አልነበረም፡፡
6ይህም የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር የሶርያ ጦር የፈረሶች፣ የሠረገሎችና ሌሎችንም ከፍተኛ የሠራዊት ድምፅ እንዲሰሙ አድርጎ ስለነበረ ነው፤ እርስ በርሳቸውም እንዲህ አሉ፡- የእስራኤል ንጉሥ የሒታውያንና የግብፃውያንን ሠራዊት ቀጥሮ እኛን እያጠቃ ነው፡፡
7ስለዚህ ሠራዊቱ በሌሊት ተነሥቶ ሸሸ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና በሰፈሩ ያለውን ሁሉ ትተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሹ፡፡
8ለምጻሞቹም ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ወደ አንዱ ድንኳን በገቡ ጊዜ በሉ፣ ጠጡ፤ ብር፣ ወርቅና ልብስም ወስደው ደበቁ፡፡ እንደገና ተመልሰው ወደ ሌላ ድንኳን ገብተው ያለውን ወስደው እንደበፊቱ አደረጉ፡፡
9ከዚያም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፡- መልካም አላደረግንም፡፡ ዛሬ የምሥራች የሚሆን ታላቅ ነገር አግኝተናል፤ ነገር ግን ዝም ብለናል፡፡ እስኪነጋም ዝም ብንል ቅጣት ይደርስብናል፡፡ አሁን ተነሥተን እንሂድና ለንጉሡ ቤተ ሰብ እንንገር፡፡
10ስለዚህ ሄደው የከተማውን በር ጠባቂዎች ተጣሩ፤ እንዲህ ብለውም ነገሩአቸው፡- ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄደን ነበር፤ ነገር ግን ማንም አልነበረም፤ አንዲት ድምፅ እንኳን የለም፤ ነገር ግን ፈረሶችና አህዮች እንደታሰሩ አሉ፣ እንዲሁም ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው፡፡
11ከዚያም የበር ጠባቂዎቹ ወሬውን ተናገሩ፤ ከዚያም እስከ ንጉሡ ቤተ ሰብ ድረስ ተሰማ፡፡
12ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፡- ሶርያውያን የደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደተራብን ስለሚያውቁ ራሳቸውን ለመሰወር ሰፈሩን ለቀው ወደ ገጠር ሄደዋል፤ እንዲህም ይላሉ፡- ምግብ ፍለጋ ከከተማ ሲወጡ በሕይወት እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማም እንወስዳቸዋለን፡፡
13ከንጉሡም ባለሥልጣናት አንዱ መልሶ እንዲህ አለ፡- ጥቂት ሰዎች ከሞት ከተረፉት አምስት ፈረሶች እንድንወስድ እለምንሃለሁ፡፡ በዚህ ከተማ የተረፈው ሕዝብ ከዚህ በፊት እንደሞቱ ሰዎች ሁሉ ከሞት የሚያመልጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሆነውን ነገር ለማወቅ እንድንችል እነርሱን እንላክ፡፡
14ንጉሡም ሁለት ሠረገላዎችን ከፈረሶች ጋር ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ እንዲህ ሲል ላካቸው፡- ሂዱና ተመልከቱ፡፡
15እነርሱም ከሶርያውያን ኋላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ በየመንገዱም ሁሉ ሶርያውያን ሲሸሹ ጥለው የሄዱትን ብዙ ልብስና መሣሪያ ሁሉ አገኙ፡፡ መልእክተኞቹም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት፡፡
16ሕዝቡ ሄደው የሶርያውያንን ሰፈር ዘረፉ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ከዚህ በፊት እንደተናገረው ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም አምስት ኪሎ የገብስ ዱቄት በአንድ ብር ተሸመተ፡፡
17ንጉሡም የከተማዪቱ ቅጥር በር በባለሥልጣኑ ኃላፊነት እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን ያንን አገልጋይ ሕዝቡ ረጋጦት በዚያው ሞተ፡፡ ይህም የሆነው ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው ለማነጋገር በሄደ ጊዜ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነበር፡፡
18ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሡ፣ በዚህ ጊዜ በሰማርያ ከተማ በር ሦስት ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ብር ይሸመታል ብሎት ነበር፡፡
19በዚያም ባለሥልጣኑ ለእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ሲል መልሶ ነበር፡- እግዚአብሔር የሰማይ መስኮቶችን እንኳ ቢከፍት ይህ እንዴት ይሆናል? ኤልሳዕም፡- ይህ ሲሆን በዐይንህ ብቻ ትመለከታለህ፤ ነገር ግን ከዚህ ምንም አትበላም ብሎት ነበር፡፡
20እንግዲህ ያ የንጉሡ ባለሥልጣን በሰማርያ ከተማ ቅጥር በር ላይ ሕዝብ ረጋግጦት ለመሞት የበቃው ይህ ትንቢት ስለ ተፈጸመበት ነው፡፡