1በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፡፡ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጎበኘው ሄዶ፡- «እግዚአብሔር ‹ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ሁሉን ነገር አስተካክል› ብሎሃል» ሲል ነገረው፡፡
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፡-
3«እግዚአብሔር ሆይ! በታማኝነትና በቅንነት እንዳገለገልኩህ፣ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር ለማድረግ ዘወትር እጥር እንደነበር ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ!» እያለ በመጸለይ ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡
4ኢሳይያስ ከንጉሡ ፊት ወጥቶ የቤተ መንግሥቱን መካከለኛ አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊት፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፡-
5«ሕዝቤን ወደሚመራው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ተመልሰህ በመግባት እንዲህ በለው፡- ‹እኔ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም ተመልክቻለሁ፤ እኔ እፈውስሃለሁ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፡፡
6በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ በመታደግ አድናለሁ፡፡ ስለ ክብሬና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ከተማይቱን በመከላከል እጠብቃታለሁ፡፡”
7ስለዚህ ኢሳይያስ የንጉሡን አገልጋዮች «የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ አምጡልኝ» ብሎ አመጡለት፤ በቁስሉ ላይ ባደረጉለት ጊዜ የሕዝቅያስ ቁስል ተፈወሰ፡፡
8ንጉሥ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን «እግዚአብሔር እንደሚፈውሰኝና ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ እንደምችል በምን ምልክት ዐውቃለሁ?» ሲል ጠየቀው፡፡
9ኢሳይያስም «እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ ራሱ ምልክት ይሰጥሃል፤ እንግዲህ አሁን የምትመርጠው ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ነው? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?» ሲል ጠየቀው፡፡
10ሕዝቅያስም «ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ማድረግ ይቀላል፤ ስለዚህ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርግልኝ» አለው፡፡
11ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ንጉሥ አካዝ ባሠራው ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ፡፡
12በዚያኑ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ መታመሙን ሰምቶ ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት፡፡
13ሕዝቅያስ መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ፣ ብሩንና ወርቁን፣ ቅመማ ቅመሙንና ሽቶውን፣ የጦር መሣሪያውንም ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ያላሳያቸው አንድም አልነበረም፡፡
14በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ፣ «እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?» ብሎ ጠየቀው፡፡ ሕዝቅያስም «እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው» ሲል መለሰለት፡፡
15ኢሳይያስም «በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ» ሲል ጠየቀው፡፡ ሕዝቅያስም «ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤቱ ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው አንድም ነገር የለም» አለ፡፡
16ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፡- «ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣
17‹የቀድሞ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ድረስ ያከማቹት፣ በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርም።
18ከዘሮችህም አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡»
19ንጉሥ ሕዝቅያስም በተለይ በእርሱ ዘመን በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለው ስለ ተረዳ «ከእግዚአብሔር ተልከህ የተናገርከኝ ቃል መልካም ነው» ሲል መለሰ፡፡
20ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የጀግንነት ሥራው ጭምር፣ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ እንዴት እንደ ሠራና ወደ ከተማይቱ ውሃ ለማምጣት ያስቆፈረው የመሬት ውስጥ ቦይ አሠራር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
21ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ፡፡