መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 22

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የባሱሮት ከተማ ተወላጅ የሆነው የአዳያ ልጅ ነበረች፡፡
2ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፡፡ ወደ ግራም ቀኝም አላለም፡፡
3ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የሜሶላም የልጅ ልጅ፣ የኤዜልያስ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱን ጸሓፊ ሳፋንን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፡፡
4«ኬልቂያስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደህ፣ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያህል ገንዘብ ከሕዝቡ እንደሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ እንድትመጣ አለው፡፡
5የመቅደሱን እድሳት ለመቆጣጠር ለተሾሙት ሰዎች ያስረክቡ፤ እነርሱም የተረከቡትን ገንዘብ ቤተ መቅደሱን ለሚጠግኑ፣ ለአናጢዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይክፈሉ፡፡
6እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሳንቃዎችንና የተጠረቡ ድንጋዮችን ይግዙ፡፡
7ነገር ግን የሥራው ኃላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቆጣጠር አያስፈልግም፡፡»
8ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለኬልቂያስ ሰጠው፤ ኬልቂያስም «የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ» ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፡፡
9ጸሐፊውም ሄደና «አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኃላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል» ሲል አስረዳ፡፡
10ከዚያም ጸሐፊው ሳፋን ለንጉሡ «ካህኑ ኬልቂያስ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ» ነው አለው፡፡
11ንጉሡም፣ የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፡፡
12እርሱም ለካህኑ ለኬልቂያስ፣ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአኪቃም፣ የሚክያስ ልጅ ለሆነው ለዓክቦር፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፡፡
13«እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቆጥቶአል፡፡»
14ካህኑ ኬልቂያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦር፣ ሳፋንና ዓሳያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሕልዳና ተብላ የምትጠራውን ነቢይቱን የሴሌም ሚስት ለመጠየቅ ሄዱ። የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው የቤተ መቅደስ አልባሳት ኃላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት፡፡
15እርስዋም እንዲህ አለቻቸው፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፡- ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፡-
16«እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፡፡
17እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖታት ሁሉ እኔን አስቆጥተውኛል፤ ቁጣዬም አይበርድም፡፡
18እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‹አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፡-
19ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድህ፣ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፡፡
20ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣውን ቅጣት በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ፡፡» ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።