መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የነቢያት ጉባኤ አባል የነበረ፣ ባልዋ የሞተባት አንዲት ሴት ወደ ኤልሳዕ መጥታ፣ ጌታዬ ሆይ፣ ባሌ ሞቶብኛል፤ እርሱም አንተ እንደምታውቀው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን እነሆ ለባሌ ገንዘብ አበድሮት የነበረ አንድ ሰው በባሌ ዕዳ ፈንታ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ወስዶ ባሪያ አደርጎ ሊገዛቸው ፈልጎአል አለችው፡፡
2ኤልሳዕም ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽ ምን እንዳለሽ ንገሪኝ? ሲል ጠየቃት፡፡ እርስዋም በትንሽ ማሰሮ ከሚገኝ የወይራ ዘይት በቀር ሌላ ምንም የለኝም ስትል መለሰችለት፡፡
3ኤልሳዕም እንዲህ አላት፡- ወደ ጎረቤቶችሽ ሄደሽ ማግኘት የምትችዪውን ያህል ባዶ ማድጋ ለምኚ፤
4ከዚህም በኋላ አንቺና ልጆችሽ ቤት ገብታችሁ በሩን ዝጉ፡፡ የማሰሮውንም ዘይት ወደ ማድጋዎቹ ማንቆርቆር ጀምሪ፤ እያንዳንዱ ማድጋ በሚሞላበት ጊዜ ለብቻው በማግለል አኑሩት፡፡
5ስለዚህም ሴትዮዋ ወደ ቤትዋ ሄዳ ከልጆችዋ ጋር በሩን ዘጋች፤ ዘይት የነበረበትን ትንሽ ማሰሮ አንሥታም ልጆችዋ እያቀረቡላት በማንቆርቆር በየማድጋዎቹ ሞላች፡፡
6ማድጋዎቹንም ሁሉ ከሞሉ በኋላ ሌላ ትርፍ የለም ወይ ስትል ጠየቀች፤ ከልጆችዋም አንዱ ሌላ ማድጋ የለም ሲል መለሰላት፡፡ ከዚያ በኋላ ዘይቱ መውረዱን አቆመ፡፡
7እርስዋም ተመልሳ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ ሄደች፤ እርሱም እንግዲህ ዘይቱን ሸጠሽ ዕዳሽን ክፈይ፤ ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ የሚሆንም ብዙ ገንዘብ ይተርፍሻል አላት፡፡
8አንድ ቀን ኤልሳዕ አንዲት ሀብታም ሴት ወደምትኖርበት ወደ ሱነም ሄደ፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ ጋበዘችው፤ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ወደ ሱነም በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ በቤትዋ ይመገብ ነበር፡፡
9እርስዋም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ ብዙ ጊዜ ወደ ቤታችን የሚመጣው ይህ ሰው የተቀደሰ የእግዚአብሔር ሰው ስለ መሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡
10ስለዚህም በሰገነቱ ላይ አንድ ትንሽ ክፍል ሠርተን በዚያች ውስጥ አል፣ ጠረጳዛ፣ ወንበርና የፋኖስ መብራት እናኑርለት፤ እርሱም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ እዚያ ያርፋል፡፡
11አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደዚያ እንደገና ሄደ፤ ወደ ተሠራለት ክፍል ገብቶ እረፍት አደረገ፡፡
12ኤልሳዕም ለአገልጋዩ ግያዝ እንዲህ አለ፡- «ይህችን ሱናማዊት ጥራት» በጠራትም ጊዜ መጥታ በፊቱ ቆመች፡፡
13ኤልሳዕም ግያዝን እንዲነግራት እንዲህ አለው፡- «እኛን ለመንከባከብ ይህን ሁሉ ተቸገረሽ፤ እኛ ደግሞ ለአንቺ ምን እናድርግልሽ? ለንጉሥ ወይም ለጦር አዛዥ ስለ አንቺ ልንነግርልሽ እንችላለን? በላት አለው፡፡ እርስዋም «በዘመዶቼ መካከል ስለምኖር በዚህ ስፍራ ምንም የሚቸግረኝ ነገር የለም» ስትል መለሰችለት፡፡
