መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጉዞ ጀመሩ፡፡
2በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን እነሆ አንተ በዚህ ቆይ እኔ ወደ ቤቴል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡ ኤልሳዕ ግን እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ ከቶ ከአንተ አልለይም ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤቴል ሄዱ፡፡
3በዚያ የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፣ እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን? ሲሉ ጠየቁት፡፡ ኤልሳዕም አዎን ዐውቃለሁ፣ ነገር ግን ዝም በሉ ሲል መለሰላቸው፡፡
4ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን እነሆ አንተ በዚህ ቆይ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡ ኤልሳዕ ግን እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ ከቶ ከአንተ አልለይም፣ ሲል መለሰለት፡፡ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ፡፡
5በዚህም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን? ሲሉ ጠየቁት፡፡ ኤልሳዕም አዎን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ ሲል መለሰላቸው፡፡
6ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን እነሆ አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡ ኤልሳዕ ግን እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ ከቶ ከአንተ አልለይም፤ ሲል መለሰለት፡፡ እነዚህም አብረው ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡
7ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤
8ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃው ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሸገሩ፡፡
9በዚህም ኤልያስ ኤልሳዕን እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ አለው፡፡ ኤልሳዕም ያንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችለኝ መንፈስ በእጥፍ ይሰጠኝ ሲል መለሰለት፡፡
10ኤልያስም «ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየከውን ስጦታ መቀበል ትችላልህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም» ብሎ መለሰለት፡፡
11እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ ፈረሰኞች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ፡፡
12ኤልሳዕም ይህን ሁሉ እያየ «የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች የሆንከው አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ!» እያለ ወደ ኤልያስ ጮኸ፤ ከዚያም በኋላ ኤልያስን ዳግመኛ አላየውም፡፡ ኤልሳዕም ከሐዘን ብዛት የተነሣ ልብሱን ከሁለት ቀደደ፤
13ከኤልያስም የወደቀውን ካባ ከመሬት አነሣ፤ ከዚያም ሄዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ደርቻ ቆመ፡፡
14ውሃውንም በኤልያስ ካባ መትቶ፣ «የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?» አለ፤ ከዚያም በኋላ እንደገና በመታው ጊዜ ውሃው ወደ ቀኝና ግራ ተከፍሎለት ወደ ማዶ ተሻገረ፡፡
15ከኢያሪኮ የመጡት ነቢያት እርሱን ባዩት ጊዜ፣ «በኤልያስ ላይ ዐድሮ የነበረው የመንፈስ ኀይል በኤልሳዕ ላይ አርፏል!» አሉ፤ ወደ እርሱም በመቅረብ ጎንበስ ብለው እጅ ነሡት
16«እነሆ! በዚህ ጠንካራ የሆንን ኀምሳ ሰዎች አለን፤ እንሂድና ጌታህን እንፈልገው፤ ምናልባት የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወስዶ በአንድ ተራራ ወይም ሸለቆ ውስጥ አሳርፎት ይሆናል፡፡» ኤልሳዕም “አትሂዱ” ሲል መለሰ፡፡
17እነርሱ ግን እምቢ በማለት እስኪያፍር ድረስ አጥብቀው ስለ ለመኑት በጉዳዩ ተስማማና ኀምሳ ሰዎች ሄደው ሦስት ቀን ሙሉ ኤልያስን ፈለጉት፤ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡
18ከዚያም በኋላ በኢያሪኮ ሆኖ ወደሚጠብቃቸው ወደ ኤልሳዕ ተመለሱ፤ ኤልሳዕም «እኔ ቀድሞውንስ አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?» አላቸው፡፡
19ጥቂት ሰዎች ከኢያሪኮ ወደ ኤልሳዕ መጥተው «ጌታችን አንተ እንደምታውቀው ይህች ምድር መልካም ናት፤ ውሃው ግን መጥፎ በመሆኑ ምድሪቱ ምርት አትሰጥም፤ ስለሁኔታው እንለምንሃለን» አሉት፡፡
20ኤልሳዕም «በአዲስ ሳህን ውስጥ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ» ብሎ አዘዘ፡፡ እነርሱም እንዳዘዛቸው አድርገው አመጡለት፡፡
21እርሱም ወደ ምንጩ ሄዶ በውሃ ውስጥ ጨው በመጨመር «እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ‹እኔ ይህን ውሃ በመፈወስ ንፁህ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የሞትና የምርት መጨንገፍ ምክንያት አይሆንም›» ሲል ተናገረ፡፡
22ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤልሳዕ በተናገረው መሠረት ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ ንጹሕ ሆነ፡፡
23ኤልሳዕም ወደ ቤቴል ለመሄድ ከኢያሪኮ ተነሣ፡፡ በመንገድ ሳለ ከከተማይቱ በርከት ያሉ ልጆች ወጥተው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ አንተ ራሰ መላጣ! ራሰ መላጣ! ከዚህ ውጣ እያሉ ጮኹበት፡፡
24ኤልሳዕም መለስ ብሎ ዙሪያውን በመቃኘት አትኩሮ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ በዚህም ጊዜ ሁለት እንስት ድቦች ከጫካ ወጥተው ከእነዚያ ልጆች መካከል አርባ ሁለቱን ሰባብረው ጣሉአቸው፡፡
25ኤልሳዕም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ ዘግየት ብሎ ግን ወደ ሰማርያ ተመለሰ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።