መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 25

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ናቡከደነፆር መላው ሠራዊቱን አስከትቶ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ ዐሥረኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ከባቢሎን መጥቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ወታደሮቹ ከከተማይቱ ውጪ ሰፍረው ዙሪያውን የሚከብብ አጥር ሠሩ፡፡
2ከበባው እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዓመት ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆየ፡፡
3ስለዚህም አራተኛው ወር በገባ በዘጠነኛው ቀን ራቡ በጣም ስለ ጸና ሕዝቡ የሚመገበው እንዳችም ምግብ አልነበረም፡፡
4ከዚያም የከተማይቱ ቅጥር ተጣሰ፤ የባቢሎን ወታደሮች ከተማይቱን ዙሪያውን ከበው በመያዝ ቢጠብቁም እንኳ የይሁዳ ንጉሥ ወታደሮች በሌሊት አምልጠው ወጡ፤ ወደ ንጉሡ የአትክልት ቦታ ከሚያስገባው መንገድ ተነሥተው ሁለቱን ቅጥሮች በሚያያይዘው የቅጥር በር በኩል በማለፍ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ ሸሹ፡፡
5ነገር ግን የከላደውያን ሠራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ አሳደደው፡፡ ወታደሮቹም ጥለውት ሸሹ፡፡
6ሴዴቅያስ ተይዞ በሪብላ ከተማ ወደሚገኘው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ተወሰደ፡፡ በዚያም ፍርድ አስተላለፉበት፡፡
7ሴዴቅያስም ዐይኑ እያየ ልጆቹ በፊቱ ታረዱ፡፡ ከዚህም በኋላ ናቡከደነፆር የሴዴቅያስን ዐይኖች አውጥቶ አሳወረው፤ እጆቹንም በነሐስ ሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፡፡
8ናቡከደነፃር በባቢሎን በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፣ አምስተኛው ወር በገባ በሰባተኛው ቀን ናቡዘረዳን ተብሎ የሚጠራው የናቡከደነፆር የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡
9እርሱም ቤተ መቅደሱን፣ ቤተ መንግሥቱን፣ በከተማው የሚኖሩትን የታላላቅ ሰዎች ቤት፣ በከተማው ውስጥ የሚገኙትንም ሌሎች ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፡፡
10በክብር ዘቡ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ወታደሮች በሙሉ የኢየሩሳሌምን ዙሪያ አጥር ደመሰሱ፡፡
11ከዚህ በኋላ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ቀርተው የነበሩትንና ሌሎችን ሰዎች እንዲሁም ከድተው ወደ ባቢሎናውያን የተጠጉትን ሁሉ ምርኮ አድርጎ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፡፡
12ነገር ግን ምንም ሀብት የሌላቸውን የመጨረሻ ድኾች አትክልት ኮትኳቾችና መሬት አራሾች እንዲሆኑ በይሁዳ ምድር ትቶአቸው ሄደ፡፡
13ባቢሎናውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን የነሐስ አምዶች፣ ባለ መንኮራኩር የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከነሐስ የተሠራውን ታላቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰባበሩ፤ ነሐሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱት፡፡
14እነርሱም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ መኮስተሪያዎችን፣ የዕጣን ማስቀመጫዎችንና ከነሐስ የተሠሩ የቤተ መቅደስ መገልገያ ዕቃዎችን ሁሉ ወሰዱ፡፡
15ጽናዎችንና ዱካዎችን ከብርና ከወርቅ የተሠሩ በመሆናቸው ወሰዱአቸው፡፡
16ንጉሥ ሰሎሞን ለቤተ መቅደስ ያሠራቸውን ሁለቱን አምዶች፣ ባለመንኮራኩር የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ታላቁን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎቸ፣ በክብደታቸው ምክንያት ሊመዝኑአቸው አልቻሉም፡፡
