መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ተኛ ነገስት 13

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ለዐሥራ ሰባት ዓመት ለመግዛት የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡
2እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓም ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፡፡ ከክፉ ሥራውም ከቶ አልራቀም፡፡
3ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ተቆጥቶ ለሶርያ ንጉሥ አዛሄል፣ እንዲሁም ለልጁ ለቤን ሀዳድ በተደጋጋሚ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፡፡
4ከዚህ በኋላ ኢዮአካዝ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ የፈጸመባቸው ግፍ እጅግ ከባድ መሆኑን ተመልክቶ የኢዮአካዝን ጸሎት ሰማ፡፡
5ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤልን ከሶርያውያን እጅ ነጻ የሚያወጣቸውን መሪ ላከላቸው፤ እነርሱም ከዚያ በፊት በነበረው ዓይነት በሰላም ኖሩ፡፡
6ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ኢዮርብዓም እስራኤልን ወደ ኃጢአት ከመራበት ከክፉ ሥራቸው አልተመለሱም፤ እስካሁንም አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል በሰማርያ ማምለክ ቀጠሉ፡፡
7ንጉሥ ኢዮአካዝ ከኀምሳ ፈረሰኞች፣ ከዐሥር ሰረገሎችና ከዐሥር ሺህ ወታደሮች በቀር ሌላ የተደራጀ የጦር ኃይል አልነበረውም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሠራዊቱን የሶርያ ንጉሥ በአውድማ እንዳለ እብቅ አድርጎ ስለ ደመሰሰበት ነው፡፡
8ንጉሥ ኢዮአካዝ የፈጸመው ሌላው ተግባርና የጀግንነት ሥራው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
9ኢዮአካዝም ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ዮአስ ነገሠ፡፡
10የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ በዚያም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፡፡
11እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
12ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
13ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ፡፡
14ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ «አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!» እያለ አለቀሰለት፡፡
15ኤልሳዕም ንጉሡን «አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ» ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደታዘዘው አደረገ ኤልሳዕም
16ለማስፈንጠር ተዘጋጅ» አለው፤ ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ፡፡
17ኤልሳዕ «የምሥራቁን መስኮት ክፈት» አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም «ፍላጻውን አስፈንጥር!» አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፣ «ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ፡፡»
18ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን «ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!» አለው፡፡ ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፡፡
19ይህም ኤልሳዕን አስቆጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን «አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ» አለው፡፡
20ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም፡፡ ከሞአብ የመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወጉ ነበር፡፡
21አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጸምበት ሰዓት በእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለታየ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኮላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስክሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ፡፡
22ኢዮአካዝ በነገሠበት ዘመን ሁሉ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤላውያንን በመውረር ያስጨንቃቸው ነበር፤
23እግዚአብሔር ግን በቸርነቱ ምሕረትን በማድረግ ረዳቸው እንጂ እንዲደመሰሱ አልፈቀደም፤ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሰጠውን ቃል ኪዳን በማሰብ ሕዝቡን ስላልረሳው ነው፡፡
24የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በሞተ ጊዜ፣ በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ልጁ ቤን ሀዳድ ነገሠ፡፡
25ከዚህም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ቤን ሀዳድን ሦስት ጊዜ ድል ነሥቶ በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ቤን ሀዳድ ይዞአቸው የነበሩትን ከተሞች አስመለሰ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።