1ስለዚህ ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎችን ሁሉ ጠርቶ ሰበሰባቸው፡፡
2እነርሱም ካህናት፣ ነቢያት፣ ሌሎችም ሰዎች ከታናሾች ጀምሮ እስከ ታላቆች ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፡፡
3ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና አሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ ስለዚህም በዚህ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳኑ ለመቆም ተስማሙ፡፡
4ንጉሡም ኢዮስያስ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን፣ ረዳቶቹ የሆኑትን ካህናትና የቤተ መቅደስ በር ዘብ የሚጠብቁ ተረኞችን ጠርቶ ለባዓልና አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ፣ እንዲሁም ለከዋክብት ማምለኪያ ያገለግሉ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ ንጉሡም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ከኢየሩሳሌም ውጪ ባለው በቄድሮን ሸለቆ በእሳት አቃጥሎ ዐመዱን ወደ ቤቴል ወሰደው፡፡
5በይሁዳ ከተማዎችና በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባሉት ስፍራዎች ሁሉ በየኮረብታው ላይ በነበሩት መሠዊያዎች መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ የይሁዳ ነገሥታት ሾመዋቸው የነበሩትን ካህናት ሁሉ ከሥራ አሰናበተ፤ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ፣ ለፕላኔቶች፤ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ለፀሐይና ለሰማይ ከዋክብት ሁሉ መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉ ካህናትን ሁሉ አስወገደ፡፡
6አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ከቤተ መቅደስ ነቅሎ ከከተማይቱ በማውጣት ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ትቢያ እስኪሆንም አድቅቆ፣ በሕዝብ መቃብር ላይ በተነው፡፡
7ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉ ሴቶች አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ መጋረጃ የሚፈትሉበትን ክፍል ሁሉ አጸዳ፡፡
8በይሁዳ ከተሞችና በመላ አገሪቱ ከጌባ እስከ ቤርሳቤህ የነበሩትን ካህናት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፡፡ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ርኩስ መሆናቸውን አወጀ፤ እንዲሁም የከተማይቱ ገዢ ኢያሱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ከዋናው ቅጥር በር በስተግራ በኩል ባሠራው ቅጥር በር አጠገብ የሚገኙትን መስገጃዎች አፈራረሰ፡፡
9የከፍታ ቦታ ካህናት በቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ለማገልገል ያልተፈቀደላቸው ቢሆንም በወንድሞቻቸው ዘንድ የነበረውን እርሾ ያልነካውን ሕብስት በሉ፡፡
10ንጉሥ ኢዮስያስ በሔኖም ሸለቆ የነበረውን «ቶፌት» ተብሎ የሚጠራውን የአሕዛብ ማምለኪያ ቦታ የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ከዚህም የተነሣ «ሞሌክ» ተብሎ ለሚጠራው አምላክ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ማንም እንዳይኖር ተከለከለ፡፡
11የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ አምልኮ መድበዋቸው የነበሩትን ፈረሶች ሁሉ አስወገደ፡፡ ለዚሁ አምልኮ ያገለግሉ የነበሩትን ሠረገሎች አቃጠለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ቀደም ሲል ታላቁ ባለሥልጣን ናታን ሜሌክ በሚኖርባቸው ክፍሎች አጠገብና በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቅጥር በር አጠገብ ይገኙ ነበር፡፡
12ንጉሥ አካዝ ባሠራቸው መኖሪያ ክፍሎች ጣራ ላይ በሚገኘው ቤተ መንግሥት የይሁዳ ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን መሠዊያዎችና በቤተ መቅደሱ ሁለት አደባባዮች ንጉሥ ምናሴ አሠርቶአቸው የነበሩትን መስገጃዎቸ ሁሉ ኢዮስያስ ደመሰሳቸው፤ መሠዊያዎቹን ሰባብሮ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ ጣላቸው፡፡
13ንጉሡም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኩሰት ተራራ በስተ ደቡብ አስታሮት ተብሎ ለሚጠራው ለአሞን አምላክ ንጉሥ ሰሎሞን አሠርቶአቸው የነበሩትን አስጸያፊ ምስሎች፣ የሲዶናውያንና የሞዓባውያን አስጸያፊ የሆኑ ጣዖታትን ሁሉ ደመሰሰ፡፡
14ንጉሥ ኢዮስያስ የድንጋይ አምዶችን ሁሉ ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስሎች ሰባብሮ ጣለ፡፡ እነርሱም ቆመውበት የነበረውን የድንጋይ ዐምዶች ሰባብሮ ስፍራውንም የሙታን አጥንት ሞላበት፡፡
15እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤቴል አሠርቶት የነበረውን የማምለኪያ ቦታ ኢዮስያስ አፈራርሶ ጣለው፤ መሠዊያውን ነቅሎ የተመሠረተበትን ድንጋይ ሁሉ ሰባብሮ በማድቀቅ እንደ ትቢያ አደረገው፤ የአሼራንም ምስል በእሳት አቃጠለ፡፡
16ከዚያም ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት፣ በኮረብቶች ላይ የተሠሩ መቃብሮች አየ፤ በእነዚያም መቃብሮች ውስጥ የነበረውን አፅም ሁሉ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በእሳት አቃጠለው፡፡ በዚህም ዓይነት መሠዊያው የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ኢዮስያስ ይህንን ሁሉ በማድረጉ ከብዙ ጊዜ በፊት በተደረገ የአምልኮ በዓል ላይ ንጉሥ ኢዮርብዓም በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ ነቢዩ የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ፡፡ ንጉሥ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት ይህንን የእግዚአብሔር ቃል ተናግሮ የነበረው ነቢይ የተቀበረበትን መካነ መቃብር የማን ነው ሲል ጠየቀ፡፡
