መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 15

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ በይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
2እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበረ፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች፡፡
3እርሱም የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
4ነገር ግን በየኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን የአሕዛብን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋቸውም ነበር፤ ስለዚህም ሕዝቡ በየኮረብቶቹ ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤
5በኋላም እግዚአብሔር ዓዛርያስን በቆዳ በሽታ መታው፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ በሽታ ስላልለቀቀው ከሥራው ሁሉ ተገልሎ በተለየ ቤት ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር፤ በዚህም ጊዜ መንግሥቱን ሲመራ የቆየው ልጁ ኢዮአታም ነበር፡፡
6ንጉሥ ዓዛርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
7ዓዛርያስም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በቀድሞ አባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ፡፡
8ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ ስድስት ወር ገዛ፡፡
9እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበሩት ነገሥታት ሁሉ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአት መራ፤ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት ተከተለ፡፡
10ሰሎም ተብሎ የሚጠራው የኢያቤስ ልጅ ሤራ በማድረግ ይብልዓም ተብላ በምትጠራው ስፍራ ንጉሥ ዘካርያስን ገድሎ በእርሱ ፈንታ ነገሠ፡፡
11ንጉሥ ዘካርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
12በዚህም ዓይነት እግዚአብሔር ለንጉሥ ኢዩ ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ በእስራኤል ይነግሣሉ ሲል የተናገው የተስፋ ቃል ተፈጸመ፡፡
13ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በሰማርያ አንድ ወር ብቻ ገዛ፡፡
14ምናሔ ተብሎ የሚጠራው የጋዲ ልጅ ከቲርጻ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገድሎም በእርሱ ፈንታ ነገሠ፡፡
15ሰሎም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም እርሱ የጠነሰሰው ሤራ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
16ምናሔም ከቲርጻ ተነሥቶ በሚያልፍበት ጊዜ የቲፍሳን ከተማ ነዋሪዎችና በዙሪያዋ የነበረውን ግዛት ሁሉ ደመሰሰ፡፡ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለእርሱ እጃቸውን ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ነፍሰ ጡሮችን እንኳ ሳይምር ሆዳቸውን ቀደደ፡፡
17ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ነገሠ፡፡ እርሱም በሰማርያ ዐሥር ዓመት ገዛ፡፡
18እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የኢርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱም እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
19የአሦር ንጉሠ ነገሥት ፎሐ እስራኤልን ወረረ፤ ምናሔም በአገሩ መንግሥት ላይ ሥልጣኑን እንዲያጸናለትና እንዲደግፈው ለመማጠን ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር እጅ መንሻ አድርጎ ለፎሐሰጠው፡፡
20ምናሔም ገንዘቡን የሰበሰበው የእስራኤል ከበርቴዎች እየንዳንዳቸው ኀምሳ ጥሬ ብር አዋጥተው እንዲሰጡ በማስገደድ ነበር፡፡ በዚህም ዓይነት ፎሐ በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄደ፡፡
21ምናሔም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
22ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ፋቂስያስ ነገሠ፡፡
23ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ ሁለት ዓመት ገዛ፡፡
24እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
25በፋቂስያስ ሠራዊት መካከል ፋቁሔ ተብሎ የሚጠራው የሮሜልዩ ልጅ የሆነ አንድ የጦር አዛዥ ከኀምሳ የገለዓድ ሰዎች ጋር ሆኖ ሤራ ጠነሰሰ፤ በሰማርያ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርዬ ጋር ገድሎ በፋቂስያስ ፈንታ ተተክቶ ነገሠ፡፡
26ፋቂስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
27ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ ሃያ ዓመት ገዛ፡፡
28እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
29የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቴልጌልቴልፌልሶር ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካ፣ ያኖዋ፣ ቃዴስና ሐጾር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች እንዲሁም የገለዓድን፣ የገሊላንና የንፍታሌምን ግዛቶች በመውረር ሕዝቡን ወደ አሦር ማርኮ የወሰደው ይኸው ፋቁሔ በነገሠበት ዘመን ነበር፡፡
30የዖዝያንም ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠ በሃያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በንጉሥ ፋቁሔ ላይ ሤራ ጠነሰሰ፤ እርሱንም ገድሎ በእስራኤል ላይ ነገሠ፡፡
31ፋቁሔ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
32የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
33በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ስድሰት ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ኢየሩሳ ተብላ የምትጠራ የሳዶቅ ልጅ ነበረች፡፡
34የአባቱንም የዖዝያንን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
35ነገር ግን በየኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን የአሕዛብን መሠዊያዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጥር በር ያሠራው ይኸው ኢዮአታም ነበር፡፡
36ኢዮአታም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
37እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በይሁዳ ላይ አደጋ እንዲጥሉባት የላካቸው ይኸው ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠበት ዘመን ነበር፡፡
38ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።