መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 21

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ምናሴ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ኀምሳ አምስት ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሐፍሴባ ተብላ ትጠራ ነበረ፡፡
2እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሕዛብን አሳፋሪ ልማድ በመከተል ምናሴ የሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
3ምናሴ አባቱ ሕዝቅያስ አጥፍቶአቸው የነበሩትን የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች እንደገና እንዲሠሩ አደረገ፡፡ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ባደረገውም ዐይነት ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሠዊያዎችን፣ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስልን ሠራ፤ የሰማይ ከዋክብትንም አመለከ፡፡
4እግዚአብሔር እንዲመለክበት ባዘዘው ስፍራ ማለትም በቤተ መቅደስ ውስጥ አረማዊ መሠዊያዎችን አቆመ፡፡
5በሁለቱም የቤተ መቅደሱ አደባባዮች የሰማይ ከዋክብት የሚመለኩባቸውን መሠዊያዎች ሠራ፡፡
6የገዛ ልጁንም መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እርሱም ራሱ ሟርተኛና አስማተኛ ሆኖ ከጠንቋዮችና ከሙታን ጠሪዎች ምክርን ይጠይቅ ነበር፤ በዚህም ሁሉ አድራጎቱ ታላቅ ኃጢአት በመሥራቱ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሣ፡፡
7በቤተ መቅደሱም ውስጥ የአሼራን ምስል አኖረ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን «ይህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እኔ ለዘለዓለም እንድመለክበት ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ የመረጥኩት ስፍራ ነው፡፡
8የእስራኤል ሕዝብ ትእዛዞቼን ቢጠብቁና ለአገልጋዬ ለሙሴ የሰጠሁትንም ሕግ ቢፈጽሙ፣ ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ከዚህች ምድር ተነቃቅለው እንዲጠፉ አላደርግም» ሲል ነግሮአቸው የነበረው ነው፡፡
9የይሁዳ ሰዎች ግን ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ይልቁንም ምናሴ እስራኤላውያን ወደፊት እየገፉ ሲመጡ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸው ሕዝቦች ይፈጽሙት ከነበረው ይበልጥ ወደ ክፉ ኃጢአት መራቸው፡፡
10ስለዚህ እግዚአብሔር በአገልገጋዮቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፡-
11«የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አሳፋሪ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ቀድሞ ከነዓናውያን ይፈጽሙት ከነበረው ሁሉ የከፋ ነው፤ በሠራቸውም ጣዖቶች የይሁዳን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ፡፡
12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የመጣው በጣም ከባድ መቅሰፍት ይህ ነው፤ ስለ እርሱም የሚሰማ ሰው ሁሉ በድንጋጤ ጆሮው ጭው ይላል፡፡
13ሰማርያንና የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ከነዘሮቹ እንደ ቀጣሁ ኢየሩሳሌምንም እቀጣለሁ፤ ሳሕን ከተወለወለ በኋላ ተደፍቶ እንደሚቀመጥ፣ እኔም ኢየሩሳሌምን ከኃጢአት አጸዳታለሁ፡፡
14ከጥፋት የተረፈውን ሕዝቤን ለጠላቶቹ ተላልፎ እንዲሰጥ እተወዋለሁ፤ እርሱም ይማረካል፤ ንብረቱም ይዘረፋል፡፡
15በእነርሱም ላይ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ኃጢአት ሠርተው እኔን በማሳዘናቸውና ቁጣዬን በማነሣሣታቸው ነው፡፡»
16ከዚህም በተጨማሪ ምናሴ የይሁዳን ሕዝብ ወደ ጣዖት አምልኮና እግዚአብሔርን ወደሚያሳዝን ኃጢአት ከመምራት አልፎ፣ ንጹሓን የሆኑትን ብዙ ሰዎችን በመፍጀት የኢየሩሳሌምን መንገዶች በደም እንዲጥለቀለቁ አድርጎአል፡፡
17ምናሴ ያደረገው ሌላው ነገርና የፈጸመው ኃጢአት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሓፍ ተመዝቦ ይገኛል፡፡
18ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱ ግቢ «የዖዛ አትክልት ስፍራ» ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አሞን ነገሠ፡፡
19አሞን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሜሶላም ተብላ የምትጠራ የዮጥባ ከተማ ተወላጅ የሐሩስ ልጅ ነበረች፡፡
20አሞን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፡፡
21የአባቱንም መጥፎ አርአያነት ሁሉ ተከተለ፤ አባቱ ይሰግድላቸውና ያመልካቸው የነበሩትንም ጣዖቶች ሁሉ አመለከ፡፡
22የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርንም ተወ፤ እግዚአብሔርንም አልተከተለም፡፡
23አገልጋዮቹ ባለሥልጣኖችም በአሞን ላይ አድመው በራሱ ቤት ውስጥ ገደሉት፡፡
24የይሁዳም ሕዝብ የአሞንን ገዳዮች ደምስሰው ልጁን ኢዮስያስን አነገሡ፡፡
25አሞን ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
26አሞን «የዖዛ አትክልት ስፍራ» ተብሎ በሚጠራው መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።