1ኢዩ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም አርባ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሳብያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች፡፡
2ካህኑም ዮዳሄ ይመክረውና ያስተምረው ስለ ነበር፣ ኢዮአስ በዕድሜው ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
3ነገር ግን በየኮረብታዎቹ ላይ የሚገኙት የአሕዛብ ማምለኪያዎች ስላልተደመሰሱ ሕዝቡ በዚያ ዕጣን እያጠኑ መሥዋዕት ማቅረባቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፡፡
4ኢዮአስም ካህናትን ጠርቶ በቤተ መቅደስ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ መባ ሆኖ የሚገባውን ገንዘብ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አዘዘ፤ ይኸውም ቋሚ ከሆነው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር መባ ሆኖ የሚቀርበውንና በበጎ ፈቃድ ሕዝቡ የሚያመጣውን ስጦታ ሁሉ የሚያጠቃልል ነበር፡፡
5እያንዳንዱ ካህን ከሚያገለግላቸው ሰዎች የሚገኘውን የገንዘብ መባ ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ገንዘቡንም እንዳስፈላጊነቱ ለቤተ መቅደሱ ጥገና አገልግሎት እንዲያውሉት ነገራቸው፡፡
6ነገር ግን ኢዮአስ እስከ ነገሠበት እስከ ሃያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ላይ ምንም ዓይነት እድሳት አላደረጉም፡፡
7ስለዚህም ኢዮአስ ዮዳሄንና ሌሎቹንም ካህናት ወደ እርሱ ጠርቶ ቤተ መቅደሱን ያላደሳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? ከዛሬ ጀምሮ የምትቀበሉትን ገንዘብ መያዝ የለባችሁም፤ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ይውል ዘንድ ገንዘቡን አስረክቡ አላቸው፡፡
8ካናቱም በዚህ ተስማምተው ቤተ መቅደሱን በራሳቸው ለማደስ የነበራቸውን ተግባር አቆሙ፡፡
9በዚህ ፈንታ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም ወስዶ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ በስተ ቀኝ በሚገኘው መሠዊያ አጠገብ አኖረው፤ የየዕለቱ ተረኞች የነበሩትም ካህናት ለአምልኮ የሚመጡት ሰዎች የሚሰጡትን የገንዘብ መባ እየተቀበሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡት ነበር፡፡
10ሣጥኑም በሚሞላበት ጊዜ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ እየመጡ ገንዘቡን በመቁጠር በከረጢት እያሰሩ ያኖሩት ነበር፡፡
11ትክክለኛውን ሒሳብ አጣርተው ከመዘገቡ በኋላ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ ኃላፊዎች ያስረክቡ ነበር፤ እነርሱም ገንዘቡን ተረክበው ለአናጢዎችና ለግንበኞች ይሰጡ ነበር፡፡
12ለድንጋይ ጠራቢዎች፣ ለማደሻ አገልግሎት የሚውል እንጨትና ድንጋይ ለሚገዙና እንዲሁም ለልዩ ልዩ አስፈላጊ ነገሮች ለሚውል ተግባር ሁሉ ይከፍሉ ነበር፡፡
13ነገር ግን ከብር ለሚሠሩ ጎድጓዳ ሳሕኖች የዐመድ ማጠራቀሚያ ጎድጓዳ ወጭት፣፣ እምቢልታ ወይም ደግሞ ከብርና ከወርቅ ለሚሠሩ ንዋያተ ቅዱሳት ከዚያ ገንዘብ ላይ ተነሥቶ የሚከፈል ሒሳብ አልነበረም፡፡
14ያ ገንዘብ በሙሉ በቤተ መቅደሱ እድሳት ተግባር ላይ ለተሰማሩት ሠራተኞች ብቻ የሚውል ነበር፡፡
15ለሥራው ኃላፊነት የተመረጡትም ሰዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ነበሩ ገንዘቡን የሰጡአቸው ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፡፡
16ስለ በደልና ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚከፈለው ገንዘብ ግን ለካህናቱ ጥቅም የሚውል እንጂ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡
17በዚያ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በጌት ከተማ ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ቀጥሎም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ተመለሰ፡፡
18የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስም ከእርሱ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ማለትም ኢዮሳፍ፣ ኢዮራምና አካዝያስ ለእግዚአብሔር ለይተው ያኖሩትን መባና የራሱን መባ ጨምሮ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች የነበረውን ወርቅ ሁሉ በመሰብሰብ ገጸ በረከት አድርጎ ለንጉሥ አዛሄል ላከለት፡፡ ሐዛሄልም ይህን ተቀብሎ ሠራዊቱን ከኢየሩሳሌም መለሰ፡፡
19ንጉሥ ኢዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
20ከዚህ በኋላ የንጉሥ ኢዮአስ ባለሥልጣኖች አንድ ላይ ተነሥተው አድመውበት ወደ ሲላ ሲሄድ በሚሎ ጥቃት አደረሱበት፡፡
21የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ኢዮአስን ገደሉት፡፡ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ፡፡