መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
2ሕዝቅያስም ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፡፡ እርሱም በኢያሩሳሌም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም አቢያ የምትባል የዘካርያስ ልጅ ነበረች፡፡
3ሕዝቅያስም የአባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
4የአሕዛብን የማምለክያ ስፍራዎች አስወገደ፤ የድንጋይ ዐምዶችንም ሰባብሮ አጠፋ፤ ኣሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የተቀረጹትን ምስሎች ሁሉ አፈረሰ፡፡ ሙሴ ከነሐስ ሠርቶት የነበረውን ኔሑሽታን ተብሎ የሚጠራውን የእባብ ምስል ሰባብሮ አደቀቀ፤ ምክንያቱም እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን ለእርሱ ዕጣን ያጥኑለት ነበር፡፡
5ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ተማመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ ወዲህ እርሱን የመሰለ ሌላ ንጉሥ በይሁዳ አልተነሣም፡፡
6ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ ከእግዚአብሔር መንገድ የራቀበት ጊዜ የለም፤ ለሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽም ነበር፡፡
7ስለዚህም እግዚአብሔር ከሕዝቅያስ ጋር ስለነበረ የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም በአሦር ንጉሠ ነገሥት ላይ ዐምፆ ለእርሱ መገዛትን አሻፈረኝ አለ፡፡
8ፍልስጥኤማውያንንም ድል ነሥቶ ከትንሽ እስከ ታላቅ የተመሸጉ ከተማ ጋዛንና በዙሪያው የሚገኘውን ግዛት፣ የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ አጠቃ፡፡
9ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ማለትም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፡፡
10በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ሆሴዕም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር፡፡
11የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹን በአላሔ ከተማ፣ ጥቂቶቹን በጋዛ አውረጃ በሚገኘው በአቦር ወንዝ አጠገብ፣ ሌሎቹን ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡
12ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነበር፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ለመስማትም ሆነ ሕጉን ለመጠበቅ አሻፈረን አሉ፡፡
13ከዚያም ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ያዘ፡፡
14ስለዚህም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በለኪሶ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም፣ እኔ በድያለሁ፤ እባክህን እኔን ተወኝ፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እልክልሃለሁ ሲል መልእክት ላከ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ለይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እኔ የምፈልገው ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንድትልክልኝ ነው ሲል መለሰለት፡፡
15ስለዚህም ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥተ ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፡፡
16እንዲሁም በእግዚዚብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ፡፡
17ነገር ግን የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከለኪሶ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ሠራዊቱም ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፡፡ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኩሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፡፡
18ከዚያ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም አገልጋዮቹ የሆኑ ሦስት ባለሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፡፡ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነው የኬልቂያስ ልጅ ኤልያቄም፣ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሳምናስና የቤተ መዛግብት ኃላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ነበሩ።
19ስለዚህም የአሦር ዋና የጦር አዛዥ እንዲህ አላቸው፡- ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፣ ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፡- እንደዚህ የተማመንክበት ነገር ምንድን ነው?
20በጦርነት የሚረዳ ኃይል እንዳለህ የተናገርከው ከንቱ ቃላት ናቸው፤ በእኔ ላይ ለማመጽ የቻልከው በምን ተማምነህ ነው?
21የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኮዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቆስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲህ ነው’ ሲል ተናገረ፡፡
22የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፡- አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ ታስብ እንደሆነ፣ ይህ እንዳይሆን አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው ብለህ ወስነሃል፡፡
23አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ አንደ ሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ፡፡
24አንተ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኮንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
25እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል፡፡
26ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ ይህን የጦር አዛዥ ትርጉሙን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጥር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን አሉት፡፡
27የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣቸሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት ለሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆነ እኔ የምናገረውን በቅጥር ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት እንድናገር አልላከኝምን? ሲል መለሰላቸው፡፡
28ከዚያም የአሦር የጦር አዛዥ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ ጮኸ፡- የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ፤
29በሕዝቅያስ አትታለሉ፤ እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም፡፡
30ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙት፡፡
31ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጉድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፡፡
32ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር የሞላባት ናት። ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፡፡ ስለዚህ ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ይታደጋችኋል” እያለ በመስበክ አያሙኛችሁ፡፡
33ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን?
34ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሴፈርዋይ፣ የሄናና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን?
35የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ንጉሠ ነገሥቶቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?
36ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፡፡
37ከዚያም ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን የጦር አዛዥ የተናገረውን አስረዱት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።