1የሶርያ ጦር አዛዥ የነበረው ንዕማን በሶርያ ንጉሥ ዘንድ ታላቅና የተከበረ ነበር፤ ምክንያቱም በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር ለሶርያ ሠራዊት ድልን አጎናጽፎ ነበር፡፡ እርሱም ደግሞ ጠንከራና ብርቱ ሰው ነበር፤ ነገር ግን ለምጻም ነበር፡፡
2ሶርያውያን በእስራኤላውያን ላይ ወረራ በፈጸሙበት ጊዜ አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ ማርከው ወስደው ነበር፤ እርስዋም ለንዕማን ሚስት ሠራተኛ ሆና ታገለግል ነበር፡፡
3ልጃገረዲቱም እመቤትዋን እንዲህ አለቻት፡- «ጌታዬ በሰማርያ ወደሚገኘው ነቢይ ቢሄድ እወዳለሁ! እርሱም ጌታዬን ከዚህ ለምጽ ሊያነፃው ይችላል!» አለቻት፡፡
4ንዕማንም ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ልጃገረዲቱ ያለችውን ሁሉ ነገረው፡፡
5ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ እንዲህ አለ፣ «ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ፤ አሁን አንተ ሂድ» ብሎ ፈቀደለት፡፡ ንዕማንም ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺህ መሐለቅ ወርቅና ዐሥር መለወጫ ልብስ አስጭኖ፣ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
6እርሱም ለእስራኤል ንጉሥ የተጻፈለትን ደብዳቤ ወሰደ፣ ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፡- «ይህ ደብዳቤ የኔ አገልጋይ ስለሆነው ስለ ንዕማን ጉዳይ የሚገልጥ ነው፤ ከለምጹም እንድትፈውሰው ወደ አንተ ልኬዋለሁ» የሚል ነበር፡፡
7የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ በቁጣ ልብሱን ቀደደ፤ እንዲህም አለ፡- «የሶሪያ ንጉሥ ይህን ሰው እንድፈውስለት እንዴት ይገምታል? እኔ ሰውን ከለምጽ እፈውስ ዘንድ የማዳንና የመግደል ሥልጣን ያለኝ እግዚአብሔር መሰልኩትን? ይህ አባባል ከእኔ ጋር ጠብ ለመጀመር የፈለገ ይመስላል!» አለ፡፡
8ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን መቅደዱን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፡- «ስለምን ልብስህን ቀደድክ? ሰውየውን ወደ እኔ ላከው፤ እርሱም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን ያውቃል!» አለው፡፡
9ስለዚህም ንዕማን ከፈረሶችና ከሠረገላዎቹ ጋር ወደ ኤልሳዕ ቤት መጥቶ በር ላይ ቆመ፡፡
10ኤልሳዕም አንዱን አገልጋይ ልኮ «ሄደህ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ራስህን በማጥለቅ ታጠብ፤ ሰውነትህም ይመለሳል፤ ንጹሕም ትሆናለህ› ብለህ ለዚህ ሰው ንገረው» ሲል ተናገረው፡፡
11ንዕማን ግን ተቆጥቶ ለመመለስ ተነሣ፤ እንዲህም አለ፡- “እኔ ነቢዩ መጥቶ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ በሽታዬ ያለበትን ቦታ በእጆቹ በመዳሰስ ከለምጽ በሽታዬ ይፈውሰኛል ብዬ ነበር፡፡
12በእስራኤል ከሚገኙት ወንዞች ይልቅ በአገሬ በደማስቆ የሚገኙት አባናና ፋርፋ አይሻሉምን? በእነርሱ ታጥቤ ንጹሕ መሆን አልችልምን?” ስለዚህ ተነሥቶ ሄደ፡፡›
13የንዕማንም አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው፡- «ጌታችን ሆይ፣ ነቢዩ ሌላ ከባድ ነገር እንድታደርግ ቢያዝህ ኖሮ ትፈፅመው ነበር፤ ታዲያ ነቢዩ ባዘዘህ መሠረት ታጥበህ ከበሽታህ መንጻት ምን ይከብድሃል?» አሉት፡፡