14ኤልሳዕም ግያዝን «ታዲያ ምን ልናደርግላት እችላለን?» ሲል ጠየቀው፡፡ ግያዝም “እነሆ ልጅ የላትም፣ ባሏም ሸምግሎአል” አለ፡፡
15ኤልሳዕም ጥራት አለው፡፡ ሲጠራትም መጥታ በበሩ አጠገብ ቆመች፡፡
16ኤልሳዕም አላት፡- በመጪው ዓመት በዚህ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ አላት፡፡ እርስዋም ጌታዬ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እባክህ አገልጋይህን አትዋሻት አለችው፡፡
17ሴቲቱም ፀነሰች፤ ልክ ኤልሳዕ የተናገረው ጊዜ ሲደርስ በዓመቱ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡
18ሕፃኑም በአደገ ጊዜ አንድ ቀን አባቱ ከአጫጆች ጋር ወዳለበት ሄደ፡፡
19እርሱም በድንገት “ራሴን! ራሴን!” ብሎ ወደ አባቱ ጮኸ፡፡ አባትየውም አንዱን አገልጋይ ጠርቶ፡- “ልጁን ወደ እናቱ ውሰድ” ሲል አዘዘው፡፡
20አገልጋዩም ልጁን ተሸክሞ ወደ እናቱ ባመጣው ጊዜ እርስዋም ተቀብላው በጉልበትዋ እንደታቀፈችው ቆይቶ እኩለ ቀን ላይ ሞተ፡፡
21ሴቲቱም ተነሥታ ልጁን በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አስተኝታ በሩን ዘግታበት ተመልሳ ሄደች፡፡
22ባልዋንም ጠርታ “አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ሰው ዘንድ ሄጄ እመለሳለሁ አለችው፡፡
23ባልዋ “ለምን መሄድ ትፈልጊያለሽ? ዛሬ ሰንበት ወይም የጨረቃ በዓል የሚከበርበት ቀን አይደለም” አላት፡፡ እርስዋም “ግድ የለም፤ እንዳልኩህ አድርግ” አለችው፡፡
24እርስዋም አህያው እንዲጫንላት ካደረገች በኋላ አገልጋዩን “በተቻለ መጠን አህያው እንዲፈጥን አድርግ፤ እኔም ካልነገርኩህ በቀር ቀስ ብሎ እንዲሄድ ዕድል አትስጠው” ስትል አዘዘችው፡፡
25እርስዋም ከዚያ ተነሥታ ኤልሳዕ ወደነበረበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣች፡፡ የእግዚአብሔርም ሰው ገና በሩቅ ሳለች ወደ እርሱ ስትመጣ አይቶ አገልጋዩን ግያዝን «ተመልከት! ያቺ ሱነማዊት ወደዚህ እየመጣች ነው! አለው፡፡
26ፈጠን ብለህ ሂድና የእርስዋን፤ የባልዋንና የልጅዋን ደኅንነት ጠይቃት» አለው፡፡ እርስዋም ግያዝን «ሁላችንም ደኅና ነን» ስትል ነገረችው፡፡
27ወደ ኤልሳዕ ወደ ተራራው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ያዘች፤ በዚህ ጊዜ ግያዝ ሊያርቃት ፈለገ፤ ኤልሳዕ ግን «ተዋት፤ እርስዋ ተጨንቃለች፣ እግዚአብሔርም ከእኔ ሰውሮታልና ምንም የነገረኝ ነገር የለም» አለው፡፡
28ሴቲቱም «ጌታዬ፣ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‹አታሳስተኝ› ብዬ ነግሬህ አልነበረምን?» አለችው፡፡
29ኤልሳዕም ግያዝን አለው፡- «ለጉዞ በፍጥነት ተነሣና ምርኩዜን በእጅህ ያዝ፡፡ ወደ ቤትዋ ሂድ፡፡ በመንገድ ማንንም ብታገኝ ሰላምታ አትስጥ፤ ማንም ሰላምታ ቢሰጥህ መልስ አትስጥ፡፡ ምርኩዜን በልጁ ፊት ላይ አኑር!» አለው፡፡