17አንዱ አምድ ስምንት ሜትር ነበረው፤ ጉልላቱ ከነሐስ የተሠራ ነበር፤ የጉልላቱም ቁመት አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በዙሪያውም ከነሐስ በተሠራ መረብ ላይ የሮማን ፍሬ ቅርጽ የመሰለ ባለፈርጥ ጌጥ ተሠርቶበት ነበር፡፡
18የሠራዊቱ አዛዥ ናቡዘረዳን ሊቀ ካህናቱን ሠራያን በማዕርግ የእርሱ ምክትል የሆነውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የቤተ መቅደስ ዘበኞች እስረኛ አደርጎ ወሰዳቸው፡፡
19ከከተማይቱም የወታደሮች አዛዥ የሆነው አንድ ባለሥልጣን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በከተማይቱ የነበሩትን አምስቱን የንጉሥ አማካሪዎች፣ የአገሩን ሕዝብ ለወታደርነት ይመለምል የነበረው መኮንንና ሌሎችንም ስልሳ ሰዎችን ወሰደ፡፡
20ከዚያም ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ በሐማት ግዛት በምትገኘው በሪብላ ከተማ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወሰዳቸው፡፡
21የባቢሎንም ንጉሥ በዚያ እነርሱን አስደብድቦ በማሠቃየት በሞት ቀጣቸው፡፡ በዚህም ዐይነት የይሁዳ ሕዝብ ከአገራቸው ተማርከው ተወሰዱ፡፡
22የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የሳፋን የልጅ ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ወደ ባቢሎን ተማርከው ሳይወሰዱ ለቀሩት ሰዎች ሁሉ ኃላፊ ይሆን ዘንድ የይሁዳ ገዢ አድርጎ ሾመው፡፡
23እጃቸውን ያልሰጡ የይሁዳ የጦር መኮንኖችና ወታደሮች የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን ገዢ አድርጎ እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ ወደ ምጽጳ መጥተው ከእርሱ ጋር ተገናኙ፤ እነዚህም የጦር መኮንኖች የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያ ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋ ከተማ ተወላጅ የሆነው የተንሑሜት ልጅ ሠራያና የማዕካ ተወላጅ የሆነው ያእዛንያ ነበሩ፡፡
24ጎዶልያስ እነርሱንና ወታደሮቻቸውን እንዲህ አላቸው፤ ከባቢሎናውያን ባለሥልጣኖች የተነሣ ምንም ዐይነት ፍርሃት ሊያድርባችሁ እንደማይገባ ቃል እገባላችኋለሁ፤ በዚህች ምድር ኑሮአችሁን መሥርቱ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ገብሩ፤ ይህን ብታደርጉ ሁሉ ነገር ይቃናላችኋል፡፡
25ነገር ግን በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የነበረውና የኤሊሳማ የልጅ ልጅ የሆነው የናታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ምጽጳ ሄደ፤ በዚያም አደጋ ጥሎበት ጎዶልያስን ገደለው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተገኙትን አይሁዳውያንንና ባቢሎናውያንን ሁሉ ገደለ፡፡
26ከዚህም የተነሣ ባቢሎናውያንን ስለፈሩ እስራኤላውያን ሀብታሞችና ድኾች ከጦር ሠራዊት መኮንኖች ጋር በአንድነት ተነሥተው ወደ ግብጽ ሸሹ፡፡
27ዮርማሮዴቅ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ከእስራት በመፍታት ምሕረት አደረገለት፤ ይህም የሆነው ዮአኪን ተማርኮ በሄደ በሠላሳ ሰባት ዓመቱ፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር በሃያ ሰባተኛው ቀን ነበር፡፡
28ዮርማሮዴቅ ለዮአኪን መልካም ነገር አደረገለት፤ እንደ እርሱ ተማርከው በባቢሎን በስደት ከሚኖሩ ነገሥታት ሁሉ የላቀ የክብር ማዕረግ ሰጠው፡፡
29ስለዚህም ዮአኪን በእስር ቤት የነበረውን ልብስ ለውጦ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማዕድ እንዲመገብ ተፈቀደለት፡፡
30እርሱም በኖረበት ዘመን ሁሉ በየቀኑ ለማናቸውም ለሚያስፈልገው ነገር ያውለው ዘንድ የዘወትር ቀለብ ይሰጠው ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።