1የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ እርሱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፡፡
2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፡፡ ነገር ግን እንደ አባቱና እናቱ አልነበረም፤ ምክንያቱም በዓል ተብሎ የሚጠራውን አባቱ አሠርቶት የነበረውን በዕድ አምላክ ምስል አስወገደ፡፡
3ይህም ሆኖ ከእርሱ በፊት እስራኤል ወደ ኃጢአት የመራው የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን አምልኮ ተከተለ እንጂ አላስወገደውም፡፡
4የሞአብ ንጉሥ ሞሳ በግ አርቢ ነበር፤ በየዓመቱም አንድ መቶ ሺህ ጠቦት የአንድ መቶ ሺህ በጎች ጠጉር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር፤
5ነገር ግን የእስራኤል ንጉሥ አካዓብ በሞተ ጊዜ የሞአብ ንጉሥ ሞሳ በእስራኤል ላይ ዐመፀ፡፡
6በዚያን ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ወዲያውኑ ከሰማርያ ወጥቶ ወታደርቹን ሁሉ በአንድነት ሰበሰበ፤
7ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥም የሞአብ ንጉሥ በእኔ ላይ አምፆብኛል፤ በእርሱ ላይ በማደርገው ጦርነት ከእኔ ጋር ትተባበራለህን? የሚል መልእክት ላከ፡፡ ንጉሥ ኢሣፍጥም አዎን እተባበርሃለሁ፤ እኔን እንደ ራስህ፣ ሠራዊቴን እንደ ሠራዊትህ፣፣ ፈረሶቼንም እንደ ፈረሶችህ መቁጠር ትችላለህ ሲል መለሰለት፡፡
8እርሱም ልናጠቃ የምንችለው በየትኛው መንገድ ነው? ሲል ጠየቀው፡፡ ንጉሥ ኢዮራምም በኤዶም በረሓ የሚገኘውን ዙሪያ መንገድ ይዘን እንጓዛለን ሲል መለሰለት፡፡
9ስለዚህም ንጉሥ ኢዮራም፣ እንዲሁም የይሁዳና የኤዶም ነገሥታት ለዘመቻ ወጡ፤ ከሰባት ቀን ጉዞም በኋላ ውሃ አለቀባቸው፤ ለሠራዊቱም ሆነ ለጭነት እንስሶቻቸው ምንም ውሃ አልነበረም፡፡
10የእስራኤል ንጉሥ ይህ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞአብ ንጉሥ አሳልፎ ሊሰጠን ነውን? ወዮልን ሲል ጮኸ፡፡
11ንጉሥ ኢዮሣፍጥም በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን መጠየቅ እንድንችል በዚህ አንድ ነቢይ የለም? ሲል ጠየቀ፡፡ ከንጉሥ ኢዮራም ሠራዊት አዛዦች አንዱ፣ ቀድሞ የኤልያስ ረዳት የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ ሲል መልስ ሰጠ፡፡
12ንጉሥ ኢዮሣፍጥም የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል አለ፤ ከዚያም በኋላ ሦስቱም ነገሥታት ወደ ኤልሳዕ ሄዱ፡፡
13ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ ኢዮራምን እኔ ለአንተ ማድረግ የሚገባኝ ምንድን ነው? ወደ አባትህና እናትህ ነቢያት ሂድ። ንጉሥ ኢዮራምም መልሶ አይደለም፣ ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞአብ ንጉሥ አሳልፎ ለመስጠት የጠራን እግዚአብሔር ነው አለ፡፡
14ኤልሳዕም እኔ በማገልግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ አንተን ለመርዳት ለመጣው ለይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ክብር ስል ነው እንጂ ለአንተስ ምንም ነገር ላደርግልህ ባልተገባ ነበር፡፡
15ነገር ግን በገና የሚደረድር ሰው አምጡልኝ አለ፡፡ ባለ በገናውም በሚደረድርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በኤልሳዕ ላይ ወርዶ እንዲህ አለ፡፡
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በዚህ የደረቀ ሸለቆ ሁሉ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሩ፡፡
17ምንም ዝናብና ነፋስ ባታዩም ይህ ሸለቆ በውሃ የተሞላ ይሆናል፡፡ እናንተ፣ የቀንድ ከብቶቻችሁና የጭነት እንስሶቻችሁ ሁሉ የምትጠጡት በቂ ውሃ ታገኛላችሁ፡፡
18ነገር ግን ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀላል ነገር ነው፡፡ ከዚህ በላይ እርሱ በሞአባውያን ላይ ድልን ያጎናጽፋችኋል፡፡
19የተመሸጉና ምርጥ የሆኑ ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል አድርጋችሁ ትይዛላችሁ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቆርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን ትደፍናላችሁ፤ ለም የሆኑ የእርሻ ቦታዎቻቸውን በማበላሸት ድንጋይ ትከምሩባቸዋላችሁ፡፡
20በማግስቱም ጠዋት መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት ሲደርስ ከኤዶም በኩል የውሃ ምንጭ ፈልቆ ምድሩን ሸፈነው፡፡
21ሞአባውያንም ሦስቱ ነገሥታት አደጋ ሊጥሉባቸው መምጣታቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ከሽማግሌ እስከ ወጣት መሣሪያ መያዝ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጥተው ለጦርነት መጡ፡፡
22በማግስቱም ጠዋት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ በውሃው ላይ የሚያበራው የፀሐይ ነጸብራቅ እንደ ደም ቀይ መስሎ ታያቸው፡፡
23ስለዚህም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ፣ ይህ ነገር ደም ነው፤ የሦስቱ ጠላቶቻችን ሠራዊቶች እርስ በርሳቸው በመተራረድ ተላልቀዋል፤ እንግዲህ ሄደን ሰፈራቸውን እንዝረፍ ተባባሉ፡፡
24እነርሱ ወደ ሰፈር በደረሱ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው አደጋ በመጣል ወደ ኋላ መለሱአቸው፤ እስራኤላውያን አገሪቱን ወርረው ሞአባውያንን ጨፈጨፉአቸው፡፡
25ከተሞቻቸውን ደመሰሱ፤ ለም በሆነው እርሻ ውስጥ በሚያልፉበትም ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውርበት ስለ ነበር በመጨረሻ እርሻዎቹ ሁሉ በድንጋይ ተሸፈኑ፤ ምንጮቻቸውን ደፈኑ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውንም ሁሉ ቆረጡ፤ በመጨረሻም የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረችው ቂርሔሬስ ብቻ ቀረች፤ እርስዋንም ድንጋይ የሚወነጭፉ ጦረኞች ከበው አደጋ ጣሉባት፡፡
26የሞአብ ንጉሥ ድል እንደ ተመታ ባረጋገጠ ጊዜ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎችን እስከትሎ የጠላት ጦር የተሰለፈበትን መስመር ጥሶ ለማምለጥና ወደ ሶሪያ ንጉሥ ለመሄድ ቢሞክርም ከቶ አልተሳካለትም፡፡
27ስለዚህ በእርሱ ምትክ መንገሥ የሚገባውን የመጀመሪያ ልጁን በከተማይቱ ግንብ ላይ ለሞአብ አምላክ መሥዋዕት አደርጎ አቀረበ፡፡ ስለዚህ በእስራኤል ዘንድ ከፍ ያለ ቁጣ ነበር፡፡ እስራኤላውያንም ለሞአብ ንጉሥ ከተማይቱን ለቀው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