30የልጁ እናት ግን ኤልሳዕን «በምትተማመንበት በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከቶ አንተን ትቼ አልሄድም!» አለችው፤ ስለዚህ እርስዋን ተከትሎ ለመሄድ ተነሣ፤
31ግያዝም ወደ ፊት ቀድሞአቸው የኤልሳዕን ምርኩዝ በልጁ ፊት ላይ አኖረ፤ ነገር ግን ልጁ ግን አልተናገረም፣ አልሰማም፡፡ ስለዚህም ተመልሶ ሄዶ ኤልሳዕን «ልጁ አልተነሣም» አለው፡፡
32ኤልሳዕም ወደ ቤቱ በደረሰ ጊዜ ልጁ ሞቶ አልጋ ላይ ነበር፡፡
33ስለዚህ ኤልሳዕ ገባና በሩን በልጁና በራሱ ላይ ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡
34ሄዶም በልጁ ላይ ተጋደመ፤ አፉን በአፉ ላይ፣ ዐይኖቹን በአይኖቹ ላይ፣ እጆቹን በእጆቹ ላይ አደረገ፤ ራሱን በልጁ ላይ ዘርግቶ ተጋደመ፤ የልጁም ሰውነት መሞቅ ጀመረ፡፡
35ከዚያም፣ ኤልሳዕ ተነሥቶ በክፍሉ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ጀመር፤ እንደገናም ተመለሰና በመዘርጋት በልጁ ላይ ተጋደመ፡፡ ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዐይኖቹን ከፈተ፡፡
36ስለዚህ ኤልሳዕ ግያዝን ጠርቶ እንዲህ አለ፣ ሱነማይቱን ጥራት አለው፡፡ እርሱም ጠራት፣ እርስዋም በመጣች ጊዜ ኤልሳዕ ልጅሽ ይኸውልሽ አንሽው አላት፡፡
37እርስዋ ወደ መሬት ለጥ ብላ በኤልሳዕ ጫማ ላይ በመውደቅ እጅ ነሣች፤ ከዚያም በኋላ ልጅዋን ይዛ ሄደች፡፡
38ከዚያም ኤልሳዕ ወደ ጌልጌላ መጣ፡፡ በአገሪቱ ራብ በነበረበት ጊዜ የነቢያት ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፡፡ እርሱም አገልጋዩን እንዲህ አለው፡- ትልቅ ድስት ጥደህ ለነቢያቱ ልጆች ወጥ ሥራላቸው አለው፡፡
39ከነቢያቱም አንዱ ቅጠላ ቅጠል ለመልቀም ወደ ሜዳ ሄደ፡፡ እርሱም በጫካ ውስጥ የበቀለ የቅል ሐረግ አገኘ፤ መሸከም የሚችለውን ያህል በርከት ያለ ቅል ቆርጦ አመጣ፡፡ እርሱም ከተፈውና ወጡ ውስጥ ጨመረው፤ ነገር ግን ምን እንደሆነ ዐላወቁም፡፡
40እነርሱም ወጡን ለሰዎቹ እንዲመገቡት አወጡ፡፡ በኋላም እየበሉ ሳለ ጮኸው፣ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ በድስቱ ውስጥ ሞት አለ! አሉት፤ ስለዚህም ሊበሉት አልቻሉም፡፡
41ነገር ግን ኤልሳዕ እንዲህ አለ፡- ጥቂት ዱቄት አምጡልኝ፡፡ ያመጡትን ዱቄት በድስቱ ውስጥ ጨምሮ እንዲህ አለ፡- ለሰዎች እንዲበሉ ወጡን አውጡ፡፡ ከዚያ በወጡ ውስጥ የሚጎዳ ነገር አልተገኘም፡፡
42በዓል ሻሊሻ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ሰው መጥቶ በመከር ጊዜ በመጀመሪያ ከተወቃው ሃያ የገብስ የዳቦ ሙልሙሎችና አዲስ የተቆረጠ እሸት በከረጢቱ አመጣለት፡፡ እርሱም ይህን እንዲበሉ ለነቢያት ልጆች ስጡአቸው አለ፡፡
43አገልጋዩም እንዲህ አለ፡- በመቶ ሰዎች ፊት ይህን ምን ብዬ ማቅረብ አለብኝ? ነገር ግን ኤልሳዕ አለ፡- እንዲበሉ ለሰዎቹ ስጣቸው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ይበላሉ ያተርፉማል፡፡
44ስለዚህም አገልጋዩ ምግቡን አቀረበላቸው፣ እግዚአብሔርም በተናገረው መሠረት ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ የተረፈ ምግብ ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።