1አካዝ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በሰማርያ ዘጠኝ ዓመት እስራኤልን ገዛ፡፡
2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፡፡ ሆኖም እርሱ ያደረገው ኃጢአት ከእርሱ በፊት የነበሩ የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙት አልነበረም፡፡
3የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ጦርነት በገጠመው ጊዜ ተሸንፎ ሆሴዕ እጁን በመስጠት በየዓመቱ ይገብርለት ጀመር፡፡
4ነገር ግን ከጥቂት ዓመቶች በኋላ ንጉሥ ሆሴዕ ሴጎር ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ግብጽ ንጉሥ መልእክተኞች በመላክ ይረዳው ዘንድ ጠየቀው፤ በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ይሰጠው የነበረውንም ግብር አቆመ፡፡ ስልምናሶር ይህን በሰማ ጊዜ ሆሴዕን አስይዞ ወህኒ ቤት አስገባው፡፡
5ከዚህ በኋላ ስልምናሶር አገሪቱን ወርሮ ሰማርያን ለሦስት ዓመት ከበባት፡፡
6ከዚያም ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ስልምናሶር ድል አድርጎ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰዳቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን በአላሔ ከተማ፣ ጥቂቶቹን በጎዛን አውራጃ ውስጥ በሚገኘው በአቦር ወንዝ አጠገብ፣ እንዲሁም ሌሎቹን በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡
7ይህም ምርኮ የሆነው እስራኤላውያን በሠሩት ኃጢአት ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ በመታደግ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ኃጢአት በመሥራት በማሳዘናቸው ነበር፡፡ ሕዝቡም ባዕዳን አማልክትን አመለኩ፡፡
8ሕዝቡም ከፊታቸው ያጠፋላቸውን የአሕዛብን መጥፎ ልማድ ተከተሉ፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት ያሠራጩትን መጥፎ ልማድ ተቀባዮች ሆኑ፡፡
9እስራኤላውያንም አምላካቸው እግዚአብሔር የሚጠላውን ነገር ሁሉ አደረጉ፡፡ ከዘብ ጠባቂዎች ማማ አንሥቶ እስከ ትልቅ ከተማ ድረስ በገጠር ከተሞቻቸው ሁሉ በየኮረብታዎቹ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፡፡
10በኮረብቶች ሁሉ ላይና በየዛፉ ጥላ ሥር የድንጋይ አምዶችንና አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስሎች አቆሙ፡፡
11እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያስወጣቸውን የአረማውያን ሕዝብ ልማድ በመከተል በአሕዛብ መሠዊያዎች ሁሉ ላይ ዕጣን አጠኑ፤ በዚህም ክፉ ሥራቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፤
12እግዚአብሔርም እንዳያደርጉ የተናገራቸውን ጣዖታትን አመለኩ፡፡
13እግዚአብሔርም እስራኤልንና ይሁዳን የሚያስጠነቅቁ መልእክተኞችንና ነቢያትን በመላክ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ሁሉ ተመለሱ፤ አገልጋዮቼ በሆኑት ነቢያትና ባለ ራዕዮች አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተም በሰጠሁት ሕጎችና ትእዛዞች የተጻፈውን ሥርዓቱን ጠብቁ ብሎ ነግሮአቸው ነበር፡፡
14እነርሱ ግን መታዘዝ አልፈለጉም፤ በአምላካቸው በእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልከኞች ሆኑ፡፡
15የሰጣቸውንም ድንጋጌ አልተቀበሉም፤ ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ ቸል አሉ፤ ለከንቱ ጣዖቶች በመስገድ ራሳቸውም ከንቱዎች ሆኑ፤ የእነርሱን መጥፎ ምሰሌነት እንዳይወርሱ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ ባለመስማት በዙሪያቸው የሚኖሩትን የአሕዛብ ልማድ ሁሉ ተከተሉ፡፡
16የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ቸል አሉ፡፡ የሚሰግዱላቸውን ከብረት የተሠሩ ሁለት ጥጆችን አቆሙ፡፡ እንዲሁም አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሠሩ፣ ለከዋክብትም ሰገዱ፣ ባዓል ተብሎ ለሚጠራውም ባዕድ አምላክ አገልጋዮች ሆኑ፡፡
17ለእነዚያም አሕዛብ አማልክት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፤ ከሙታን ጠሪዎችና ከጠንቋዮችም ምክር ጠየቁ፤ እግዚአብሔር ለሚጠላው ክፉ ነገር ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፡፡
18ስለዚሀም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ተቆጥቶ የይሁዳን መንግሥት ብቻ በማስቀረት እስራኤላውያንን ከፊቱ አስወገደ፡፡
19የይሁዳ ሰዎችም ቢሆኑ አምላካቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዞች አልጠበቁም ነበር፡፡ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ የተቀበሉትን ልማድ ተከታዮች ነበሩ፡፡
20ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሁሉ ተዋቸው፤ ከፊቱም እስኪወገዱ ድረስ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው፡፡
21እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከይሁዳ ከለየ በኋላ እስራኤላውያን የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምን መርጠው አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን እንዲተዉ በማድረግ አሠቃቂ ወደ ሆነ ኃጢአት መራቸው፡፡
22በአገልጋዮቹ ነቢያት ሁሉ አማካይነት እግዚአብሔር እስራኤልን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ እስራኤላውያን የኢዮርብዓምን ኃጢአት ሲሠሩ ኖሩ እንጂ ከዚያ አልራቁም፡፡
23ስለዚህ እስራኤላውያን ከአገራቸው ተማርከው በመወሰድ እስከ ዛሬ ድስ በአሦር ይኖራሉ፡፡
24የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን ኩታ፣ ዓዋና፣ ሐማትና ሴፈርዋይ ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ፡፡
25እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፡፡
26ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብረው የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው የሚል ወሬ ደረሰው፡፡
27ስለዚህ ንጉሠ ነገሥቱ ማርኮ ካመጣቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያ ተመልሶ በመሄድ የዚያች አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ ሲል አዘዘ፡፡
28ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤተል ተቀመጠ፤ በዚያ ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባቸው አስተማራቸው፡፡
29በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ፡፡
30በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኤርጌል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ አሲማት ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤
31የዓዋ ሕዝብ ኤልባዝርና ተርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክቶቻቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሴፈርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፡፡
32እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር፡፡ ከእያንዳዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፡፡
33በዚህ ዓይነት እግዚአብሔርን ማክበርና ማምለክ ጀመሩ፡፡ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክት ይሰግዱ ነበር፡፡
34ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን አያመልኩም ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፣ ሥርዓቶች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም፡፡
35እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፡- ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፣ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፣ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፡፡
36በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፡፡
37ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፣ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፡፡
38እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፡፡
39እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከኃይለኛው ጠላቶቻችሁ እጅ አድናችኋለሁ፡፡
40ነገር ግን እነዚያ ሕዝቦች ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ፡፡
41እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው፡፡