1ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡
2ወዲያውም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነውን ኤልያቄምን፣ የቤተ መንግሥቱን ጸሐፊ ሳምናስንና ሽማግሌዎች ካህናትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ራሳቸው ማቅ ለብሰው ነበር፡፡
3ለኢሳይያስም እንዲነግሩት የላከው መልእክት ከዚህ የሚከተለው ነው፡- ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፡፡
4የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢው ይቀጣ ይሆናል። ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ለተረፉት ሰዎች እባክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡
5የንጉሥ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፣
6ኢሳይያስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብላችሁ ለንጉሣችሁ ንገሩት አላቸው፣ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ሲሰድቡኝ ስለ ሰማችሁት ቃል አትፍሩአቸው፡፡
7እነሆ እኔ የሽብር ወሬ የሚያሰማ መንፈስ እልክበታለሁ፤ ስለዚህ ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሄድ፣ እዚያ በገዛ ምድሩ በሰይፍ ተመትቶ እንዲሞት አደርጋለሁ፡፡
8ከዚያ የአሦር የጦር አዛዥ፣ የአሦር ንጉሥ ከሰፈሩ ከለኪሶ ተነሥቶ ልብናን ሊያጠቃ እንደ ሄደ በመስማቱ እርሱም ወደ ለኪሶ ሄደ፡፡
9በኢትየጵያ ንጉሥ በቲርሃቅ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን ሰናክሬም ሰማ፤ ወዲያውኑ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኞች እጅ ላከ፡-
10«የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ፣ የምትታመንበት አምላክ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አትወድቅም ብሎ አያታልልህ፤
11የአሦር ነገሥታት አገሮችን ሁሉ እንዴት ፈጽመው እንደ ደመሰሱ ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?
12የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፣ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር የሚኖሩትን የዓዴንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ከአማልክቶቻቸው አንድ እንኳ ሊያድናቸው ችሎአልን?
13ለመሆኑ የሐማት፣ የአርፋድ፣ የሴፈርዋይም፣ የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት የት አሉ?»
14ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞች ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው፡፡
15እንዲህ ሲልም ጸለየ፡- «የሠራዊት አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በኪሩቤል ላይ የተቀመጥህ፣ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ የዓለምንም መንግሥታት የምትመራ አንተ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህ አንተ ነህ፡፡
16አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የደረሰብንን ነገር ሁሉ ተመልከት፣ አንተን ሕያው የሆነከውን አምላክ በመስደብ ሰናክሬም የተናገረውን የዛቻ ቃል ሁሉ አድምጥ፤
17እግዚአብሔር ሆይ፣ የአሦር ነገሥታት ብዙ ሕዝቦችንና ምድራቸውን መደምሰሳቸው እርግጥ ነው፡፡
18ከእንጨትና ከድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ የሰው እጅ ሥራ እንጂ አማልክት ስላልነበሩ በእሳት ላይ ጥለው አጠፉአቸው፡፡
19እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፣ አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም መንግሥታት ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦር ንጉሥ አድነን፡፡»
20ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፡- «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‹ስለ አሦር ንጉሠ ነገሥት ስለ ሰናክሬም ዛቻ ወደ እኔ የጸለይከውን ጸሎት ሰምቻለሁ፡፡
21ስለ እርሱ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፡- የጽዮን ድንግል ትንቅሃለች፤ ታፌዝብሃለች፤ አንተ እየሸሸህ ሳለህ፣ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች ከኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል፡፡
22የሰደብከውና የተዳፈርከው ማንን ነው? ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው በማን ላይ ነው? በትዕቢትስ ዐይንህን ያነሳኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡
23በመልእክተኞችህ አማካይነት፣ በእግዚአብሔር ላይ ስድብን አብዝተሃል፤ ‹በሠረገሎቼ ከፍተኛ ወደ ሆኑት ተራራዎች፣ ወደ ሊባኖስ ጫፍ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹን የሊባኖስ ዛፎችዋንና ምርጦቹን ዝግባ ቆርጬአለሁ፤ ወደ ዳርቻዋና ውብ ወደሆነው ጫካዋ ደርሼአለሁ፤› ብለሃል፡፡
24‹በባዕድ አገር ጉድጓድ ቆፍሬ ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ኮቴዎች የግብጽን ወንዞች አድርቄአለሁ› ብለህ ታብየሃል፡፡
25ሰናክሬም ሆይ! አስተውል፤ ጥንቱኑ እኔ እንደ ወሰንኩት፣ በቀድሞው ዘመን እንዳቀድኩትና አሁን በሥራ ላይ ባዋልኩት መሠረት የተጠናከሩ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እንድትለውጥ ያደረግኹህ እኔ መሆኔን አልሰማህምን?
26የእነዚያ አገር ነዋሪዎች ኃይላቸው ተዳክሞ፣ ተስፋ በመቁረጥ እንዲያፍሩ ተደርገው በምሥራቅ ነፋስ እንደተመቱ የመስክ አትክልቶች፣ እንደ ቀጨጩ አረንጓዴ ቡቃያዎች፣ በጣራ ላይ እንደበቀሉ ሣር ናቸው፡፡
27እኔ ግን መነሣትህንና መቀመጥህን፣ መውጣትህንና መግባትህን፣ እንዲሁም እኔን መቃወምህን ዐውቃለሁ፡፡
28በእኔ ላይ ያለው ተቃውሞህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ በአፍንጫህ ትናጋ፣ በአፍህም ልጓም አድርጌ፣ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ፡፡»
29ከዚያም ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን አንዲህ አለው፤ «ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፣ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የሚበቅለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ፤
30በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰድዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ፤
31ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ተራራ የተረፉት ወገኖች ይወጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ይፈጽማል፡፡»
32ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሠ ነገሥት የተናገረውም ቃል ይህ ነው፡- «ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርስዋ አይቀርብም፤ በአፈር ቁልልም አትከበብም፡፡
33እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡
34ስለ ራሴ ክብርና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ ተከላክዬ አድናታለሁ፡፡»
35በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ፡፡
36ስለዚህ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ወደ ኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመለሰ፡፡
37ከዕለታት በአንዱ ቀን ናሳራክ በሚል ስም በሚጠራው ባዕድ አምላኩ ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ፣ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አደራሜሌክና ሳራሳር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶን የተባለው ነገሠ፡፡