14ከዚያም ንዕማን የእግዚአብሔር ሰው ባዘዘው መሠረት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ሰባት ጊዜ በመነከር ታጠበ፤ ከበሽታውም ፈጽሞ ነጻ፡፡ ሰውነቱም እንደ ሕፃን ልጅ ገላ በመታደስ ፍፁም ጤናማ ሆነ፡፡
15ንዕማንና አጃቢዎቹ ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመልሰው መጥተው በፊቱ ቆሙ፡፡ ንዕማንም እንዲህ አለ፡- «ከእስራኤል አምላክ በቀር በምድር ላይ ሌላ አምላክ እንደሌለ እነሆ አሁን ዐወቅሁ፡፡ ስለዚህም ከአገልጋይ ይህን ስጦታ እባክህ ተቀበለኝ» አለው፡፡
16ኤልሳዕ ግን «በፊቱ ቆሜ በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ምንም ስጦታ አልቀበልህም» ሲል መለሰለት፡፡ ንዕማንም ስጦታውን እንዲቀበል አጥብቆ ቢለምነውም ኤልሳዕ ሊቀበለው አልፈቀደም፡፡
17ስለዚህም ንዕማን እንዲህ አለ፡- «ስጦታዬን የማትቀበለኝ ከሆነ ለሌሎች ባዕዳን አማልክት የሚቃጠልም ሆነ ሌላ አይነት መሥዋዕት የማቀርበውን ከአሁን ጀምሮ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ለማቅረብ ስለወሰንሁ የሁለት በቅሎ ጭነት አፈር ይዤ እንድሄድ ፍቀድልኝ፡፡»
18ስለዚህም የአገሬን ንጉሥ በማጀብ ሬሞን የተባለ ባዕድ አምላክ ወደሚመለክበት መቅደስ ብገባና ብሰግድም እንኳ እግዚአብሔር በዚህ ጉዳይ ይቅር እንደሚለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በእርግጥም በዚህ ጉዳይ ይቅር ይለኛል፡፡»
19ኤልሳዕም «በሰላም ሂድ!» አለው፤ ንዕማንም ተሰናብቶ ሄደ፡፡
20እርሱም ጥቂት ራቅ ብሎ እንደ ሄደ፣ የኤልሳዕ አገልጋይ ግያዝ ለራሱ እንዲህ አለ፡- «ጌታዬ ሶሪያዊው ንዕማን ካመጣው ስጦታ ሳይቀበል አሰናብቶታል፡፡ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ ተከትዬው ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ» ሲል በልቡ አሰበ፡፡
21ስለዚህም ግያዝ ንዕማንን ከኋላው ተከተለው፡፡ ንዕማንም መለስ ብሎ አንድ ሰው እየሮጠ ሲከተለው ባየ ጊዜ እርሱን ለመገናኘት ከሠረገላው ወርዶ እንዲህ አለ፡- «ሁሉ ነገር ሰላም ነው?»
22ግያዝም፡- «ሁሉ ነገር መልካም ነው፡፡ ጌታዬ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖሩ ሁለት ወጣት የነቢያት ልጆች ድንገት መጡብኝ፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መቀየሪያ ልብሶች ላክልኝ ብሎ ልኮኛል» ሲል መለሰለት፡፡
23ንዕማንም፡- «እባክህ ሁለት መክሊት ብር ለመስጠት በጣም ደስተኛ ነኝ» ሲል መለሰለት፡፡ ብሩን በሁለት ከረጢት ሞልቶ ከሁለት መለወጫ ልብሶች ጋር በሁለት አገልጋዮች አስይዞ ከግያዝ ፊት እንዲሄዱ አደረገ፡፡
24ግያዝም ወደ ኮረብታው በደረሰ ጊዜ፣ ግያዝ ሁለቱን ከረጢት ብር ከእጃቸው ወስዶ ወደ ቤት አስገባ፡፡ እነርሱንም አሰናብቶአቸው ሄዱ፡፡
25ወደ ቤት ተመልሶ ገብቶ በጌታው በኤልሳዕ ፊት በቆመ ጊዜ ኤልሳዕ እንዲህ አለው፡- «ግያዝ ከወዴት መጣህ?» እርሱም፡- «ጌታዬ፣ አገልጋይህ የትም አልሄድኩም» ሲል መለሰ፡፡
26ኤልሳዕም ለግያዝ፡- «ሰውየው አንተን ለመገናኘት ከሠረገላው ሲወርድ እኔ በመንፈስ ከአንተ ጋር አልነበርኩምን? እነሆ አሁን ገንዘብና ልብስ፣ የወይራና የወይን ተክል ቦታ፣ በግና የቀንድ ከብት ወይም አገልጋዮችን ለመቀበል ጊዜው ነውን?
27ስለዚህ እነሆ የንዕማን ለምጽ ወደ አንተና ዘሮችህ ለዘላለም ይተላለፋል» አለው፡፡ ግያዝም ከፊቱ ወጥቶ ሄደ፣ ለምጹም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