1የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
2አካዝም በሚነግሠበት ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፡፡ እርሱም የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት አልተከተለም፡፡ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ደስ የማያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
3ይልቁንም የእስራኤልን ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፡፡ የራሱን ልጅ እንኳ ሳይቀር ለጣዖታት የሚቃጠል መስዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ይህንንም ድርጊት የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት እግዚአብሔር ከእስራኤል ምድር ያስወገዳቸውን አሕዛብ ይሠሩት የነበረውን አስጸያፊ ድርጊት በመከተል ነበር፡፡
4አካዝ በየኮረብቶቹ ላይ በተሠሩት የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና በእያንዳንዱም ዛፍ ሥር መሥዋዕት በማቅረብ ዕጣን አጠነ፡፡
5የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል መጡ፤ ከበቧትም፡፡ ነገር ግን አካዝን ድል ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡
6በዚያን ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የኤላትን ከተማ አስመልሶ በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ በዚያ የነበሩትን አይሁድ አስወጣ፡፡ ከዚያም በኤላት የሰፈሩት ኤዶማውያን እስከ አሁንም በዚያ ይኖራሉ፡፡
7ስለዚህም ንጉሥ አካዝ ወደ አሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር «እኔ ለአንተ ታማኝ አገልጋይህ ነኝ፤ አደጋ ከጣሉብኝ ከሶርያና ከእስራኤል ነገሥታት እጅ መጥተህ እኔን አድነኝ» በማለት መልእክተኞችን ላከ፡፡
8አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት የተገኘውን ብርና ወርቅ ሰብስቦ ለዚሁ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት በማድረግ ላከለት፡፡
9ከዚያም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር የአካዝን ጥያቄ በመቀበል ዘምቶ ደማስቆን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፡፡ ንጉሥ ረአሶንንም ገደለ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ቂር ተብላ ወደምትጠራው ስፍራ ወሰደው፡፡
10ንጉሥ አካዝም ከንጉሠ ነገሥት ቴልጌልቴልፌልሶር ጋር ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ፡፡ በደማስቆም አንድ መሠዊያ አየ፡፡ ያንንም መሠዊያ በተመሳሳይ ሁኔታ መሥራት የሚያስችለውን ቅርጽ አዘጋጅቶ ለካህኑ ለኦሪያ ላከለት፡፡
11ስለዚህ ኦሪያ ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ንድፍ መሠረት መሠዊያ ሠራ፡፡
12ንጉሡም ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ መሠዊያውን ተመለከተ፤ ወደ መሠዊያው ቀርቦም መሥዋዕት አቀረበ፡፡
13በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠል የእንስሶች መሥዋዕትና የእህል መባ አቀረበ፡፡ የመባውን ወይን ጠጅና የኅብረት መሥዋዕት ደም አፈሰሰበት፡፡
14ከነሐስ ተሠርቶ ለእግዚአብሔር የተለየውም መሠዊያ በዚያ አዲስ መሠዊያ፣ በቤተ መቅደሱ መካከል ነበር፤ ያንንም መሠዊያ አስነሥቶ እርሱ ባሠራው በአዲሱ መሠዊያ በስተሰሜን በኩል አኖረው፡፡
15ከዚያም ካህኑን ኦሪያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ይህንን የእኔን ታላቅ መሠዊያ ማለዳ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በምሽት ለሚቀርበውም የእህል መባ ስለ ንጉሡና ስለ ሕዝቡ የሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ የሚቀርብበትና የሕዝቡ የወይን ጠጅ መባ የሚፈስበት እንዲሆን አድርግ፤ የሚሠዉትንም የእንስሳት ደም ሁሉ በእርሱ ላይ አፍስስ፤ ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ግን እኔ ራሴ የምፈልገውን ነገር የምጠይቅበት እንዲሆን አድርግ፡፡
16ካህኑም ኦሪያን ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው አደረገ፡፡
17ንጉሥ አካዝም በቤተ መቅደስ ውስጥ መገልገያ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ መንኩራኩሮች ቆርጦ ልሙጥ የሆነውን ነገር ከጎናቸው ወስደ፡፡ በእነርሱ ላይ የነበሩትንም የመታጠቢያ ሳሕኖች ወሰደ፤ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ከታች በኩል ተሸክመውት ከነበሩት ከነሐስ ከተሠሩት ከዐሥራ ሁለት የበሬ ቅርጾች ጀርባ ላይ አንሥቶ ከድንጋይ በተሠራ መሠረት ላይ አኖረው፡፡
18አካዝ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት የተነሣ በቤተ መቅደሱ የሠሩትን የሰንበት መግቢያ መንገድ ንጉሡ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በውጪው በኩል ከሚገባበት መግቢያ ጋር አስወገደው፡፡
19ንጉሥ አካዝ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
20አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በአባቶቹ መካነ መቃበር ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ፡፡