መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ቆሮንቶስ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የተወደዳችሁ ሆይ፥ እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን እየተከተልን ስጋችንን እና መንፈሳችንን ከሚያረክስ ከማናቸውም ነገር ራሳችንን እናንፃ።
2ለእኛ በልባችሁ ስፍራ ስጡን! ማንንም አልበደልንም፥ማንንም አልጎዳንም፥ ማንንም ለራሳችን ጥቅም አልበዘብዝንም።
3ይህንን የምላችሁ ልኮንናችሁ ብዬ አይደለም፤ምክንያቱም አብረን ለመሞትም ሆነ ለመኖር በልባችን ውስጥ አላችሁና ነው።
4በእናንተም ታላቅ መታመን አለኝ፣ትምክህቴም ናችሁ። በመከራዎቻችን እንኳ መፅናናት እና የተትረፈርፈ ደስታ ሞልቶኛል።
5ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ ሰውነታችን እረፍት አልነበረውም። ይልቁንስ በውጭ ግጭት እና በውስጥ ፍርሃት ስለነበረብን በሁሉ አቅጣጫ ተጨነቅን ።
6ነገር ግን ተስፋ የቆረጡትን የሚያፅናና አምላክ በቲቶ መምጣት አፅናናን።
7የእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተም እርሱን ያፅናናችሁት ማፅናናት እኛን አፅናናን። ለእኔም ያላችሁን ታላቅ ፍቅር፥ርህራሄ እና ጥልቅ ሃሳብ ሲነግረን በይበልጥ ተደሰትሁ።
8ምንም እንኳ በመልዕክቴ ባሳዝናችሁም ለምን ፃፍኩ ብዬ አልፀፀትም። ነገር ግን፥የምፀፀተው መልዕክቴ ለጥቂት ጊዜም እንዳሳዘናችሁ ስለማውቅ ነው።
9አሁን የምደሰትበት ምክንያት ስላዘናችሁ ሳይሆን ሃዘናችሁ ወደ ንስሃ ስለመራችሁ ነው። እግዚአብሔር የሚወደው አይነት ሃዘን እየተለማመዳችሁ ስለሆነ በእኛ ምክንያት ያጣችሁት ነገር የለም።
10እግዚአብሔር የሚወደው ሃዘን ፀፀት የሌለበት፥ ወደ ድነት የሚመራ ንስሃን ያመጣል። ዓለማዊ ሃዘን ግን ሞትን ያመጣል።
11እግዚአብሔር የሚወደው ሃዘን ምን አይነት ታላቅ ቁርጠኝነት እንዳመጣላችሁ እዩ። ይህም ታላቅ ቁርጠኝነት ምን ያህል ንፁህ መሆናችሁን፥ ምን ያህል በሃጢያት ላይ እንድትቆጡ እንዳደረጋችሁ፥ ምን አይነት ናፍቆት እንዳሳደረባችሁ፥ ምን አይነት በጎ ቅንዓት እንደፈጠረባችሁ ፥ፍትህ እንድታደርጉም ምን አይነት ጥልቅ መሻት እንዳደረገላችሁ ተመልከቱ! በዚህ በኩል በሁሉም ንፁህ መሆናችሁን አስመስክራችኋል።
12ምንም እንኳ ብፅፍላችሁም የፃፍኩት ለክፉ አድራጊ ወይም በክፉ አድራጎቱ መከራ ለሚቀበል ሳይሆን ለእኛ ምን ያህል እንደምታስቡ በእግዚአብሔር ፊት እንዲታወቅ ነው።
13በዚህ እንበረታታለን። እኛ ከመፅናናታችን በተጨማሪ በቲቶ ደስታ ሃሴት አድርገናል፤ መንፈሱ በሁላችሁ ምክንያት አርፏልና ነው።
14ስለናንተ በመመካት ለእርሱ ተናግሬ ነበር፣እናንተም አላሳፈራችሁኝም። በሌላ አንፃር ስለናንተ የተናገርነው ሁሉ እውነት ነበር፥ለቲቶም ስለናንተ የተናገርነው ሁሉ ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል።
15እርሱም በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ ያደረጋችሁለትን አቀባበል እንዲሁም የሁላችሁንም መታዘዝ በሚያስብበት ጊዜ ለእናንተ ያለው ፍቅር ታላቅ ነው።
16በናንተ ሙሉ መታመን ስላለኝ፥ሃሴት አደርጋለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።