1የንጉሥ አካዝያስ እናት ጎቶልያ የልጅዋን መገደል እንደ ሰማች ተነሥታ የንጉሣውኑን ቤተ ሰብ አባላት በሙሉ ገደለች፡፡
2ከእርስዋም እጅ ማምለጥ የቻለ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን አክስቱ የነበረችው በአባትዋ በኩል የንጉሥ አካዝያስ እኅት የንጉሥ ኢዮራም ልጅ ዮሳቤት ከሞቱት ከንጉሥ ልጆች መካከል ወስዳ በመደበቅ ከሞት አዳነችው፤ እርሰዋም ሞግዚቱን ወስዳ በቤትዋ መኝታ ክፍል ውስጥ ስለደበቀችው በጎቶልያ እጅ ሳይገደል ቀረ፡፡
3ጎቶልያ በነገሠችበት ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዮሳቤት ሕፃኑን ኢዮአስን በመደበቅ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመንከባከብ አሳደገችው፡፡
4ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ለንጉሡ ክብር ዘቦችና ለቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ሁሉ ኃላፊ ወደሆኑት የጦር አዛዦች ሁሉ ልኮ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አስጠራቸው፤ በዚያም ሊያደርገው ያቀደውን ይስማሙበት ዘንድ በመሐላ እንዲያረጋግጡለት አደረገ፤ ከዚያም በኋላ የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን አሳያቸው፡፡
5የሚከተለውንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ በሰንበት ቀን ለጥበቃ በምትሰማሩበት ጊዜ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤
6ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ የሱርን የቅጥር በር ይጠብቅ፤ የቀረው አንድ ሦስተኛ እጅ ደግሞ ከሌሎቹ ጥበቃዎች በስተኋላ ያለውን ቅጥር በር ይጠብቅ፡፡
7በሰንበት ቀን ከጥበቃ ነጻ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ንጉሡን ለመከላከል ቤተ መቅደሱን ይጠብቁ፤
8ንጉሥ ኢዮአስን በዙሪያው በምትጠብቁበትም ጊዜ ሰይፋችሁን መዛችሁ ወደሚሄድበት ስፍራ ሁሉ አብራችሁ ሂዱ፤ ወደ እናንተ ለመቅረብ የሚደፍር ማንም ቢኖር ይገደል፡፡ ንጉሡ ሲወጣና ሲገባ ከእርሱ አትለዩ፡፡
9የጦር አዛዦቹም ካህኑ ዮዳሄ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል በሰንበት ቀን ለጥበቃ የሚሰማሩትንና ከጥበቃም የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ጭምር አሰልፈው ወደ ካህኑ ዮዳሄ አመጡ፡፡
10ዮዳሄም በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮችና ጋሻዎች አውጥቶ ለጦር አለቆቹ ሰጣቸው፡፡
11ጭፍሮቹም ሰይፋቸውን እንደ መዘዙ ንጉሡን ከበው በቤተ መቅደሱ በቀኝና በግራ በመሠዊያው አጠገብ እንዲቆሙ አደረጋቸው፡፡
12ከዚያም ዮዳሄ ኢዮአስን አቅርቦ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነለት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጂ አስረከበው፤ በዚህ ዓይነት ኢዮአስ ተቀብቶ ነገሠ፡፡ ሕዝቡም በእጃቸው እያጨበጨቡ፣ ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ አሉ፡፡
13ንግሥት ጎቶልያ የክብር ዘቦቹንና የሕዝቡን ጩኸት ድምፅ በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወደተሰበሰበበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መጣች፡፡
14እዚያ እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባሕል መሠረት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ ቆሞ አየቸው፤ እርሱም በጦር አዛዦችና በእምቢልታ ነፊዎች ታጅቦ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል እያሉ እምቢልታ ይነፉ ነበር፤ ጎቶልያ በድንጋጤ ልብስዋን ቀዳ ይህ በክሕደት የተፈጸመ ሤራ ነው ስትል ጮኸች፡፡
15ዮዳሄም የጦር አለቆችን ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል ጎቶልያን አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርስዋን ለመከተል የሚሞክር ቢኖር ይገደል ሲል አዘዛቸው፡፡
16እነርሱም እርስዋን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያ የፈረስ መግቢያ ቅጥር በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት፡፡
17ዮዳሄ፣ ንጉሡና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ከእግዘአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ፤ እንዲሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ፡፡
18ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ወደ ባዓል ቤተ መቅደስ ሄዶ አፈራረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበረ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የባዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት፡፡ ዮዳሄም ቤተ መቅደሱን በየተራ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ፤
19ከዚህም በኋላ እርሱ፣ የጦር አለቆች፣ የንጉሡ የክብር ዘብና የቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ንጉሡን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት አጅበው እንዲሄዱና ሕዝቡም ሁሉ ከኋላ እንዲከተል አደረገ፤ ኢዮአስም በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ገብቶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፡፡
20ጎቶልያ በቤተ መንግሥት በሰይፍ ስለ ተገደለች ሰው ሁሉ ተደሰተ፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች፡፡
21ኢዮአስም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፡፡