17የቤቴል ሕዝብ ከይሁዳ መጥቶ በዚህ መሠዊያ ላይ ይህንን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ እንደሚፈጸምበት ተናግሮ የነበረው የነቢዩ መቃብር ነው ሲሉ መለሱለት፡፡
18ኢዮስያስም እንዳለ ይኑር፣ የእርሱ አፅም ከዚህ መንቀሳቀስ የለበትም ሲል መለሰ፡፡ ስለዚህም የእርሱም ሆነ የሰማርያው ነቢይ አፅሞች ከዚያ እንዲነሡ አልተደረገም፡፡
19ከዚያም ንጉሥ ኢዮስያስ በማንኛይቱም የእስራኤል ከተማ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማነሣሣት ምክንያት የሆኑ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሁሉ አፈራረሰ፡፡ በቤቴል ያደረገውን ሁሉ በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ፈጸመ፡፡
20በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ያገለግሉ የነበሩትንም የአሕዛብ ካህናት ሁሉ አረዳቸው፡፡ በመሠዊያዎቹም ላይ አጥንቶቻቸውን አቃጠለ፡፡ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡
21ከዚያም ንጉሥ ኢዮስያስ በቃል ኪዳን መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የፋሲካ በዓል ያከብሩ ዘንድ ሕዝቡን አዘዘ፡፡
22መሳፍንት የሕዝቡ ገዢዎች ከነበሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን በማናቸውም የእስራኤል ወይም የይሁዳ ነገሥታት አማካይነት ይህንን የመሰለ የፋሲካ በዓል ተከብሮ አያውቅም፡፡
23ነገር ግን ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የእግዘአብሔር ፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ተከበረ፡፡
24ሊቀ ካህናቱ ኬልቂያስ በቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው ሕግ ሁሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማሰብ፣ ንጉሥ ኡዮስያስ ከኢየሩሳሌምና ከሌላውም የይሁዳ ከተማ ሁሉ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ሁሉ የቤተ ሰብ አማልክት ጣዖቶችንና ሌሎችም አረማዊ የአምልኮ መፈጸሚያ ዕቃዎችን ሁሉ አስወገደ፡፡
25ለኦሪት ሕግ በመታዘዝ በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኃይሉ እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደ ንጉሥ ኢዮስያስ ያለ ከእርሱም በፊት ሆነ ከእርሱ በኋላ ከቶ አልነበረም፡፡
26ይሁን እንጂ ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ምናሴ ባደረገው ክፉ ነገር ምክንያት በይሁዳ ላይ የነደደው የእግዚአብሔር ቁጣ እስከ አሁን ድረስ ገና አልበረደም ነበር፡፡
27ስለዚህ እግዚብሔር እንዲህ አለ፡- በእስራኤል ላይ ያደረግኹትን ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ አደርጋለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ሕዝብ ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኳትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራል ብዬ የነበረውንም ቤተ መቅደስ እተዋለሁ፡፡
28ንጉሥ ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
29በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ኒካዑ የተባለው የግብጽ ንጉሥ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመርዳት ሠራዊቱን እየመራ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተጓዘ፡፡ ንጉሥ ኢዮስያስም መጊዶ ላይ የግብጽን ሠራዊት ለማገድ ጦርነት ገጥሞ በዚያ ውጊያ ላይ ተገደለ፡፡
30አገልጋዮቹም ባለሥልጣኖች ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እዚያ በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ የይሁዳም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን መረጡ፣ በአባቱም ፈንታ አነገሡት፡፡
31ኢዮአክስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም አሚጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፡፡
32ኢዮአክስ የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡
33እርሱንም ኒካዑ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ኢዮአክስ በኢየሩሳሌም እንዳይነግሥ በሐማት ምድር በምትገኘው በሪብላ አስሮ ይሁዳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ብር ሠላሳ አራት ኪሎ ወርቅ ግብር እንዲከፍል ባደረገው ጊዜ የኢዮአክስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ፡፡
34ንጉሥ ኒካዑ የኢዮአክስ ልጅ ኤልያቄም በአባቱ በኢዮስያስ ፈንታ ተተክቶ በይሁዳ እንዲነግሥ አደረገ፡፡ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፡፡ ኢዮአክስ በንጉሥ ኒካዑ ተማርኮ ወደ ግብጽ ተወሰደ፤ በዚያም ሞተ፡፡
35ኢዮአቄም ለግብጽ ንጉሥ ለኒዑዑ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንደየችሎታቸው በሕዝቡ ላይ ግብር ጣለ፡፡
36ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ዘቢዳ ተብላ የምትጠራ የሩማ ከተማ ተወላጅ የሆነው የፈዳያ ልጅ ነበረች፡፡
37ኢዮአቄም የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