1የነቢያት ልጆችም ኤልሳዕን፡- «ከአንተ ጋር የምንኖርበት ስፍራ ከሁላችንም ጠባብ ነው አሉት፡፡
2ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደን ዛፍ ቆርጠን የምንኖርበትን ቤት በዚያ እንድንሠራ ፍቀድልን!» አሉት፡፡ ኤልሳዕም «መልካም ነው ቀጥሉ!» በማለት መለሰላቸው፡፡
3ከእነርሱም አንዱ ኤልሳዕን አብሮአቸው እንዲሄድ ጠየቀው፤ ኤልሳዕም እሄዳለሁ አላቸው፡፡
4እርሱም አብሮአቸው ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ ዛፍ የመቁረጥ ተግባራቸውን ጀመሩ፡፡
5ነገር ግን አንዱ ዛፍ በመቁረጥ ላይ ሳለ መጥረቢያው ወድቆ ውሃው ውስጥ ጠለቀ፤ እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ: - «ጌታዬ ሆይ! መጥረቢያው የተዋስኩት ነው፣ ምን አደርጋለሁ?» ሲል ጮኸ፡፡
6የእግዚአብሔርም ሰው፡- «በየት በኩል ነው የወደቀው?» ሲል ጠየቀው፡፡ ሰውየውም መጥረቢያው የወደቀበትን ስፍራ አሳየው፡፡ እርሱም አንድ እንጨት ቆርጦ ወደ ውሃው በጣለ ጊዜ መጥረቢያው ተንሳፈፈ፡፡
7ኤልሳዕም፡- «ውሰደው» አለው፡፡ ሰውየውም ጎንበስ ብሎ አነሣው፡፡
8እነሆ፣ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከፍቶ ነበር፡፡ እርሱም ከጦር አዛዦቹ ጋር ተማክሮ የሚሰፍሩበትን ቦታ መረጠ፡፡
9የእግዚአብሔርም ሰው: - «ሶርያውያን ደፈጣ አድርገው ስለሚጠብቁህ ከዚህ ወደዚያ ስፍራ አትቅረብ» ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ፡፡
10የእስራኤልም ንጉሥ ወታደሮቹ ወደሚኖሩበት፣ የእግዚአብሔር ሰው ወደተናገረበትና ወዳስጠነቀቀበት ስፍራ ላከ፡፡ ይህም ድርጊት ከአንድ ጊዜ ወይም ከሁለት ጊዜ በላይ ንጉሡ እዚያ ሲሄድ ከጥበቃ ጋር ነበር፡፡
11የሶርያ ንጉሥም፡- «ከእኛ መካከል ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ግንኙነት ያለው ማን እንደሆነ አትነግሩኝምን?» ሲል ጠየቃቸው፡፡
12ከእነርሱም አንዱ «ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ከእኛ መካከል ይህን የሚያደርግ ማንም የለም፤ በመኝታ ክፍልህ እንኳ ሆነህ የምትናገረውን ሁሉ ሳይቀር ለእስራኤል ንጉሥ ምሥጢሩን የሚገልጥለት ኤልሳዕ የተባለው ነቢይ ነው» ሲል መለሰለት፡፡
13የሶርያው ንጉሥ፡- «እርሱ የሚገኝበትን ስፍራ ፈልጉ፤ እኔም ልኬ እማርከዋለሁ» አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ በዶታይን እንደሚኖር ተነገረው፡፡
14ስለዚህ ንጉሡ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ብዙ ሠራዊት ወደ ዶታይን ላከ፡፡ እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ፡፡
15በማግስቱም ማለዳ የኤልሳዕ አገልጋይ ከመኝታው ተነሥቶ ከቤት ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀቡ የሶርያ ወታደሮች ከተማዪቱን መክበባቸውን አየ፡፡ ወደ ኤልሳዕም ተመልሶ: - «ጌታዬ ወዮ! ምን ማድረግ ይሻለናል?» ሲል ጠየቀው፡፡
16ኤልሳዕም «አይዞህ አትፍራ፤ ከእነርሱ ጋር ከተሰለፈው ይልቅ ከእኛ ጋር የተሰለፈው ሠራዊት ይበልጣል» አለው፡፡
17ኤልሳዕም «እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችል ዐይኖቹን ክፈትለት!» ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕን አገልጋይ ዐይኖች ከፈተለት፤ በኮረብታው ብዙ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ እንዳሉ ተመለከተ፡፡
18ሶርያውያንም ወደ እርሱ በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ እንዲህ ሲል ጸለየ፡- «እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች እንዲታወሩ አድርግ!» እግዚአብሔርም ኤልሳዕ እንደ ጸለየው፣ ዐይኖቻቸው እንዲታወሩ አደረገ፡፡
19ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ሶርያውያንን፡- «መንገድ ተሳስታችኋል፤ የምትፈልጓት ከተማ ይህች አይደለችም፤ ይልቅስ ወደምትፈልጉት ሰው እኔ ልምራችሁ፣ ተከተሉኝ» ብሎ ወደ ሰማርያ መራቸው፡፡
