1በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ከገበረለት በኋላ እንደገና አመፀ፡፡
2እግዚብሔር በአገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት ይሁዳን ስለ ማጥፋት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ወራሪ ቡድኖች ባቢሎናውያንን፣ ሶርያውያንን፣ ሞአባውያንንና አሞናውያንን በኢዮአቄም ላይ አስነሣበት፡፡
3ይህም ሁሉ የሆነው ንጉሥ ምናሴ በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የይሁዳን ሕዝብ ከፊቱ ለማስወገድ እግዚብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፡፡
4በተለይ ምናሴ የንጹሓንን ሰዎች ደም በማፍሰሱና ኢየሩሳሌምንም በንጹሓ ደም በመሙላቱ ምክንያት ይህ ሁሉ ሊፈጸም ችሎአል፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚብሔር ለምናሴ ምሕረት ሊያደርግለት አልፈቀደም፡፡
5ኢዮአቄም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
6ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ልጁ ዮአኪን ነገሠ፡፡
7የባቢሎን ንጉሥ ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ግብጽ ሰሜናዊ ጠረፍ ድረስ የግብጽ ይዞታ የነበረውን ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ስለ ነበረ፣ የግብጽ ንጉሥና ሠራዊቱ ከዚያ በኋላ ከግብጽ ውጪ ዘመቻ አላደረጉም፡፡
8ዮአኪን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ሦስት ወር ገዛ፡፡ እናቱም ኔስታ ተብላ የምትጠራው የኢየሩሳሌም ተወላጅ የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች፡፡
9አባቱ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡
10በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን አጠቃ፤ ከተማይቱንም ከበባት፡፡
11ሠራዊቱ ከብቦ በነበረበት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡
12የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን ከእናቱ፣ ከልዑላን መሳፍንቱ፣ ከጦር አዛዦቹና ከባለሥልጣናቱ ጋር ወደ ባቢሎን ንጉሥ ተወሰዱ፡፡ የባቢሎን ንጉሥም በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማረከው፡፡
13ናቡከደነፆርም በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ ጠራርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡ ቀደም ሲል እግዚብሔር በተናገውም ቃል መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚብሔር ቤተ መቅደስ አሠርቶት የነበረውን የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰባበረ፡፡
14ናቡከደነፆር የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ልዑላን፣ መሳፍንቱን ሁሉና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎች ጭምር በድምሩ ዐሥር ሺህ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፡፡ ከእርሱም ጋር የዕደ ጥበብ ዐዋቂዎችንና የብረት አንጣሪዎችን ሁሉ ወሰደ፤ በይሁዳ እንዲቀሩ ያደረገው የመጨረሻዎቹን ድኾች ብቻ ነበር፡፡
15ናቡከደነፆር ዮአኪንን አስሮ ከእናቱ፣ ከሚስቶቹ፣ ከአገልጋዮቹ፣ ከባለሥልጣኖቹና ከይሁዳ ታላላቅ ሰዎች ጋር በአንድነት ሰብስቦ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፡፡
16የባቢሎን ንጉሥ ሰባት ሺህ ለውጊያ ብቃት ያላቸው ወንዶችን እንዲሁም አንድ ሺህ ብረት ቀጥቃጮችንና ዕደ ጥበበኞችን ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡
17ናቡከደነፆርም በዮአኪን ምትክ ማታንያ ተብሎ የሚጠራውን የዮአኪንን አጎት በይሁዳ አነገሠው፤ ስሙንም በመለወጥ ሴዴቅያስ ብሎ ጠራው፡፡
18ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም አሚጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የነበረው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፡፡
19እርሱም አባቱ ኢዮአቄም ባደረገው ዓይነት በእግዚአብሔር ክፉ አደረገ፡፡
20እግዚብሔር ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ተቆጥቶ ነበር፡፡ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ፡፡