1የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
2እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ከኢየሩሳሌም ዮዓዳን ተብላ የምትጠራ ነበረች፡፡
3አሜስያስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠርቶአል፤ ይሁን እንጂ እንደ ቀድሞ አያቱ እንደ ንጉሥ ዳዊት አልነበረም፤ እንደ ዳዊት በመሆን ፈንታ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ፡፡
4ይኸውም በየኮረብታዎቹ ላይ የተሠሩትን የአሕዛብ ማምለኪያዎችን አላፈረሰም፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ በየኮረብታዎቹ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጠኑን እንደቀጠለ ነበር፡፡
5አሜስያሰ መንግሥቱን አደላድሎ እንደ ያዘ ወዲያውኑ፣ ቀደም ሲል ነግሦ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባለሥልጣኖች በሞት ቀጣ፤
6ይሁን እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም፤ ይልቁንም በኦሪት ሕግ እግዚአብሔር «ልጆቻቸው በፈጸሙት ኃጢአት ወላጆች በሞት አይቀጡበትም፤ ወላጆችም በፈጸሙት ኃጢአት ልጆች በሞት አይቀጡበትም፤ እያንዳንዱ ሰው ራሱ በፈጸመው ወንጀል ብቻ በሞት ይቀጣል» ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽሞአል፡፡
7አሜስያስ «የጨው ሸለቆ» እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ዐሥር ሺህ የሚሆኑ የኤዶም ወታደሮችን ፈጀ፤ ሴላ ተብላ የምትጠራውንም ከተማ ይዞ «ዮቅትኤል» ብሎ ጠራት፤ እስከ አሁንም በዚሁ ስም ትጠራለች፡፡
8ከዚህ በኋላ አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን በመላክ «እንግዲህ ና ፊት ለፊት ጦርነት እንግጠም!» ሲል ለጦርነት አነሣሣው፡፡
9ንጉሥ ዮአስ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት «አንድ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ላይ የምትገኝ ኩርንችት የሊባኖስ ዛፍ ‹ለወንድ ልጄ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሴት ልጅህን ስጠኝ› ስትል መልእክት ላከችበት፤ ነገር ግን አንድ የሊባኖስ አውሬ እግረ መንገዱን በዚያ ሲያልፍ ስለ ረገጣት ያቺ ኩርንችት ሞተች፡፡
10አሜስያስ ሆይ! እነሆ አንተ ኤዶማውያንን ድል ስላደረግህ ልብህ በትዕቢት ተሞልቶአል፤ ባገኘኸውም ድል በመደሰት ዐርፈህ በቤትህ ብትቀመጥ ይሻልሃል፤ በአንተና በሕዝብህ ላይ መከራና ውድቀት ስለ ምን ታስከትላለህ?»
11አሜስያስ ግን የዮአስን መልስ ከምንም አልቆጠረውም፤ ስለዚህም ንጉሥ ዮአስ ሠራዊቱን አስከትሎ በአሜስያስ ላይ በመዝመት በይሁዳ ምድር በምትገኘው በቤት ሳሚስ ጦርነት ገጠመው፡፡
12ይሁዳም ድል ተመታ፤ ወታደሮቹም ሁሉ ተበታትነው ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
13ዮአስም የአካዝያስን ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመድረስ ገሠገሠ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ከኤፍሬም ቅጥር በር «የማዕዘን ቅጥር በር» ተብሎ እስከሚጠራው በር ድረስ ጠቅላላ ርዝመቱ ሁለት መቶ ሜትር የሆነውን የቅጥር ግንብ አፈረሰ፡፡
14በዚያም ያገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ፣ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅዱሳትና የቤተ መንግሥቱን ሀብት ሁሉ ጭኖ ወደ ሰማርያ ተመለሰ፤ በመያዣ ስም የተማረኩ ሰዎችንም ይዞ ሄደ፡፡
15ንጉሥ ዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው የጀግንነት ሥራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
16ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ፡፡
17የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የዮአስ ልጅ አሜስያስ ዐሥራ አምስት ዓመት ቆየ፡፡
18አሜስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
19አሜስያስን ለመግደል በኢየሩሳሌም ሤራ ተጠንስሶ ነበር፤ ስለዚህ አሜስያስ ሸሽቶ ወደ ለኪሶ ከተማ ሄደ፤ ነገር ግን ጠላቶቹ ወደ ለኪሶ ሰዎችን ልከው እዚያ አስገደሉት፡፡
20ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡
21የይሁዳም ሕዝብ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጁ የነበረውን ዓዛርያስን አነገሡት፤
22ዓዛርያስም ቀድሞ ተይዛ የነበረችውን ኤላትን ከአባቱ ሞት በኋላ በጦር ኃይል ድል ነሥቶ አስመልሶ እንደገና ሠራት፡፡
23የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፡፡
24ዳግማዊ ኢዮርብዓምም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ ከእርሱ በፊት የነበረውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
25ቀድሞ የእስራኤል ይዞታ የነበረውን በስተሰሜን ከሐማት መተላለፊያ ጀምሮ በስተ ደቡብ እስከ ሙት ባሕር የሚገኘውን ግዛት ሁሉ ድል ነሥቶ እንደገና አስመለሰ፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በጋትሔፌር ተወላጅ አገልጋይ በሆነው በአሚታይ ልጅ በነቢዩ ዮናስ አማካይነት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ነበር፡፡
26እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን አሠቃቂ መከራ ተመለከተ፤ በእስራኤል ውስጥ ባርያዎችም ሆኑ ነጻ ሰዎች ረዳት አልነበራቸውም፡፡
27ይሁን እንጂ እነርሱ ለዘለዓለም ፈጽሞ እንዲደመሰሱ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም፤ ስዚህ በዳግማዊ ኢዮርብዓም አማካይት አዳናቸው።
28ዳግማዊ ኢዮርብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፣ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነት፣ እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩት ደማስቆና ሐማት ለእስራኤል እንዲመለሱ ያደረገበት ታሪካዊ ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
29ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ሞተ፤ በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ዘካርያስ ነገሠ፡፡