20ወደ ሰማርያም በደረሱ ጊዜ ኤልሳዕ፡- «እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች ማየት እንዲችሉ ዐይኖቻቸውን ክፈት!» ሲል ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን በከፈተላቸው ጊዜ በሰማርያ መካከል መሆናቸውን ተረዱ፡፡
21የእስራኤልም ንጉሥ ሶርያውያንን ባያቸው ጊዜ «ጌታዬ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?» ሲል ኤልሳዕን ጠየቀው፡፡
22ኤልሳዕም «አይሆንም! እንኳን እነዚህን በሰይፍህና በቀስትህ የማረካቸውን ወታደሮች መግደል አይገባህም፤ ይልቅስ የሚበሉትንና የሚጠጡትን ምግብ አቅርብላቸውና ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አድርግ» አለው፡፡
23ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ለእነርሱ ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ ከበሉና ከጠጡም በኋላ ወደ ሶርያ ንጉሥ መልሶ ላካቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሶርያውያን በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጋቸውን አቆሙ፡፡
24ከዚህ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ መላ ሠራዊቱን ሰብስቦ በእስራኤል ላይ በማዝመት ጉዳት አደረሰ፤ የሰማርያን ከተማም ከበበ፡፡
25ስለዚህ በሰማርያ ጽኑ ራብ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ የአንድ አህያ ራስ ሰማኒያ መክሊት ብር፣ ሁለት መቶ ግራም የሚያህል የርግብ ኩስ ዋጋ እስከ አምስት መክሊት ብር ይሸጥ ነበር፡፡
26አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ በከታማዪቱ የቅጥር ግንብ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት: - «ንጉሥ ሆይ እባክህ እርዳኝ!» ስትል ጮኸች፡፡
27ንጉሡም «እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከአውድማው ወይንስ ከወይን መጭመቂያው ይመጣልን?
28ለመሆኑ ችግርሽ ምንድን ነው?» ሲል ጠየቃት፡፡ እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፡- «ባለፈው ቀን ይህች ሴት ‹ዛሬ ያንቺን ልጅ እንብላ፤ በማግስቱ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን› ስትል አሳብ አቀረበች፡፡
29ስለዚህም የእኔን ልጅ ቀቅለን በላን፤ በማግስቱም ‹ልጅሽን አምጪና እንብላ› ብዬ ጠየቅኋት፤ እርስዋ ግን ደበቀችው፡፡»
30ንጉሡም ይህንን የሴትዮዋን ቃል በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ በግንቡ ላይ በመሆኑ በአቅራቢያው የነበረው ሕዝብ ንጉሡ በውስጡ ማቅ ለብሶ እንደ ነበር አዩ፡፡
31ንጉሡም ድምፁን ከፍ በማድረግ «የዛሬይቱ ጀምበር ከመጥለቅዋ በፊት የሳፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ሳይቆረጥ ቢያድር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!» ሲል ተናገረ፡፡
32በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ከሽማግሌዎች ጋር በቤቱ ተቀምጦ ነበር፡፡ ንጉሡም ኤልሳዕን ይዞ የሚመጣ መልእክተኛ ላከ፡፡ የንጉሡ መልእክተኛ ከመድረሱም በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን፡- «ይህ ነፍሰ ገዳይ እኔን ለማስገደል አንድ ሰው ልኮአል! እነሆ እርሱ እዚህ በሚደርስበት ጊዜ በሩን ዝጉ፤ ወደ ውስጥም እንዲገባ አትፍቀዱለት፤ ንጉሡም እርሱን ተከትሎ መጥቶ በኋላው ይገኛል» አላቸው፡፡
33ገና ይህን ተናግሮ ሳይጨርስ ንጉሡ ድንገት ከተፍ ብሎ «ይህን መከራ ያመጣው እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ ከዚህ በላይ እግዚአብሔርን የምጠብቀው ለምንድን ነው?» አለ፡፡