መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞአብ በአስራኤል ላይ ዐመፀ፡፡
2በዚያን ጊዜ የአስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ ክፉኛ ቆስሎ ነበር፤ እርሱም እኔ ከዚህ ሕመም እድን እንደሆነ በፍልስጥኤም የአቃሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡል ጠይቁልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፡፡
3ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔሌዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ ነውን?
4ስለዚህ እግዚአብሔር እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም፤ ከተኛህበት አልጋም አትነሣም፤ ብሎሃል በሉት፡፡ ከዚያም ኤልያስ ትቶ ሄደ፡፡
5መልእተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ? ሲል ጠየቃቸው፡፡
6እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድን ነው? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም፤ ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም!
7ንጉሡም በመንገድ ያገኛችሁት ይህንን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው? ሲል ጠየቃቸው፡፡
8እነርሱም ጠጉራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው ሲሉ መለሱለት፡፡ ንጉሡም እርሱማ ኤልያስ ነው! አለ፡፡
9ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኮንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፡፡ መኮንኑም ኤልያስን በአንድ ኮረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል አለው፡፡
10ኤልያስም እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ አለው፤ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኮንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ፡፡
11ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኮንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል አለው፡፡
12ኤልያስም እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኮንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ፡፡
13ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኮንን ላከ፤ ይህኛው መኮንን ግን ወደ ኮረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን፤ ሕይወትችንንም ከሞት አድን፣
14ሌሎቹን ሁለት መኮንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ፡፡
15የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ አለው፡፡ ስለዚህም ኤልያስ ከመኮንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፡፡
16እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን እንዲጠይቁ መልእክተኞችን የላክህ በእስራኤል አምላክ እንደሌለ በመቁጠርህ ነውን? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ሳትወርድ ትሞታለህ እንጂ አትድንም አለው፡፡
17ስለዚህ እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት አካዝያስ ሞተ፡፡ አካዝያስ ወንዶች ልጆች ስላልነበሩት በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ወንድሙ ኢዮራም ነገሠ። ይህም የሆነው የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነበር፡፡
18ንጉሥ አካዝያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።